የካቲት ፳፰ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በምግባረ ሰናይ አጠቃላይ ሆስፒታል በመከናወን ላይ ያለውን የማስፋፋፊያ ሥራን ጎበኙ።
ብፁዕነታቸው በሆስፒታሉ ጉብኝት ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት ሲሆን ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ለማሻሻል እና ለማስፋፋት በማቀድ የሚያከናውነው የግንባታ ሥራ የደረሰበትን ደረጃ ለመመልከት የታሰበ ጉብኝት መሆኑ ታውቋል።
ከአሁን ቀደም ሆስፒታሉ በዘመናዊ መንገድ እንዲገነባ ቅዱሰ ሲኖዶስ መፍቀዱን ተከትሎም የዲዛይን ማሻሻያ ሥራ እየተሰራ መሆኑም በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል። አሁን የሚከናወነው የግንባታ ሥራ የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማስፋፋትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
በጉብኝቱ ወቅት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማዘመንና ለማስፋፋት እየተከናወነ ያለው ሥራ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ገልጸው የግንባታ ሥራው በታቀደለት ጊዜ ተከናውኖ ወደ ሥራ መግባት እንዲችል የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።