ኅዳር ፳፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም.
“”””””””””””””””“”””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
==============

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስተዳደር ጉባኤ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጋር ባደረገው ውይይት በሀገረ ስብከቱ በኩል የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተመለከተ በተደረገው የጋራ ውይይት በሀገረ ስብከቱ የሚስተዋሉትን ዋናዋና ችግሮች መቅረፍ ይቻል ዘንድ በጠቅላይ ቤተክህነት በኩል ተለይተው የሚታወቁት ዋናዋና ነጥቦች ለሀገረ ስብከቱ እንዲደርሰው ተደርጎ መፍትሔ እንዲሰጥበት የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ በጉባኤው ወቅት በሰጡት ማጠቃለያ ሀሳብ ላይ በገለጹት መሰረት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስተዳደር ጉባኤ ኅዳር 24ቀን2016ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ሀገረ ስብከቱ በኩል በአፋጣኝ ምላሽ ሊያገኙ ይገባቸዋል ያላቸውን 13 ነጥቦችን በመለየት ለሀገረ ስብከቱ እንዲደርሰውና ከበዛ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለተጠቀሱት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምላሽ እንዲሰጥና የውሳኔውን መፈጸም አለመፈጸም በተመለከተም ተከታትለው የሚያስፈጽሙ ሦስት የመምሪያ ኃላፊዎችን መድቧል።

የጠቅላይ ቤተክህነቱ ዋና ዓላማ ሕግ፣ደንብና መመሪያ ተከብሮ ስራ እንዲሰራ ፣ፍትሕና ርትዕ እንዲነግስ፣
ተጠያቂነትና ግልጽነትን የተከተለ ተቋማዊ አሰራር እንዲሰፍን ለማድረግ እንደሆነ ከመግለጽ ጋር የሚከሉት ዋና ዋና ነጥቦች በሥራ ላይ እንዲውሉ ሲል ልዩነት በሌለው ድምጽ ወስኗል።

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አስመልክቶ በጋራ የውይይት መድረክ ችግሮችን በመለየት በውይይት በመፈተሸ በጋራ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንዲቻል አስቀድሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም በወሰነው መሠረት ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው የጋራ የውይይት መድረክ እንደ ችግር ተለይተው በቀረቡ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ተመሥርቶ በቀረበው የቃለ ጉባኤ ዘገባ ላይ ተወያይቶ ለመወሰን የተደረገ ስብሰባ ነው፡፡
በመሆኑም ጉባኤው  ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ከክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተደረገውን  የጋር የውይይት መድረክ አስመልክቶ ከቃለ ጉባኤ ጸሐፊዎች የቀረበውን የቃለ ጉባኤ ዘገባ በንባብ ካዳመጠ በኋላ የችግሩ መንስዔ ናቸው በማለት የተለዩ ዋና ዋና ነጥቦች፦

1.በሀ/ስብከቱ ረጅም ዘመናት ሲንከባለል የመጣ  የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ የሚታወቅ ቢሆንም በአሁኑም ሰዓት የበለጠ ተባብሶ የቀጠለ መሆኑን፤

2 የመልከም አስተዳደር ችግርሩ መንስዔ የሕጎችና የደንቦች ጥሰት፤በእቅድና በጸደቀ በጀት ላይ ተመስርቶ ያለመሥራት ውጤት መሆኑን፤

3. መተዳደሪያ ደንቡ ተጥሶ በፍላጎት ላይ ያልተመሠረተ ቅጥርና የሠራተኞች መብትን ያላከበረ የዝውውር ምደባ ውጤት መሆኑን፤

4.የሐብትና የገንዘብ ቁጥጥር ሥራው ደካማ መሆኑ፤

5.ከበላይ መስሪያ ቤት ጋር ተናቦ ያለመሥራትና መሰል ችግሮች ያስከተለው ውጤት መሆኑን ከጋራ ስብሰባውና ከዘገባ ሪፖርቱ ለአስተዳደር ጉባኤው ግንዛቤ በመውሰድና በውይይት የተለዩትን ዋና ዋና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አስመልክቶ የሀስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በማጠቃለያ በሰጡት ሐሳብ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮቹ ተለይተውና ተቆጥረው ይሰጡን ለመፍታት ዝግጁ ነን በማለት በገቡት ቃል መሠረት አስተዳደር ጉባኤው በችግሮቹ ላይ በሰፊው ተወያይቶ የሚከተለውን ውሳኔ ወስኗል፡፡

ው ሳ ኔ
አስተዳደር ጉባኤው ከፍ ብሎ በጋራ የውይይት መድረኩ በዝርዝር የተቀመጡትን ዋና ዋና የችግር መንስኤዎችን በመለየት በሀ/ስብከቱ የተሸለ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት መልካም አስተዳደር ማስፈን ይቻል ዘንድ ፡-

1.በሀ/ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ  ንኡስ ቁጥር   የህግ ድንጋጌ መሠረት ሀ/ስብከቱ ዓመታዊ እቅዱንና በጀቱን አጥንቶና በጉባኤ ወስኖ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አቅርቦ በማጸደቅ ተግባራዊ ያደርጋል በሚል የተደነገገ ቢሆንም እስከአሁን ድረስ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ቀርቦ የጸደቀ በጀት ባለመኖሩ ሀ/ስብከቱ ዓመታዊ ዕቅዱንና በጀቱን በአስቸኳይ በጉባኤ ወስኖ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አቅርቦ በማጸደቅ ተግባራዊ እንዲያደር፤

2.ሀ/ስብከቱ የሰው ኃይል እጥረት ሳይሆን ያለውን የሰው ኃይል ከሥራው ጋር በማጣጣም ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት የማሠራት ችግር መሆኑን ጉባኤው ተረድቷል በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም ቋሚ ሲኖዶስ ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም.  ፣ መስከረም 27 ቀን 2015 ዓ.ም እና ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በወሰነው መሠረት ለሥራው ሲባል መተዳደሪያ ደንቡ ተጠብቆ ከሚደረግ የውስጥ ዝውውርና ሽግሽግ በስተቀር  ይህ ውሳኔ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ምንም ዓይነት ቅጥር እንዳይፈጸም፤

3.ሽልማትና ልዩ ልዩ ስጦታዎችን በተመለከተ አንድ ሰው ሊሸለም የሚችለው ዕለት ተዕለት እንዲያከናውን ከተሰጠው የሥራ ተልዕኮ በላይ ለተቋሙ እድገትና ለተሻለ አሠራር በእራሱ ተነሳሽነት ላከናወናቸው ተጨማሪ የሥራ  አፈጻጸም የተለየ ብልጫ እንዳስመዘገበ ሲታመን ለበለጠ ሥራ ለማነሳሳትና ለሌሎቹ ምሳሌ መሆኑ የታመነ ነው፤ ነገር ግን እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ከሀ/ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ድረስ እየተፈጸመ ያለው ሽልማት ግን ለብዙ ትችትና የሐብት ብክነት የተጋለጠ በመሆኑ ሽልማት መስጠት አስፈላጊነቱ ሲታመንበት የሥራ አፈጻጸምንና የአገልግሎት ትጋትን መሠረት አድርጎ እንዲከናወን እንዲደረግና ከነዚህ መመዘኛ መሥፈርት ውጪ ያሉ ሽልማቶች እንዲቆም፤

4. የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እስከአሁን ሲያደርገው እንደቆየው ሁሉ ሒሳቡን በውጭ ኦዲተር ለማስመርመር በያዘው እቅድ መሠረት ኦዲተሮችን አወዳድሮ  ሥራውን ለማስጀመር ዝግጅቱን ያጠቃለለ ሲሆን  ሀ/ስብከቱም በአስቸኳይ እስከ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ድረስ የሚገኙትን ሒሳቦች በገለልተኛ የውጭ ኦዲተር አስመርምሮ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያቀርብ፤

5. በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ደረጃ ለፐርሰንት መሰብሰቢያ በሚል የተከፈቱ የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች እስከ አሁን ድረስ በሀ/ስብከቱና በክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ጣምራ ፊርማ ሲንቀሳቀስ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ከሁለቱ ፈራሚዎች በተጨማሪ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተጨምረው በሦስት ጣምራ ፊርማ ብቻ እንዲንቀሳቀስና ከፐርሰንቱ የሚገኘው የባንክ ወለድም  ተጠቃሎ ወደ ሀ/ስብከቱ የባንክ ሒሳብ ፈሰስ እንዲደረግ፤

6. ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጀምሮ እስከ ሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ድረስ መስተንግዶ በሚል ሽፋን ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ብክነት እየደረሰ እንደሚገኝ ጉባኤው በጋራ ውይይቱ ከተነሱ ሐሳቦች ተገንዝቧል፤ ስለሆነም አስቀድሞ በእቅድ ላይ  ተመሥርቶ ከጸደቀ የእህል ውሃ መስተንግዶ በጀት ውጭ ምንም ዓይነት የመስተንግዶ ወጪ እንዳይደረግ፤

7. ሀ/ስብከቱ ለሐብትና ንብረት ቁጥጥር በሚል በወራዊ እና ዓመታዊ ክብረ በዓላት በተቆጣጣሪነት ወደ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚልካቸው ልኡካን የገንዘብ እና የንብረት ገቢን አስመልክቶ አጠቃላይ ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ ያለባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚላኩትም ልኡካን ምደባ እውቀትን፣ የሥራ ልምድንና ታማኝነትን መሠረት ያደረገ እንዲሆንና የሚከፈለውም አበል ከአጥቢያ እስከ ሀ/ስብከት ድረስ በቋሚ ሲኖዶስ በተወሰነው የአበል አከፋፈል መሠረት ብቻ ተፈጻሚ እንዲሆን፤

8. እስከ አሁን ድረስ ለዓመታዊ የሒሳብ ምርመራ የሚላኩ ልኡካን የሒሳብ እውቀት የሌላቸውን ሁሉ በጅምላ በመመደብ የሚፈጸመው ዓመታዊ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሒሳብ ምርመራና የኦዲት ሥራ አግባብነት የሌለውና በርካታ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ በጋራ ውይይቱ ስለተረጋገጠ ሀ/ስብከቱ የሒሳብ ሙያና ልምድ ባላቸው የጽ/ቤቱ ሠራተኞች የኦዲትና ቁጥጥር ሥራውን እንዲያከናውን ሆኖ የሒሳብ ባለሙያ እጥረት ካጋጠመው ከዋናው መሥሪያ ቤት የቁጥጥር መመሪያ አገልግሎት ከሚገኙ ኦዲተሮች ጋር በጣምራ ዓመታዊ የኦዲት ሥራው እንዲያከናውን፤

9. በጋራ የውይይት መድረኩ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ የሥራ በደል ደርሶባቸው አለአግባብ ከሥራ የታገዱ፣ በወቅታዊ ችግር ከሥራ የተፈናቀሉ የትግራይና ሌሎች አካባቢዎች ተወላጅ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ፣ ያለ ሥራ የተንሳፈፉና በሕገወጥ መንገድ ከደረጃ ዝቅ ያሉ እንዲሁም በአጥቢያ ደረጃ የተከሰቱ የሰበካ ጉባኤ ምርጫና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች በሙሉ ተጠቃለው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተፈተውና ምላሽ አግኝተው ለዋናው መሥሪ ቤት ሪፖርት እንዲቀርብ፤

10.ከሀ/ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ እስከ የበላይ ሕግ የሆነው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ጥብቅ አስተዳዳሪ የሚል የሥራ መደብ በሌለበት ሁኔታ ሀ/ስብከቱ በእራሱ ፍላጎት ስያሜውን ፈጥሮ በርካታ አስተዳዳሪዎች ያለ ሥራ መደብ ተንሳፈው እያለ ከአሥራ ሁለት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ጥብቅ በሚል አስተዳዳሪ እየተመሩ መሆናቸውን በመረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለሆነም በቀጣይ ከመዋቅር ውጭ በሆነ ስያሜ በየትኛውም አብያተ ክርስቲያናት ጥብቅ አስተዳዳሪ እንዳይመደብ እንዲደረግና አሁን በጥብቅ አስተዳደር በሚል ክፍት በሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ላይ መተዳደሪያ ደንቡ ተጠብቆ ያለ ሥራ የተንሳፈፉና በአቤቱታ ላይ የሚገኙት አስተዳዳሪዎች ምደባ ተጠንቶ እንዲቀርብ፡፡

11. ለሀ/ስብከቱ መልካም አስተዳደር ችግር እንደ ዋና መንስኤ የሆኑት በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት እና በአጥቢያ ደረጃ የሚፈጸሙ ቅጥር፣ ዝውውርና እግድ በሙሉ እንዲቆም፤

12. ከክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት እስከ ሀ/ስብከት በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ የሥራ ኃላፊዎች ለሀ/ስብከቱ መተዳዳሪያ ደንብ ተፈጻሚነትና ስለ መልካም አስተዳደር ችግሮች አፈታት እስከታች አስፈጻሚ አካል ደረስ ግንዛቤ ይፈጠርልን በማለት በአጽንኦት ባሳሰቡት መሠረት ከሀ/ስብከት አስከ አጥቢያ ድረስ ላሉት የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋችና የቢሮ ሰራተኞች እንዲሁም ለሰበካ ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በቀጣይ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በኩል በአጭር ጊዜ ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅ፤

13. የሀ/ስብከቱ ማኅበራዊ ሚዲያ የተቋቋመበት መሠረታዊ ዓላማ ከሀ/ስብከት እስከ አጥቢያ ያሉትን የዕለት ተዕለት ሐዋርያዊና አስተዳደራዊ ክንውኖችን ለምዕመናን ተደራሽ ለማድረግ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፤ ይሁን እንጂ  ማኅበራዊ ሚድያው ከቋቋመበት ዓላማ ውጪ የሀ/ስብከቱን የመልካም አስተዳደር ችግር በጋራ ውይይት ለመፍታት የተደረገውን የምክክር መድረክ በተሳሳተ መድረክ በመዘገብ የተዛባ መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ በማድረግ የፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ጉባኤውን በእጅጉ ያሳዘነ አድራጎት ሲሆን ዋናው መሥሪያ ቤት ባደረገው ማጣራትም በድረገጹ ላይ የማይመለከታቸው ግለሰቦች ጭምር የራሳቸውን ፍላጎት የሚለጥፉበት አጋጣሚዎችም እንዳሉ መረጃዎች ቀርበዋል፡፡ ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱ ሕገ ወጥ አድራጎት እንዳይደገም ሆኖ በቀጣይ ከሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊውና ከሚመለከታቸው የክፍሉ ሠራተኞች በስተቀር የትኛውም አካል የራሱን ፍላጎትና የተዛባ መረጃ እንዳይለጥፍ በሀ/ስብከቱ በኩል ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግ ሲል ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ወስኖ የዕለቱን ስብሰባ በብፁዕ አባታችን ጸሎትና ቡራኬ አጠናቋል፡፡

ትእዛዝ
1ኛ. የአስተዳደር ጉባኤው የውሳኔ ቃለ ጉባኤ በመሸኛ ደብዳቤ ለሀ/ስብከቱ ይላክ፤
2ኛ. የቅሬታ አቅራቢ ባለጉዳዮች ስም ዝርዝር ከመሸኛ ደብዳቤ ጋር ለሀ/ስብከቱ ይላክ፤
3ኛ. ይህ ውሳኔ በአግባቡ ስለመፈጸሙና አለመፈጸሙ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ምምሪያ ፤የሕግ አገልግሎት መምሪያና የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ እየተከታተሉ ሪፖርት እንዲያደርጉ፤