ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ አገልግሎት ቀጥለዋል።
በቅድሚያ በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ጸሎተ ኪዳን አድርሰዋል ።
በመቀጠልም በታሪካዊ ይዘቱ በዓለም ላይ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሙዝየሞች መካከል አንዱ የሆነውን የእስራኤልን ሙዝየም ጎብኝተዋል። በሙዝየሙ ሲደርሱ ከእስራኤል መንግሥት የፕሮቶኮል አቀባባል ተደርጎላቸዋል። የሙዝየሙ ጉብኝት ዓላማ በክርስትናና በአይሁድ ሃይማኖቶች መካከል ያለውን ተዛምዶ በእውነት ላይ ተመስርቶ መረዳት ነው።
በጉብኝቱም የአባታችን አዳም ከድቀት በኋላ የነበረውን ገጽታ የሚያሳይ ምስለ ቅርጽ፣ ዕፀ በለሷ ከተበላች በኋላ የነበራት ምስል፣ እስራኤል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተለይም ከክርስትና እምነት ጋር ያላት ታሪካዊ ግንኙነት፣ አክሱም ተቆፍረው ከተገኙት ሳንቲሞች (coins ) ተመሳሳይነት ያላቸው ሳንቲሞች፣ የኢየሱስ ክርስቶስመቃብር፣ እግሩ የተቸነከረበት ችንካርና በአፍሪካ ሙዝየም ውስጥ ጎልቶ የሚታየውን የኢትዮጵያ ክፍል (በክፍሉ ውስጥ ሁሉም በሚያሰኝ መልኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀብት የሆኑ የብራና መጻሕፍት ፣ ንዋያተ ማኅሌት፣ የካህናት መገልገያዎች ናቸው) ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ማጠቃለያ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እንደገለጹት በትንሽ ሀብትና አነስተኛ እድሜ ያላቸውን ቅርሶች አሰባስቦ በዚህ መልክ ለዐይን በሚስብ ውብና ማራኪ በሆነ አቀራረብ ለህዝብ ዕይታ ማዘጋጀት ከተቻለ ረጅም እድሜና ሰፊ ታሪክ የሰው ልጅ የታሪክ ባለቤትነት የሚረጋገጥባት ኢትዮጵያና እራሷ ቅርስ ሆና ቅርሶችን እየጠበቀችና እየተንከባከበች የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅርሶቿን በዚህ መልኩ አደራጅታ ለዓለም ብታቀርብ በምጣኔ ሀብትም ሆነ በቱሪዝም ፍሰት ወደር የማይገኝላት አገር ልትሆን ትችላለች።
ከዚህ ያየነውን ልምድ ቀምረን ለመጠቀም እንደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በፈቃደ እግዚአብሔር ጥረት የምናደርግ ይሆናል ብለዋል። በተለይም የኢየሩሳሌም ሞዴል ከተማን በተመለከተ ኢትዮጵያውያንም የዛሬ ማንነታችን የቆመው በትላንታችን መሆኑን ተገንዝበን ታሪኮቻችን መገናኛ ድልድዮቻችን እንጅ ማለያያ የጥላቻ ግርዶሾቻችን እንዳይሆኑ እንደ እስራኤላውያን በትጋት መሥራትና ሁሉንም ሰንዶ አስተማሪ ማድረግ ይኖርብናል ። እየገጠመን ላለው መከራም መድኃኒቱ ታሪክን ለትውልድና ለሀገር ግንባታ ማዋል ነው በማለት አጸጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በመጨረሻም ከእስራኤል መንግሥት ቱሪዝም ሚንስትር ከአቶ ሃም ካትስ ጋር ኢትዮጵያውያን ለልደት፣ ለትንሣኤ ና ለልዩ ልዩ በአላት ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሊመጡ ሲያስቡ ያለምንም መንገላታት ቪዛ በሚያገኙትበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
ክቡር ሚንስትሩም የቆየ ታሪካዊ ግንኙነትና የደም ትስስር ካለን ከኢትዮጵያ ጋር ሃይማኖታዊ ጉዞዎች ያለምንም እንከን እንዲካሄዱ ማድረግ ግዴታችን ነው። ለኢትዮጵያውያን ልዩ እንክብካቤ ለማድረግ እንጥራለን ብለዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅም ስለተደረገላቸው የክብር አቀባበል አመስግነው ለእስራኤልና በአካባቢው ላሉ አገራት እግዚአብሔር አምላክ ሰላም ፍቅር ስምምነት እንዲሰጣቸው ጸልየዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ከጉብኝቱ በኋላ በባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የተያዘላቸውን ፕሬዘንደንታዊ ክፍል በመተው ማረፊያቸውን በደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አድርገዋል።
በጉብኝቱና በውይይቱ ወቅት ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ጋር አብረው የተጓዙ የድል፣ የትንሣኤ፣የአዳ፣ የአፍሮ ሆሊ ላንድና ቆሮንቶስ አስጎብኝ ድርጅቶች ባለቤቶችና የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።©EOTC TV