ግንቦት ፲፯ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ “ተደራሽነት ያለው የሕዝብ ግንኙነት ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ ለአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊዎች በሕዝብ ግንኙነት ምንነት፣ አሠራር፣ አደረጃጀትና በእርቶዶክሳዊ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀም ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው ሥልጨና ተጠናቀቀ።

በዛሬው እለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ለአሰልጣኞችና በስልጠናው ላይ ለተሳተፉ የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊዎች የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት ከቅዱስነታቸው እጅ ተቀብለዋል።በዚሁ ጊዜም ቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ መልዕክት፣ ቃለ በረከትና ቃለ ምዕዳን አስተላልፈዋል።

በዚሁ ጊዜም የተዘጋጀው በለ ፲ ነጥብ የአቋም መግለጫ ተነቧል። የአቋም መንለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

‹‹አምላከ ሰማይ ይረድአነ ወንህነ አግብርቲሁ ንትነሣእ ወነሐንጽ ሎቱ፡፡››
‹‹የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፡፡››
ነህምያ 2፡20

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና ኃላፊ፤ ክቡራን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያና ድርጅቶች ኃላፊዎች፤ ክቡራን ሠልጣኞች፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔር ረድቶን የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን እና የብፁዓን አባቶቻችን ጸሎት አግዞን ይህንን የቤተ ክርስቲያናችንን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ የምንችልበትን የሥልጠና፣ የውይይትና የምክክር መርሐ-ግብራችንን አጠናቀን በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ለመባረክ በመብቃታችን ታላቅ መንፈሳዊ ሐሴት የተሰማን መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ በመረዳትና ያሉባትን ፈተናዎች በጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለመወጣት በማሰብ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ለእኛ በየአህጉረ ስብከቱ ላለን የሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊዎች ካዘጋጀውና ከ ግንቦት 15 – 17 ቀናት 2016 ዓ/ም ከተሰጠው የሥልጠና፣ የውይይትና የምክክር መርሐ-ግብር ዘርፈ ብዙ እውቀትን ገብይተናል፡፡

በሥልጠና መርሐ-ግብሩ ያገኘነውን ዕውቀት፣ ግንዛቤና ምክረ-ሐሳብ መነሻ በማድረግም እግዚአብሔር አምላካችን እንደሚረዳን በማመንና የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን እና የብፁዓን አባቶቻችንን ጸሎት ተስፋ በማድረግ በሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልግብንንና ዘመኑን የዋጀ መንፈሳዊ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀታችንን ስንገልጽ በታላቅ ደስታ ነው፡፡

ለሦስት ቀናት በቆየው የሥልጠና መርሐ-ግብር፡-
1.ኛ ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገራችን ያበረከተቻቸውን ወደር የለሽ አስተዋጽኦዎች ተረድተናል፡፡
2.ኛ ስለ ሕዝብ ግንኙነት ምንነት፣ ተልእኮ፣ የአፈጻጸም ስልትና የውጤታማነት ግምገማ ተምረናል።
3.ኛ ስለ ሕዝብ ግንኙነት ሙያዊ ስነ ምግባር እና የሕግ ተጠያቂነት ከፍተኛ ግንዛቤ አግኝተናል።
4.ኛ የቤተ ክርስቲያናችንን ልማትና ተግዳሮት በንቃት በመከታተል፤ የሚነሡትን አሉታዊ አመለካከቶች ወይም የተሳሳቱ ግንዛቤዎች በማጥራት በምእመናን እና በማኅበረሰቡ መካከል መተማመንና መከባበር እንዲኖር በትጋት መሥራት እንዳለብን ተረድተናል።
5.ኛ ከጠባቂነት በመውጣት በቆራጥነት፤ በበቂ ክህሎት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ፊት ለማሻገር ጠንክረን መሥራት እንዳለብን ተገንዝበናል፡፡
ከእነዚህ ግንዛቤዎች በመነሣትም ቤተ ክርስቲያናችን በሕዝብ ግንኙነት መስክ ውጤታማ ትሆን ዘንድ የሚከተሉትን ጠቃሚ ተግባራት ለመፈጸም እኛ በሥልጠናው የተሳተፍን የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊዎች እግዚአብሔር አምላካችንን አጋዥ አድርገን በብፁዕ ወቅዱስ አባታችንና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፊት ቃል እንገባለን፡፡
6.ኛ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በእቅድ በመምራት፣ ፈንድ በማፈላለግ፣ የሚዲያ ሠራዊትን በስልጠና በማጠናከርና የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማሟላት ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ቃል እንገባለን፡፡
7.ኛ በአህጉረ ስብከት የሚከሰቱ ማናቸውንም አወንታዊ ዜናዎችና አሉታዊ ተግዳሮቶች ሳምንታዊ በሆነ መርሐ-ግብር ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በተከፈተልን የግንኙነት መስመር ለማስተላለፍ ቃል እንገባለን፡፡
8.ኛ የቤተ ክርስቲያናችንን ነባራዊ ሁኔታ በንቃት በመከታተልና ትክክለኛ መረጃዎችን በመስጠት፤ አሉታዊ አመለካከቶችን እና የተሳሳቱ ግንዛቤዎች የማጥራት ሥራን በትጋት ለመሥራት ቃል እንገባለን።
9.ኛ ቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ እሴቶቿን እንደ ጠበቀች፤ ከወቅታዊ ጉዳዮችና የመገናኛ መንገዶች ጋር በመላመድ በምታደርገው ጉዞ የሚገጥሟትን እንቅፋቶች በድል መሻገር እንድትችል የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
10.ኛ ማኅበራዊ ሚዲያ የሌለን አህጉረ ስብከት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከፍተን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓቷን፣ ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ክብረ በዓላቶቿን፣ የአደባባይ በዓላቶቿን፣ የሀገረ ስብከታችንን የልማት፣ የስብከተ ወንጌልና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ለምእመናንና ለቤተክርስቲያናችን ወዳጆች ተደራሽ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
ለዚህም የቅዱስ አባታችንና የብፁዓን አባቶቻችን ጸሎት ትርዳን፡፡

ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ/ም.
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ