ታኅሣሥ ፭ቀን፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
————————-
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፥ የባህር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ በእስራኤል በነበራቸው የ፭ ቀናት ሐዋርያዊ አገልግሎት በሀገረ እስራኤል ከሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም ኢትዮጵያውያን በዐበይት በዓላት ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያለምንም መንገላታት ቪዛ በሚያገኙትበት ሁኔታና በሀገሪቱ በሚገኙ የኢትዮጵያውያን ገዳማት ዙሪያ ተነጋግረዋል። በተለይም በዴር ሱልጣን ገዳማችን በየጊዜው ስለሚፈጠረው ሁከትና ኢትዮጵያውያን በአልን በሰላም እንዳያከብሩ ስለሚደርስባቸው በደል አስረድተው የጥንት ይዞታችን ተከብሮ በዓልን በሰላም እንድናከብር ገንቢ ውይይት አድርገዋል።

በሌላ በኩል በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ገዳማት ከሚያገለግሉ መነኮሳት ጋር ገዳማቱ አንድነታቸው ተጠብቆ ሰላምና ፍቅር የነገሠበት አገልግሎት እንዲሰጡ መመሪያ ያስተላለፉ ሲሆን ፤ በሌሎች ጉዳዮች ደግሞ ሰፊ ምክክር ተደርጓል። የኢትዮጵያ ገዳማትንና በገዳማቱ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ሊደረግ ስለሚገባው እገዛና ድጋፍም ከብፁዕ አቡነ ዕንባቆም በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስና ከማኀበሩ ጋር ጥልቅ ውይይት አድርገዋል።

ብፁዕነታቸው በኢየሩሳሌም የሚገኙ ቅዱሳት መካናትን የተሳለሙ ሲሆን ፤ በሀገረ እስራኤል የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ሲመለሱ በቴልአቪቭ ቤንጎርዮን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስና በገዳማቱ በሚያገለግሉ አበው መነኮሳት ሽኝት ተደርጐላቸዋል።© EOTC TV