ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዘዘ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም ባልቻ በቅጽል ስሙ (ልጅ ያሬድ) በቀረበበት ተደራራቢ ክስ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዘዘ።
ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ የፀረ-ሽብርና የሕገ-መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም ባልቻ በቅጽል ስሙ( ልጅ ያሬድ) በተባለ ግለሰብ ላይ ተደራራቢ ክሶችን አቅርቧል። በተለይም በኮምፒዩተር የሚፈጸም ወንጀል ድንጋጌን መተላለፍ፣ የቤተክርስቲያንና የሰዎችን ክብርና መልካም ስም በማጉደፍ፣ ጥላቻ ንግግር ማሰራጨት የሚሉ ነጥቦች ይገኙበታል። ክሱ ከደረሰው በኋላ ተከሳሹ ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄው ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል አዟል።
ይሁንና ተከሳሹ ችሎት በቀረበበት ጊዜ ዐቃቤ ሕግ ለቤተክርስቲያን ክብር፣ ለማህበረሰቡ ስነልቦና፣ እሴትና ባህል ሲባል በክሱ ላይ የቀረቡ ዝርዝር ነጥቦች እንዳይታተም በሚዲያ እንዳይቀርብ እንዲሁም ችሎቱ በዝግ እንዲሆን አቤቱታ አቅርቧል። አቤቱታውን የመረመረው ፍርድ ቤቱም የማህበረሰቡን ክብርና ስነልቦናን ከግምት ውስጥ በማስገባት የክሱ ዝርዝር ጉዳይ በሚዲያ እንዳይሰራጭ ችሎቱ በዝግ እንዲሆን ብይን ሰጥቷል።
© ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬት