“አስመ የአክለክሙ ዘኀለፈ መዋዕል ዘገበርክሙቦቱ ፈቃዶሙ ለአህዛብ”“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” /1ኛ ጴጥ. 4፥3/፡፡
“አስመ የአክለክሙ ዘኀለፈ መዋዕል ዘገበርክሙቦቱ ፈቃዶሙ ለአህዛብ”“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” /1ኛ ጴጥ. 4፥3/፡፡
ውድ ኦርቶዶክሳውያን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
እንኳን ብርሃናት ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት የዓመት ዑደታቸውን ጨርሰው ለሚጀምሩበት ርእሰ ዐውደ ዓመት ለሆነው ለኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ።
የአዝማናት ባለቤት አምላካችን እግዚአብሔር ሳይገባን በዘመን ላይ ዘመንን እየጨመረልን በየዘመናቱም ብዙ መልካም ነገር እያከናወነልን ነው። ይህም የአምላካችንን ፍቅር የሚያስረዳንና በተጨመሩልን ዘመናት የትናንት ስህተታችንን አርመን የተጣላን እንድንታረቅ፣ የበደልን እንድንክስ፣ ግፍ ከመሥራትና ድሀን ከመበደል እንድንርቅ እንዲሁም ህገ ወንጌልን አምነን የታረዘን እንድናለብስ፣ የተጠማን እንድናጠጣ፣ የተራበን እንድናበላ እንጂ፤ በቀደመ የኃጢአት ሕይወት እንድንመላለስ እንዳልሆነ የሚያስታውሰን ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” እንዳለው ያለፈው ዘመናችንን ወደኋላ ትተን አሮጌውን ሰውነት አውልቀን አዲሱን ሰው በመልበስ የተጨመረልንን አዲስ ዓመት ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበት ከጠብ ከክርክርና ከመገዳደል የምንወጣበት በተግባረ ክርስትናና በፍቅረ ቢጽ የምናሸበርቅበት እንዲሆን አደራ እንላለን። አዲሱ ዓመት በሀገራችን ያሉ ክፉ ነገሮች ሁሉ ተወግደው ፍጡራን ሁሉ መውጣት መግባታቸው የሰላም እንዲሆን አምላከ ሰላም ወደሆነው አምላካችን ዘወትር እንጸልያለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
አባ ሕርያቆስ የሀድያ ስልጤ የደቡብና ምዕራብ
አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ