የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዛሬ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር አካሄደ።
===========================
በመረሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የባሕርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ኀላፊ ፣ ከ15 በላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳስት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኀላፊዎች፣ሠራተኞች፣ የአዲስአበባ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ የአዲስአበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ የአዲስአበባ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች ፣ የኢትዮጵያ አባት አርበኞች ማኅበር አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኘበት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የእንኳን አደረሰዎ መርሐግብር ተካሂዷል ።

ቅዱስነታቸው መርሐግብሩን በጸሎት የከፈቱ ሲሆን የእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካህናት ጸሎተ ወንጌል አድርሰዋል። ለመርሐግብሩ መክፈቻ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ደቀመዛሙርት እና ሊቃውንት ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል። በመቀጠልም የአዲስአበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ተወካዮች የእንኳን አደረሰዎ መልእክታቸውን ሲያስተላለፉ “አሮጌውን ሰው ተውትና አዲሱን ሰው ልበሱት” የሚል ሐይለ ቃል አንስተው እግዚአብሔር ዘመንን ሲለውጥ ከነበርንበት አሮጌ ማንነት አንስቶ በአዲስ መነሳሳት እንድኖር በማሰብ ነው ብለዋል።

መልእክቱን ያስተላለፉት አባቶች ከላይ የተነሱበትን ርዕስ ሲያብራሩ “አሮጌውን” የሚለውን ሐሳብ የተጠቀምነው በ2016ዓ.ም. የተሾመው ዮሐንስ አልፎ ማቴዎስ መተካቱን ለማጠየቅ፣ በጉምና በደመና እንዲሁም ጭጋግ የነበረውን የክረምቱን ወራት አልፈን ምድር በአበባ የምታጌጥበትን ወቅት ልናገኝ መሆኑን ለማጠየቅ እና ያሳለፍነው ዘመን የቤተክርስቲያን መቃጠል ፣የምዕመናን መታረድ የነበረበት መሆኑ በመረዳት አዲሱ ዓመት ይህ ሁሉ እንዲቆም ተስፋ የምናደርግበት በመሆኑ ነው ብለዋል ። ከዚህ ጋር አያይዘውም ቅዱስነታቸው በዓመቱ ያደረጉትን ከ10 በላይ ሐዋርያዊ ሥራ በመጥቀስ በእያንዳንዱ ሥራቸው ላይ የሚሰጡት መመሪያ ለአድባራትና ገዳማት ትልቅ መነሳስት መፍጠሩ ተናግርዋል። የቅዱስነታቸው ጸሎትና ቡራኬን በመማጸን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

ከዚህ በኋላ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በኩል መዝሙር እየሰለጠኑ ያሉ ማዕከላዊ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና የጋሞኛ ዘማሪዎች ወቅቱን አመላክተው ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል። በቀጠል በአራቱ ወንጌላውያን ልክ አራት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅኔ እንዲቀርቡ ተደርጓል። ከሊቃውንቱ ቅኔ በኋላ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሐም የመንበረ ፓትርያርክ ሠራተኞችንና የባርሕዳር ሀገረ ስብከት እንዲሁም የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሠራተኞች ስም የእንኳን አደረሰዎ መልእክት ሲያስተላልፉ ከተለያዩ የውጪ ሀገራት መጥተው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተጠምቀው የሥላሴ ልጅነት ያገኙ ምዕመናን በማስተዋወቅ ጀምረዋል።

በመቀጠልም “አቤቱ ወደ አንተ መልሰን እኛም ወደ አንተ እንመለሳለን ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ” የሚለውን ቃል በማንሳት ዘመነ ማቴዎስ በቀድሞው ዘመን አባቶቻችን ይኖሩበት የነበረውን ህይወት እንዲሰጠን ልንጸልይ ይገባል ብለዋል ። አባቶቻችን እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ይሠሩ እንደነበር ሁሉ እኛም በአዲሱ ዘመን በመከባበር ልናገለግል እንደሚገባ አስረድተዋል። የጥፋት ዘመን አልፎ ለአንድነትና ለሰላም የምንቆምበት ሊሆን ይገባል ሲሉ አብራርተዋል። ብፁዕነታቸው ቀጥለው ነገር ግን ተቆጥተኸናል የሚል ቃል አለ ይህንንም ማሰቡ መልካም ነው ። አሁንም እኛን አልተቆጣንም ልንል አንችልም ። የቁጣው ምክንያት ደግሞ ራስ ወዳድነትና መሰሎች ናቸው ብለዋል። በመሆኑም በአዲሱ ዘመን በአንድ ቅዱስ ፓትርያርክ በአንድ ቅዱስ ሲኖደስ እንደቀድሞው ልንኖር ይገባል የሚል ማሳሰቢያና መመሪያ ከሰጡ በኋላ አዲሱ ዘመን የሰላም የፍቅር፣ የአንድነትና የመተሳሰብ እንዲሆንል በመመኘትና በድጋሚ ቅዱስነታቸውን እንኳን አደሰዎ በማለት ሐሳባቸውን አጠናቀዋል።

ከብፁዕነታቸው በመቀጠል የመንበረ ፓትርያርክ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ክቡር መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ (ዶ/ር) የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ለቅዱስነታቸው ፣ ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና ለብፁዕ የሲኖዶስ ጸሐፊ የተዘጋጀውን ሽልማት እንዲሰጥ አድርገዋል። ሠራተኞቹ ይህን ሽልማት ያዘጋጁበት ምክንያት ቤተክርስቲያን ባለችበት የፈተና ወቅት ለማሳለፍ የሚያደርጉትን ጥረት እወቅና ለመስጠትና የኑሮ ውድነቱን ታሳቢ በማድረግ የደመወዝ ማሻሻያ በመደረጉ ምክንያት ምስጋናን ለመግለጽ ነው ተብሏል።

የመርሐ ግብሩ የመገባደጃ ፕሮግራም ላይ ከእንግሊዝ ፣ ከጃማይካ ፣ እና ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት መጥተው የሥላሴን ልጅነት ያገኙ ምዕመናን ከቅዱስነታቸው ቡራኬ ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔርን በዝማሬ አመስግነዋል። የመርሐግብሩ ፍጻሜ ላይ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ያለፈው ዘመን የሰቆቃ፣ የጦርነት እና የተላያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች የደረሱበት ዘመን ነበር ። ነገር ግን አዲሱ ዓመት እነዚህን ሁሉ እንዳናይ ትልቅ ተስፋችን ነው ። ባላፉት ችግሮች ትምህርት ወስደን ንስሐ ልንገባ ያስፈልጋል። አብዛኞቹ ችግሮቻችን ሰው ሰራሽና እኛው በራሳችን ያመጣናቸው ናቸው። ስለዚህ በአዲሱ ዓመት ራሳንን በራሳችን ላለ መጉዳት ጥረት ልናደርግ ይገባል ብለዋል ።

እንደሚታወቀው ለአዲስ ዓመት ልብሳችንን አንጽተን በዓሉን እናደምቃለን። ነገር ግን ልባችን ሳይነጻ ልብስ ብንለብስ ምን ይጠቅማል? የሆነው ሆኖ ጠለቅ ብለን ምንድነው የሆነው ብለን ልናስብ ይገባል። ይህም እንዲስተካከል ሁላችንም እናስብበት። ዝንባሌ ከሌለንና በር ሳንከፍትለት በተዘጋ በር እግዚአብሔር እንዲሠራልን ማድረግ ስለማንችል የልባችንን በር ከፍተን እግዚአብሔር እንዲያስተካክለው መፍቀድ አለብን ብለዋል። ዓመተ ምሕረት ላይ ሆነን ዓመተ መዓት አሳልፈናል። እግዚአብሔር ይህንን ተመልክቶ በዘመነ ማቴዎስ ያለፈውን ሁሉ ጥርግርግ አድርጎ ወስዶ የምሕረት ዓመት ያምጣልን በማለት ሐሳባቸውን በመጠቅል ለተሰበሰቡት ሁሉ ቡራኬ በመስጠት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖል።