በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ከሁሉ አስቀድሞ የዘመናት ባለቤት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ አሸጋግሮ በዚህ ታላቅ ጉባኤ እንድንገናኝ ስለፈቀደልን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡ እንደሚታወቀው በብዙ ፈተናዎችና መከራዎች እያለፋችሁ በ42ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ለመገኘት እንኳን ደኅና መጣችሁ፡፡ ሁሉን አዋቂ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ለምንናፍቀውና ስለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለምንመካከርበት ለዚህ ታላቅ ጉባኤ እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ላይ ስለሚመጣ ፈተና ዝግጁ ሆነን እንድንጠብቅቢያስ ገነዝቡንም ሊቁ አባታችን ቢንያሚን ደግሞ ለየት አድርጎ ‹‹ንኵን ድልዋነ ለሃይማኖት እንተ ኢትጸንን መጠርጠር ለሌለባት ሃይማኖትለሚመጣ ፈተና ዝግጁ እንሁን›› ብሎናል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሊመጣ የሚችልን ፈተና አስቀድሞ አውቆ የመውጫ መንገዱንም አዘጋጅቶ መጠበቅ የችግሩን መፍትሔ ግማሽ መንገድ እንደመራመድ ይቆጠራልና፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ወባሕቱ ኅዳጠ ሀለወክሙ ይእዜ ትተክዙ በዘይመጽአክሙ መከራ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል (1ጴጥ 1፥ 6-7)
እንዳለው ያሳለፍነው ዓመት ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ አብዝታ የተፈተነችበት፣ በፈተናውና በደረሰው መከራ ያዘነችበት፣ ኦርቶዶክሳውያን ልጆቻችን የቤተ ክርስቲያንን
ቅጥር አናስደፍርም፣ የቅዱስ ሲኖዶስን አንድነት እናስከብራለን ብለው በቅጽረ ቤተክርስቲያን ደማቸው የፈሰሰበት፣ በሰማእትነት ያለፉትም አስከሬናቸው ሳይነሳ ለቀናት የቆየበት፣ ልጆቿ ከል የለበሱበት፣ ብፁዓን አባቶች እጅግ ያዘኑበት፣ ኀዘናችንን በወጉ ያልገለጽንበት የፈተና ዓመት ነበር፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ብዙ ፈተናዎችን አስተናግዳ እንደየጠባያቸው ሸኝታለች፡፡ ወደፊትም ትፈተናለች፡፡ በኃይለ እግዚአብሔርም ፈተናውን ድል እየነሣች ጉዞዋን ትቀጥላለች፡፡

ነገር ግን በዘመናችን የገጠመን ፈተና በዐይነቱም በይዘቱም የተለየ በመሆኑሁላችንም አገልግሎታችንን፣ የሃይማኖት ጽናታችንንና ዝግጁነታችንን እንድንጠይቅ አድርጎናል፡፡ ምንም እንኳን የደረሰብን ፈተናና እርሱ የወለደው መከራ፣ ስደት፣ ሞት፣ መፈናቀልና ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራ በቃላት ተገልጾ የሚያልቅ ባይሆንም ይህንን እያሰብን ቆዛሚዎች አንሆንም፡፡ ይልቁንም ቅዱስ ጳውሎስ “ዓዲ ንትመካህ በሕማምነሂ እስመ ነአምር ከመ ሕማም ይፌጽም ትዕግሥተ ላዕሌነ፡፡ ወትዕግሥትሰ መከራ ወበመከራ ይትረከብ ተስፋ” ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፣ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፣ በመከራችንም ደግሞ እንመካለን (ሮሜ 5፥ 3-4)
እንዳለ በደረሰብን መከራ የአባቶችና የልጆች አንድነት የታየበት፣ የምእመናን በተለይም የወጣት ልጆቻችን የሃይማኖት ጽናት የተገለጠበት፣ ካህናትና ምእመናን የአባቶቻቸውን ቃል የሰሙበት፣ ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኑን የጠበቀበት፣ ጠላት እንደደገሰው ሳይሆን እንደ መንፈስ ቅዱስ ሀሳብ ልጆቿ ፈተናውን የተጋፈጡበት በመሆኑና አምላካችን እግዚአብሔር ራሔላዊ እንባችንን ተቀብሎ በአጭር ጊዜ መልስ የሰጠበትና ድክመታችንን ያየንበት በመሆኑ በደረሰብን መከራ እንመካለን፡፡

ሐዋርያው ያዕቆብ እንዳስተማረን ፈተናውን በደስታ ተቀብለን መከራው ሳይበግረን ጸንተን ከተገኘን የሕይወትን አክሊል እንጎናጸፋለንና “ኦ አኀው ኩኑ በኩሉ ፍሥሓ ሶበ መንሱት ይመጽአክሙ ዘዘዚአሁ እንዘ ተአምሩ ከመ መከራሃ ለሃይማኖትክሙ ትዕግሥተ ይገብር ለክሙ፡፡ ወብፁዕ ብእሲ ዘይትዔገሣ ለእኪት እስመ ተመኪሮ ይነሥእ አክሊለ
ሕይወት ዘአሰፈዎሙ እግዚአብሔር ለእለ ያፈቅርዎ ”…ወንድሞች ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት፡፡ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለእርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና (ያዕ 1፥ 3-4፣ 12)፡፡
ከፈተናው የተማርነውም እንደወርቅ ተፈትነን ነጥረን በመውጣት ለሶስት ሺህ ዘመናት ጸንታ የቆየችውንና የታሪክ ባለቤት የሆነችውን ቅድስት ሃይማኖታችንን ለትውልድ
ማስተላለፍ ያለብን መሆኑን ነው፡፡

ከመከራው ተምረን ለነገ ፈተና ለመዘጋጀት እንችል ዘንድ ገጥሞን ለነበረ ፈተና ምክንያቶች የነበሩትን በጥቂቱ ማንሳት የግድ ይለናል፡፡

1. የውስጥ አንድነታችን እየላላ መምጣት፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳውና ታሪክም እንደሚነግረን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አጽንቶ እኛ ዘንድ ያደረሳት የአገልጋዮቿ
ካህናትና የተገልጋዮቿ ምእመናን አንድነት ነው፡፡ አሁን ላይ ግን በተለያዩ ሥጋዊ ምኞቶችና ምክንያቶች ከአጥቢያ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ያለን አገልጋዮች የውስጥ አንድነታችን በመላላቱና መለያየታችን በየጊዜው እየሰፋ በመምጣቱ
ሊፈትነን ለሚያደባ ጠላት መንገድ ከፍተንለታል፡፡

በዚህም ተፈትነናል፡፡ እኛ ማናውቃቸው እሱ በሚያውቃቸው ደጋግ አባቶችና እናቶች ጸሎትና እንባ አለፍነው እንጅ መለያየት ያደረሰብን መከራ ዘመነ ሰማዕታትን የሚያስታውሰን ነው፡፡ የመለየታችንና የአንድነታችን መላላት ምክንያቱ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያንና ከልጆቿ ይልቅ ራሳችንን በማስቀደማችን ነው፡፡ የራስን ሥጋዊ ፍላጎት ለማሳካት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሕግ አለማክበር እንደ በጎ ነገር መቆጠሩ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ግላዊነትን ድል ለመንሣት የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት በሕይወታችን መተርጎም አለብን፡፡

“አስተበቁዐክሙ አኀዊነ በስሙ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትበሉ ኵልክሙ አሐደ ቃለ ወኢትተክዙ ወትኩኑ ፍጹማነ
ወኢትትፋለጡ ወሀልዉ በአሐዱ ምክር ወበአሐዱ ልብ – ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጅ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንለምችኋለን” (1ቆሮ 1፡10) በሚለው ኀይለ ቃል ራስን ማስገዛት ተገቢ ነው፤

2. የሌሎች አካላት ዓላማ አስፈጻሚዎች ሆኖ መገኘት፡፡ አሁን ላይ በአገራችን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ጠል ሰዎችእየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ጥላቻ ማንንም ሳይፈሩ በሚዲያዎቻቸው እያወጁ ይደመጣሉ፡፡ የላካቸው ወይም በርቱ ባይ ያለ እስኪመስል ድረስ ያለስሟ ስም ያለታሪኳ ታሪክ መለጣጠፍ የዘወትር ተግባራቸው ሆኗል፡፡

እነዚህ አካላት ራሳቸው ያልቻሉትን መከፋፈል በተለያየ ምክንያት ያኮረፉትን ልጆቿን ተጠቅመው እናታችንን ቤተ ክርስቲያንን ይፈትናሉ፡፡ ከእኛም ዓላማቸውን ሳይረዱና ሳይገባቸው በጊዜያዊና ዕለታዊ ስሜቶች ተገፋፍተው የመርዛማ ተልእኳቸው አስፈጻሚዎች በመሆን ተባባሪዎች አልጠፉም፡፡ ይህም ለግላዊ ስሜቶቻችንም ሆነ ተበደልን ለምንለው በደል መፍትሔ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ፈተና የሚያበዛ ነው፡፡ በመሆኑም የውጭ አካላትን መርዘኛ አካሄድ
ተረድተን ሲኖዶሳዊ መዋቅራችንንና አንድነታችንን አጠናክረን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅና ለትውልድ ማሻገር ውዴታችን ሳይሆን ግዴታችን ነው፡፡

ይህንን ለማድረግ ራሳችንን ለራሳችን ሳይሆን ራሳችንን ለቤተ ክርስቲያን ሰጥተን ማገልገል አለብን፡፡ ይህንን የማንፈጽም ከሆነ ግን ሀሳባችን ሀሳብ፤ ንግግራችንም ንግግር ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፡ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ክቡራን የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች የተከበራችሁ የዚህ ታላቅና ታሪካዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶቻችን እስከ አሁን የመጣንበትንም መንገድ ስንመረምር ስለበጎ ነገር ተናግረን ከሠራነው ይልቅ ያልሠራነው ይበልጣል፡፡ ለአገራችን ሰላም ለሕዝባችን በሰላም ወጥቶ መግባት ከኛ ከሃይማኖት አባቶች ብዙ ይጠበቅ ነበር፡፡ የአገራችን ውስብስብ ችግር አልፈታ
ያለው ምናልባትም እኛ በአምላካችን የተሰጠንን ሓላፊነት አለመወጣታችን ይሆናል፡፡

ለዚህም ነው ትውልዱ ለክፋት ያባከነውን ጊዜ፣ ያጠፋውን ምጣኔ ሀብት ስናይ ተናግረን ከሠራነው በጎ ነገር ሳንናገር የሠራነው ክፋት ይበልጣል የምንለው፡፡ ከበጎነት ክፋትን፣
ከአንድነት መለያየትን ከፍቅር ጥላቻን ልጆቻችን የመረጡ ይመስላል፡፡ ይህስ የሆነው ለምንድን ነው ብለን ብንጠይቅ መልሱ በቃልምበግብርም ተግተን ባለማስተማራችን ምሳሌነታችን እየወረደ በመምጣቱ ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡

ነገር ግን ከዚህ አረንቋ ልንወጣ የምንችለውም በስክነት የምክክር ጊዜ ሲኖረን ነው፡፡ ልንመካከርባቸው የሚገቡ ጉዳዮችም በርካታ ናቸው፡፡ በተለይም በቤተ ክርስቲያንየአገልጋዮች መፈናቀል እየከፋ እንጅ እየተሻሻለ አይደለም፡፡ በየደረጃው ያለን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለጉዳዩ ትኩረትና ጊዜ ሰጥተን መክረን፣ ችግሮችን ለይተን መፍትሄ መስጠት ካልቻልን ፈተናዎቻችን እየከበዱ መሄዳቸው አይቀሬ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ልጅና የእንጀራ ልጅ አይኖርም፡፡
አንዱ አየተመገበ ሌላው ጦም አዳሪ፤ የአንዱ ቤተ ስብእ እየተሰበሰበ የሌላው እየተበተነ የሚሄድበት አሠራር ከአጥቢያ ጀምሮ እየተፈተሸ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ይህም ለነገ የማይባል ተግባራችን መሆን አለበት፡፡

እየተመካከሩ ይሠሩ የነበሩ አባቶቻችን የቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር የሆነውን ሰበካ ጉባኤን መሥርተው ለፍሬ ሲያበቁ ያስተማሩን በፈተና ወጀብ ውስጥ እያለፉም ቢሆን ዘመን ተሻጋሪ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ “ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር ወእንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግዕዞሙ ወሞፃእቶሙ ተመሰሉ በሃይማኖቶሙ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን
ዋኖቻችሁን አስቡ፣ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” (ዕብ 13፡7) እንዳለ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን ስናስብ የመሠረቱትን ነቢዩንና ሰማዕቱን
ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስንና የቅዱስነታቸውን ራዕየ ሰበካ ጉባኤ ለማስፈጸም የደከሙትንና ፈተናውንና መከራውን ተቋቁመው ሰበካ ጉባኤን በዓለትላይ የመሠረቱትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን መዘከር የግድ ይለናል፡፡ እነሱ ባይመሠርቱት ኑሮ ዛሬ ላይ ምን እንሆን ነበር ብለን ስናስብ ለሃሳባችን መልስ እናጣለታለን፡፡ አባቶቻችንን በጊዜው የነበረው ፈተና ከመሥራት አልበገራቸውም፡፡ ይልቁንስ ቀጣዩን ፈተና አሳያቸው አጠነከራቸው እንጅ፡፡ ጠንክረው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በማገልገላቸውም አሁን ለደረስንበት ስኬትና የኑሮ እድገት አብቅተውናልና ደጋግመን እናመሰግናቸዋለን፡፡

በአጠቃላይ የዓለም ስልጣኔ ጫፍ ላይ በደረሰበት ዘመን የምንገኝ በየደረጃው ሓላፊነት ያለብን አገልጋዮች ዓለምን እየቃኘን መሥራት ግድ ይለናል፤ ፈታኞች ሳንሆን የፈተናዋ መድኃኒቶች መሆን አለብን፡፡ ይህንን የማንፈጽም ከሆነ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በኛ ላይ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከቁጣው ለመዳን ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ለቤተ
ክርስቲያን ቅድሚያ መስጠትን በተግባር እንድንፈጽም በታላቅ ትሕትና እያሳሰብኩ በጉባኤያችን በተጨበጠ፣ በተዳሰሰ፣ እውነትን መሠረት ባደረገ ጉዳይ ላይ ተወያይተን የውሳኔ ሐሳባችንን ለቅዱስ ሲኖዶስ እንድናቀርብ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡