“እግዚኦ ሚ በዝኁ እለ ይሣቅዩኒ፦አቤቱ፥ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ ! ” (መዝ. 3፡1)


አባታዊ የማጽናኛ መልእክት

በጎፋ ዞን፣ በገዜ ጎፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት ናዳ እጅግ ብዙ የሚሆኑ ወገኖቻችን በመሞታቸው ታላቅ ኀዘን ተሰምቶናል ። ምንም እንኳ የመከራ ድሀ ባንሆንም ይህ መከራ ለነጋሪውም ለሰሚውም ከባድ መሆኑን እንገነዘባለን ።

ይሁን እንጂ ጭንቀታችን ብዙ ቢሆንም እግዚአብሔር መልካም የምንሰማበትን ዘመን እንደሚያመጣ ተስፋ እናደርጋለን ።

በተለይም ደግሞ እኛ ክርስቲያኖች በወገኖቻችን መጎዳት ብናዝንም በትንሣኤ ሙታን ስለምናምን የምጽናና በመሆኑ የሞቱት ልጆቻችን ዕረፍተ ነፍስ እንዲያገኙ እየጸለይን፤ የመከራው ገፈት ቀማሽ ለሆኑት የአካባቢው ማኅበረሰብእ ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ሁሉም አቅሙ በፈቀደው መጠን እንዲደርስላቸው ስንል አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር አምላክ ለቤተሰቦቻቸውና ለሕዝቡ መጽናናትን ይስጥልን፤ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ዋሽንግተን ዲሲ~ አሜሪካ
© “የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ልዩ ጽሕፈት ቤት”