ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን በተመለከተ በትግራይ ተፈናቃዮች የተደረገው መሰረተ ቢስ ውንጀላ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም ወደ አሥመራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር የተገናኙት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኤርትራና በኢትዩጵያ ስምምነት በተደሰተበት ማግስት የተፈጠረውን ሰላምና ዕርቅ እውቅና ለመስጠት በተደረገ ሥነሥርዓት ላይ ለመገኘት የአማራ ክልል ልዑክ በመሆን መጓዛቸው በቀጥታም ህነ በተዘዋዋሪ ከትግራይ ጦርነት ጋር ግንኙነት የለውም።
ብፁዕነታቸው ወደ አሥመራ በተጓዙበት ወቅት በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የትግራይ ክልል የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በሐዋሳ በተደረገ ስብሰባ ላይ ዶ/ር አቢይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስቴር ከኤርትራ ጋር ሰላም እንዲፈጠር በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደረጉትን ጥረት በማሞገስ እውቅና በሰጡ ማግስት ብፁዕነታቸው አሥመራ መገኘታቸው በምን መመዘኛ ወንጀል ሊሆን ቻለ?የአክሱም ሐውልትን በስጦታ ማበርከትስ ከኢትዮጵያዊነት መገለጫዎቻችን ቅርሶች አንዱን ከማበርከት የዘለለ ሌላ ትርጉም እንደምን ሊሰጠው ይችላል?
ይልቅኑ ከጦርነቱ አስቀድሞ ችግር እንዳይፈጠርና ጦርነት እንዳይቀሰቀስ በብፁዕነታቸው አሳሳቢነት በአማራና በትግራይ ክልላዊ መንግስታት በኩል የሰላምና የአንድነት ውይይት እንዲካሔድ የተደረገው ጥረትና በትግራይና በፌደራል መንግስት መካከል ጦርነት አንዳይቀሰቀስ ለማድረግ ብፁዕነታቸው ያቀረቡት ሀሳብ በራሳቸው በትግራይ ክልል አባቶች እምቢተኝነትና ፌዝ የተሞላበት ትችት ሳይሳካ መቅረቱን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሚያውቁት ሀቅ ነው።
ብፁዕነታቸው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ሥራአስኪያጅ ከመሆናቸው በፊት ጦርነቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንዳንድ የትግራይ ሊቃውንትና ተወላጆች የደረሰባቸውን የሥራ መፈናቀል በተመለከተ የቋሚ ሲኖዶስ አባል በነበሩበት ጊዜ ሊቃውንቱና የትግራይ ተወላጆች ወደ ሥራና ደመወዛቸው እንዲመለሱ ከፍተኛውን ዋጋ የከፈሉና ውሳኔው እንዲወሰን ያደረጉት ታሪካዊ ተጋድሎ ለምን ተረሳ?ከዚሁ ጋር ተያይዞ በወቅታዊ ሁኔታ የሚታሰሩ የትግራይ ተወላጆችን በመከላከል፣የታሰሩትን በመጠየቅና በማስፈታት ለፈጸሙት ተጋድሎስ እውቅና መንፈግስ ምን ይሉታል?
ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ከሆኑ በኋላም በቋሚ ሲኖዶስ ደረጃ አስቀድመው የወሰኗቸው ውሳኔዎች በተሟላ ደረጃ እንዲፈጸሙ ለማድረግ ካደረጉት ጥረት በተጨማሪ በችግሩ ምክንያት ያለደመወዝና ያለሥራ የተቀመጡ የክልሉ ተወላጆችና ሊቃውንት በአሰሰቸኳይ ሥራ እንዲሰጣቸውና ደመወዛቸው ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ እንዲከፈላቸው በማድረግ እያደረጉት ያለው ተጋድሎ በትግራይ በኩል ጆሮ ዳባ ልበስ ቢባልም በአዲስ አበባ የሚገኙ የክልሉ ተዘላጆች የሚመሰክሩት ሀቅ ነው።
አሁንም በትግራይ አባቶችና በኢትዮጵያ እርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መካከል ያለው ችግር ቀኖና ቤተክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ፣ቅዱስ ሲኖዶስ ይቅርታ እንዲጠይቅና የስምምነት አመቻች ኮሚቴውም ሥራው የተሳካና ውጤታማ በሆነ መልኩ ማከናወን እንዲችል በማድረጉ ረገድ በሚገባ ኃላፈነታቸውን ፍጹም ተቋማዊ በሆነ መልኩ በመወጣት ላይ ያሉ ጠንካራ አባት ናቸው።
ይህን ሁሉ ተቋማዊ ተጋድሎ በቅንነትና በኃላፊነት መንፈስ የሚፈጽሙ አባትን ባልተገባ መንገድ መውቀስና መወንጀል ታዲያ ምን ይሉታል?ዛሬ በትግራይ የተደረገውን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጉዞን ተከትሎ ተፈናቃይ ወገኖችን በመወከል በተላለፈው መልዕክት ላይ የተገለጸውም በምንም መመዘኛ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን የማይወክል፣ስብዕናቸውን የማይገልጽና የማይመለከታቸው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ሐምሌ ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ