ሚያዚያ ፲፬ቀን፳፻፲ወ፮ ዓ/ም
የአዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
በሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ድርጅት አዘጋጅነት የተሰናደው “ንጹሕ ምንጭ ኢትዮጵያ ልዩ ታሪካዊ ዐውደ ርእይ” በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ ጉብኝትና ቡራኬ ተጠናቀቀ።
ዐውደ ርእዩ ከአንድ ሳምንት በላይ በይታ ላይ የቆየ ሲሆን ትናንት ሚያዚያ ፲፫/፳፻፲፮ ዓ/ም በቅዱስነታቸው ጉብኝትና ቡራኬ ፍጻሜው ሆኗል።
በሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ድርጅት አማካኝነት ተዘጋጅቶ ለእይታ የበቃው ዐውደ ርእይ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ትውልዳዊ ሀብቶችን በትንናትናዊ ውበታቸው በአሁናዊ ቅኝት የቀረበበት ትውልዱን የሚመጥን ሥራዎች የታዩበት ነው ተብሏል።
በመርሐ ግብር ከቅዱስነታቸው ጋር ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ሌሎች ብፁዓን አባቶች፣ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሐላፊዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ኦርቶደክሳውያን ተገኝተዋል።