ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የግብፅ  ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልዑካንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

ጥር 24 ቀን 2017.ዓ.ም.
=================
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በብፁዕ አቡነ አምባ ቢመን  የሚመራውን የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ልዑካንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል ።ልዑካኑ  ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ   የተላከ የሰላምታ መልእክት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በማቅርብ  በሁለቱ ተቋማት መካከል  የነበረውን የጋራ ትብብር በማጠነከር ላይ ውይይት አድርጓል። እንደ ልዑካኑ ገለጻ ከዚህ በፊት በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የሚገኙ የጋራ የመገልገያ ሥፍራዎችን  በጋራ መጠቀም የሚስችል አንድነት  የነበረን በመሆኑ አሁንም የተለመደውን ሥራ ማለትም  የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  በምትገኝበት  ቦታ ሁሉ የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን  እንድትገለገል የኮፕትክ ቤተክርስቲያን ባለችበት ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን  መገልገል እንድትችል የሚያስችል ሁኔታን ማስቀጠል ነው ብለዋል ።

ልዑካኑን በጽሕፈት ቤታቸው ያነጋገሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይዘውት የመጡት ሐሳብ የነበረና በመገልገያ ሥፍራ በማጣት የሚቸገሩ ምዕመናን  የሚታደግ ሐሳብ ነውና በአድናቆትና በደስታ   ተቀብለነው እየተገበርነው ያለ ቢሆንም አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስም ይህንን የሰላም መልእከተኛ እና በሁለቱም ተቋማት ውስጥ የሚገለገሉ ምዕመናን ችግርን የፈታ ሐሳብ በልዑካኑ በኩል የማጠናከሪያ ሐሳብ እንድንሰጥበት ስላደረጉ እናመሰግናለን ብለዋል።

በመቀጠልም ልዑካኑ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ  የግብፅ ኮፕቲክ  ፓትርያርክ የተላከውን ስጦታ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ያስረከቡ ሲሆን ቅዱስነታቸውም  ስለ ስጦታው አመስገነዋል። በመጨረሻም ልዑካኑ ስለተደረገላቸው መልካም አቀባበልና ይሁንታ መደሰታቸውን ገልጸው የቅድት ሥላሴ ካቴድራል በኢትዮጵያውያን ምዕመናን ትከሻ ተሠርቶ ማለቁ እጅግ ደስ እንዳሰኛቸው በመግለጽ የግብጽ ኮፕቲክ እንደተለመደው በካቴድራሉ መገልገል የሚችሉበት  መንገድ ስለ ተመቻቸላቸው አመስገነው የውይይቱ ፍጻሜ ሆኗል።