“የሕገ ወጥ ቡድኑን የሹመት ይጽደቅልን” ጥያቄን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መቼውንም የማትቀበለው ጥያቄ ነው”።

“የሕገ ወጥ ቡድኑን የሹመት ይጽደቅልን” ጥያቄን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መቼውንም የማትቀበለው ጥያቄ ነው”።

የመንበረ ፓትርያርክ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

በዛሬ ዕለት የተካሔደውን በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና በሕገ ወጥ መንገድ በተሾሙ የቀድሞ አባቶች መካከል የነበረውን ውይይት አስመልክተው መግለጫው የሰጡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ሲሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ከመጋቢት ፮/፳፻፲፭ ዓ/ም ጀምሮ በሕገ ወጥ የተሾሙ ግለሰቦችን አስመልክቶ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ለመቀበል ያከናወነውን ተግባራት አብራርተዋል።

በዚህም ቅዱስ ሲኖደስ በቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ከሕገ ወጥ የተሾሙ ግለሰቦች በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት የይቅርታ መመልከቻ እንዲያስገቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ ያስተላላፈ ቢሆንም በይቅርታ ደብዳቤ አስገብተው ከተመለሱት ከአንዱ ” አባ ” ኃይለ ኢየሱስ ከተባሉት ውጭ ሌሎች ግን በይቅርታ ከመመለሰ ይልቅ ለውይይትና ሕገ ወጥ ድርጊቱም እንዲጸድቅላቸው መጠየቃቸውን ተገልጿል።

የመምሪያው ኃላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ቀጥለው ቤተ ክርስቲያን የይቅርታ ቤት የሰላም ዓደባባይ የንስሓ ሰገነት በመሆኗ ለፍቅር ረጅም ርቀት በመጓዝ ግለሰቦቹ ጋር በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ እንዲሁም በሌሎች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት መወያያቷን አስታውሰዋል። ከዚህም አልፎ ቤተ ክርስቲያን የሀገር ሰላም የኢትዮጵያውያን የደኅንነት ኑሮ በእጅጉ ስለሚያሳስባት በብዙ ርቀት ለይቅርታ በሯን ከፍታ ስትጠባበቅ እንደነበረችም አክለው ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በዛሬው ዕለት ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ የመጡት ሁሉንም እንወክላለን ያሉት 6 ግለሰቦች ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና ከብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ጋር የተወያዩ ሲሆን በውይይቱ ግን የተዘረጋው የቤተ ክርስቲያን የፍቅርና ይቅርታ እጅ በግለሰቦቹ ግን እንደመልካም አልታየም። ከዚህ ይልቅ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ከተደረሱ 10 የስምምነት ነጥቦች መካከል በተራ ቁጥር 6 የሚገኘው ውሳኔ “በሕገ ወጥ መንገድ የተሾሙት “አባቶች” ወደ ቀደመ አገልግሎታቸው ይመለሳሉ” የሚል ቢሆንም ግለሰቦቹ ግን በመርሕ ደረጃ ስምምነቱን እንቀበለዋለን በአፈጻጸም ደረጃ ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ሹመታችንን ያጽድቅልን” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የመምሪያው የሓላፊ ገልጸዋል።

ስለሆነም ይላሉ የመምሪያው ሓላፊ ቤተ ክርስቲያን እስካሁን የሄደችበት የይቅርታ መንገድ እጅግ የሚያስመሰግን ሲሆን ከዚህ በኋላ ሕገ ወጦቹን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን የሚከተለውን ውሳኔ መወሰኗን አስታውቀዋል።
፩.በየትኛውም መንገድ የጋራ ውይይት አይኖርም
፪.ለይቅርታ የሚመጡ ከሆነ በቡድን ተሰባስቦ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ እንዲሆን
፫.የይቅርታ ማመልከቻውን እያንዳንዳቸው ለመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ማስገባት ይኖርባቸዋል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዚህና በሌሎች መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ መጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም (21/07/2015 ) ምልዓተ ጉባኤ መጠራቱ የሚታወስ ነው።©Eotc tv