የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
+ + +
ብፁዕ ወቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት የእሥራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር የሆኑትን ክብርት ሻረን ሃስኬል፣ በኢትዮጵያ የእሥራኤል አምባሳደር ክቡር አብርሃም ንጉሤን እና ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎችን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ ክብርት ምክትል ሚኒስቴር ሻረን ሃስኬል በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ለእርሳቸውና ለመጡት ልዑካን በተደረገላቸው የክብር አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸው እሥራኤል የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ፤ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በእሥራኤል ሀገር መንግሥት በኩል ያለውን ፍላጎት አስረድተዋል፡፡

ቅዱስነታቸውም የሃይማኖት መሠረት የሆነችው እሥራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ከዘመነ ኦሪት ጀምሮ ሰፊ ትስስር ያለው መሆኑን በማስታወስ ዓለም በልዩ ልዩ መልኩ እየተፈተነች ባለበት ወቅት በእሥራኤልና ፍልስጥኤም መካከል ተከስቶ በቆየው ጦርነት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው በኢየሩሳሌምና አካባቢዋ የሚገኙ ገዳማት፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ አብያተ እምነት እና ታሪካዊ ቦታዎች በጦርነቱ ጉዳት እንዳይርስባቸው ጥበቃ በማድረግ የእሥራኤል መንግሥት የወሰደውን ጥንቃቄ በማድነቅ አመስግነዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ከእሥራኤል ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ሰፊ ውይይት ቤተ ክርስቲያናችን ከእሥራኤል መንግሥት ጋር በጋራ የምታከናውናቸው ተግባራትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግጋት ባከበረ መልኩ ማዕከላዊ አሠራርን በመጠበቅ አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡