ጥር 29 ቀን 2016 ዓ.ም
================
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
+++++++++++++

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዛሬ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማኅበር ባዘጋጀው የነዳያን ምገባ መርሐ ግብር ላይ በመገኘት ነዳያንን በጋራ ከመገቡ በኋላ ቃለበረከት፣ቃለምዕዳንና ቃለቡራኬ ሰጥተዋል።

በዚሁ ጊዜም ማኅበሩ በተለይም በ2016ዓ.ም በጀት አመት ያከናወናቸውን መንፈሳዊ፣ማኅበራዊና ልማታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ በቪዲዮ የተቀነባበረ ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን የማኅበሩ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ መጋቤ አእላፍ ጸጋዬ የእንኳን ደህና መጡ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ መምህር ኤልያስ ሙላቱ በማኅበሩ የተከናወኑ ዋናዋና ተግባራትን የተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ አዳምጠዋል።

የማኅበሪ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ መጋቢ አእላፍ ጸጋዬ ደበበ በመልዕክታቸው ቅዱስነታቸውና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች ማኅበሩ ባዘጋጀው የምገባ መርሐ ግብር ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።

በመቀጠልም ቅዱስ አባታችን ቤተክርስቲያንን ለመምራት ወደዚህ የተቀደሰ ኃላፊነት ከመጡ ጀምሮ ፍጹም በሆነ ቅድስናና ንጽሕና፣ትህትናና ትዕግስተኝነት ያከናወኑት ሐዋርያዊ አገልግሎት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ መሆኑን የሚያረጋግጠው በቤተክርስቲያናችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የገጠማት ፈተናዎችን ሁሉ በቅዱስታቸዎ ጽኑ ጸሎት ያለፈቻቸው መሆኑን ጠቁመው የቅዱስነታቸው ጽኑዕ አቋምም ቤተክርስቲያናችን በቀጣይ ይገጥማት የነበረው አደጋ በእጅጉ የቀነሰ መሆን የቻለው በቅዱስነታቸዎ አርቆ አሳቢነትና ትዕግስት መሆኑን እኛ የመንፈስ ቅዱስ ልጆችዎ የምናቀው ሃቅ በመሆኑ በቅዱስነትዎ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፍጹም ደስተኞች መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ።ብለዋል።

በመጨረሻም ማኅበራችን ከጠቅላይ ቤተክህነት እውቅና ማግኘቱን ተከትሎ ከዚህ በኋላ የማኅበራችን ሥራዎችን በሙሉ በቅዱስነትዎ አመራር ሰጪነትና በጠቅላይ ቤተክህነት ማኅበራት ማደራጃ ቁጥጥርና ክትትል መምሪያ በኩል ተቋማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ሥራችንን በመፈጸም የሚጠበቅብንን አገልግሎት በብቃት የምንወጣ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እወዳለሁ ብለዋል።

አያይዘውም ማኅበራችን ሕጋዊ ቅርጽ ኖሮት በቤተክርስ
ቲያናችን ሕግጋት መሰረት ሥራውን ማከናወን እንዲችል እና ሕጋዊ ፈቃድ እንዲያገኝ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ከፍተኛ አባታዊ ድጋፍ ላደረጉልን ለብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ለብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ፣ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ያለኝን ከፍተኛ ክብር በቅዱስነትዎ ፊት ስገልጽ በታላቅ ደስታ ነው።በማለት መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።

የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ መምህር ኤልያስ ሙላቱ ማኅበሩ በተለይም በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት በመንፈሳዊ፣ማኅበራዊና ልማታዊ ሥራዎች ያከናወናቸውን ዝርዝር ተግባራትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ዝርዝር ሪፓርት ያቀረቡ ሲሆን ማኅበሩ በበጀት ዓመቱ ብር 968,534,947,00 (ዘጠኝ መቶ ስልሳ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ አራት ሺህ )ወጪ በማድረግ ስኬታማ ሥራን አከናውኗል ብለዋል።

በተያዘው መርሐ ግብር መሰረትም ቅዱስነታቸውና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በነዳያን ምገባ መርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሲሆን በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ላይም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ድሆችን የሚረዳው ልጃችንን ሥራዎች ለማየት በመገኘታችን ደስተኞች ነን ድሆችን የሚያበላ፣የታመሙትን የሚረዳ፣የታረዙትን የሚያለብስ ንዑድ ክቡር ነው እግዘብሔር የሚወደው ትልቁ ነገርነው ይሔ ነውና ካሉ በኋላ እግዚአብሔር ለሰዎች ሀብት የሚሰጠው ሀብቱን ለድሆች እንዲያካፍል ነው።ልጃችን የሚያደርገው መልካም ሥራ እግዚአብሔር የሚያዘውንና የሚወደውን ነው መሔድም መብላትም ያቃታቸውን የሚንከባከበው ልጃችንን እግዚአብሔር ይጠብቅህ፣ሐብትን ንብረትህን ይባርክልህ በማለት መልዕክታቸውን ካጠቃለሉ በኋላ ቃለ በረከትና ቃለ ምዕዳን በመስጠት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።

ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማኅበር በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማኅበራት ማደራጃ ቁጥጥርና ክትትል መምሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣውን የማኅበራት ምዝገባ መስፈርቶችን በማሟላት ሕጋዊ ዕውቅናና ፈቃድ የተሰጠው መሆኑ ይታወቃል።