ኅዳር8/2016 ዓ.ም
አዳማ – ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ 42ኛው የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ጸሎተ ቡራኬ ፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ልዑካን ፡ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፡ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች ፡ የየወረዳ ቤተ ክህነቱ ሊቃነ ካህናትና ሠራተኞች ፡ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፡ የጽ/ቤት ሠራተኞች ፡ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተወካዮች፡ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የመክፈቻ አባታዊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ” ሥራችን ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ብቻ ነው ሌላ ተልዕኮ የለንም ይኼ ጠቅላላ ጉባኤ ጠንካራ ጎን ብቻ በማንሳት ሳይሆን ደካማ ጎናችንን ነቅሰን በማውጣት ኃላፊነት በተሞላ መንገድ ለመፍትሔ ልንረባረብ ይገባል በጎና እግዚአብሔርና ምዕመናን የሚደሰቱበትን መንፈሳዊ አገልግሎት ማሳካት የሚቻለው ደግም በአንድነትና በፍቅር ነው ያሉ ሲሆን ጉባኤው ከጠንካራ መንፈሳዊ ሥራዎች ባሻገር ከሀገረ ስብከት – አጥቢያ ያሉ ክፍተቶች ላይ ትኩረት በማድረግ መወያየት እንዲችል አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ጉባኤው በጠዋቱ መርሐግብሩ የሀገረ ስብከቱን የ2015 ዓ.ም አጠቃላይ ሪፖርት ፡ የ12ቱንም ወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ ሪፖርት ጉባኤው እያደመጠ ይገኛል፡፡ሲል ሐመረ ተዋሕዶ ሚዲያ ባደረሰን ዘገባ ገልጿል።