ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የብፁዕ አቡነ ሰላማ የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም እና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የበላይ ጠባቂ ሊቀጳጳስ ዕረፍትን በማስመልከት ያስተላለፉት አባታዊ የሐዘን መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

«መኑ ሰብእ ዘየሐዩ ወኢይሬእያ ለሞት: ሕያው ሆኖ የሚኖር ሞትንስ የማያይ ማን ነው?»
መዝሙር ፹፱፥፵፰

የትህትና፣ የጸሎት ሕይወት እና የመልካምነት ምሳሌ የነበሩት ብፁዕ አባ ሰላማ ሊቀ ጳጳስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን የሰማነው በታላቅ ሐዘን ነው።

ያለንበትን ፈተና የበዛበት ዘመን በጸሎት የሚያሻግሩ አባቶችን ማጣት ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ ቢሆንም በቅዱስ መጽሐፍ ሞትን ሳያይ ሕያው ሆኖ መኖር የሚችል ማን ነው? እንደተባለ ሰው በምድር ላይ የሚኖርበት ዘመን በእግዚአብሔር ዘንድ የተቆጠረ እና የተለካ በመሆኑ ብፁዕነታቸው ሃይማኖትን ጠብቀውና መልካሙን ገድል ፈጽመው ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር በክብር ተሸጋግረዋል።

ብፁዕነታቸው በዕረፍተ ሥጋ ከእኛ በመለየታቸው ጥልቅ ሐዘን ቢሰማንም በሰማይ የሚጠብቃቸውን ክብር እያሰብን እንጽናናለን።

የብፁዕነታቸውን ነፍስ በቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት አጠገብ ያሳርፍልን!
ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እና ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውም መጽናናትን ያድልልን!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
አሜን!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም 18 ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት
ዋሽንግተን ዲሲ አሜሪካ