ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዶ/ር የሐይማኖት አባቶች ሠላም እንዲሰብኩ አሳሰቡ!

የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የመቱ ፈለገ ሕይወት መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

”  በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። መዝ.65:11 የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ቃል መሠረት አድርገው መልእክታቸውን አስተላለልፈዋል።

ፈጣሪ ዘመናትን አሳልፎ አዲሱን ዘመን የሚያሳየን በመልካምነታችን ሳይሆን በምህረቱ ብዛት ነው ያሉት ብፁዕነታቸው፤ሁሌም  ዓዲስ ዘመን የሚሰጠን ለሥራና ለለውጥ ነው ብለዋል።አዲሱን ዓመት ስንቀበል በሳለፍነው አሮጌ ዓመት ምን የጎደለን ነገር አለ?ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅና ምናልባታም ባጠፋነው ጥፋት ተጸጽተን ንሰሀ ገብተን እንመለስ ዘንድ አዲሱ ዘመን በቸርነቱ ተሰጥቶናል ብለዋል።

በሀገሪቷ ውስጥ በሁሉም ስፍራ ሠላም መጥፋቱ ዋና አጀንዳ ሆኗል ያሉት ብፁዕነታቸው ፤ በእኛ መሀል ሠላም የለም ፣ሁሌም መጣላት የሰርክ ተግባራችን ሆኗል፤ በየስፍራው የሚሰማው ዜና አሳዛኝ እየሆነ መጥቷል፣ጦርነት ሀገሪቷን ወደ ኋላ እየመለሳት ነው፣ ይህ ሁሉ የበደላችን ውጤት ነውና በአዲሱ ዓመት ወደ ልባችን ተመልሰን ልንለውጥ ይገባናል ብለው የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች  ሠላምን አብዝተው በመስበክ በሕዝብ መሀል ስምምነትና መተማመን  እንዲኖር መስራት አለባቸው  ብለዋል።

የሰው ልጅ በችሮታ የተሰጠውን ጊዜ ተጠቅሞ ካልተለወጠ የተለወጠ  ዘመን ማክበሩ ጥቅም የለውም ብለዋል። ብፁዕነታቸው አያይዘው  በርካትቶቻችን በአዲሱ ዘመን አስበን ልብሳችንን እንቀይራለን እንጂ ልባችንን አንቀይርም ብለው በውስጣችን ያለው  የድንጋይ ልብ አውጥተን የሥጋ ልብ የምህረትና የፍቅር ልብ ሊኖረን ይገባል በለዋል።

በአዲሱ ዘመን ጋራና ሸንተረሩ አበባን ለብሰው ደምቀውና አምረው ተቀይረው ይታያሉ ያሉት ብፁዕነታቸው የሰው ልጅ ግን አይቀየርም  ከምድር አበባ አንሰናልናል በእውነት ወደ ፈጣሪያችን መመለስ አለብን ብለው  ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ እንደሚጠፋ እንስሳ  እየሆነ መምጣቱ አሳሳቢ ነውና በተጨመረልን ዓዲሱ ዘመን ልንመለስ ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች፣በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ለሀገረ ስብከታችን ሕዝብ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወንጌላዊ ወደ ዘመነ ማቴዎስ ወንጌላዊ በሠላምና በጤና  አሸጋገረን አሸ፡ሀጋገራችሁ ብለዋል!

ጳጉሜ 5/2016 ዓ. ም
የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሚዲያ