ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ “ተደራሽነት ያለው የሕዝብ ግንኙነት ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ ለአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊዎች የሁለተኛ ቀን ሥልጠና በሕዝብ ግንኙነት ምንነት፣ አሠራር፣ አደረጃጀትና በእርቶዶክሳዊ ማኅበራዊ
ሚዲያዎች አጠቃቀም ዙሪያ እየተሰጠ ነው።

በዘርፉ ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ባላቸው መምህራን እየተሰጠ ያለው ሥልጠና በቡድን ውይይት ዳብሮ የጋራ ውይይት እየተደረገበት የሚገኝ ሲሆን በማጠቃለያም በመምሪያው ዋና ኃላፊ የማጠቃለያ መልዕክትና የሥራ መመሪያ የሚሰጥ ሲሆን የመምሪያውንና የአህጉረ ስብከትን የሕዝብ ግንኙነት በማስተሳሰር ወጥ፣ ተቋማዊና ተዓማኒነት ያለው የመረጃ ፍሰት የሚፈጠርበት ሥርዓት እንዲዘረጋ ይደረጋል።

ሥልጠናው በነገው እለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ለአሰልጣኞችና በስልጠናው ላይ ለተሳተፉ የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊዎች የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት ሰጥተው አባታዊ መልዕክት፣ ቃለ በረከትና ቃለ ምዕዳን ካስተላለፉ በኋላ የሥልጠናው መርሐ ግብር ይጠናቀቃል።