ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ስብሰባ እየተካፈሉ ይገኛሉ፤

ኅዳር ፲፰ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ስብሰባን ለመካፈል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ወክለው የተጓዙ ሲሆን ስብሰባው በጄናቫ ቦሴ የቴዎሎጅ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ በየጊዜው በሚያደርጋቸው ከፍተኛ ጉባኤዎች ላይ ቤተ ክርስቲያን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በሚመራ ልዑክ የምትሳተፍ ሲሆን በዚሁ መሠረት ከኅዳር 17-20 ቀን 2016 ዓ/ም በሚደረገው ጉባኤ ለመገኘት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የተወከሉ ልዑካንን በመምራት በጉባኤው እየተሳተፉ መሆኑ ታውቋል፡፡

ብፁዕነታቸው በቅርቡ በቅዱስ ሲኖዶስ የታወጀውም የጸሎትና ምኅላ መርሐ ግብር ላይ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሲሳተፉ የቆዩ ሲሆን ከጉዳዩ አስፈላጊነት አንፃር ወደ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ቢጓዙም በዚያው ባሉበት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያወጀችውን ጾምና ጸሎተ ምኅላ የተረዱ የጉባኤው ተሳታፊዎች እነሱም ከኢትዮጵያውያን ጋር ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ አብረው መሆናቸውን በጉባኤው ላይ ገልጸዋል፡፡

ብፁዕነታቸውም የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለመፈጸም ባሉበት ከልኡካናቸውና ጋር ሥርዓቱን እያካሄዱ መሆኑ ታውቋል፡፡