የምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከት የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ከአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሥራ መመሪያ ተቀበሉ።

ሰኔ ፯ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም አዲስ አበባ

ከዓመት በላይ ያለ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ሥራቸውን ለመከወን ፈተና ውስጥ የቆዩት የምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከት የአስተዳደር ጉባኤ አባላት በግንቦት ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአባትነት ከተመደበላቸው ከብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ጋር በመገናኘት እና ገንቢ ውይይት በማድረግ የሥራ መመሪያ ተቀበሉ።
የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱ ከብፁዕነታቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ያለ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ በቆዩባቸው ጊዜያት የሀገረ ስብከቱን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማሳለጥ ባለመቻላቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ መቆየታቸውንና ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ችግራቸውን ተመልክቶ አህጉረ ስብከቱን በፍጹም መንፈሳዊ የአባትነት መንፈስ ሊመሩ ሙሉ ፈቃደኝነቱ ያላቸውን ብፁዕ አቡነ ሩፋኤልን በመመደቡ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱ ከብፁዕነታቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ተዘግቶ የቆየውን የአህጉረ ስብከቱን የባንክ አካውንት በማስከፈት በውዝፍነት የቆየ የአገልጋዮችን ደመወዝ ለመክፈል ሥራ ከመጀመር ባለፈ በጅምር የቆሙ የልማትና የአስተዳደር ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ዝግጁነታቸውን አሳይተዋል።
ብፁዕነታቸው ለአስተዳደር ጉባኤ አባላቱ በሰጡት አባታዊ መመሪያም ጠንክረው በመሥራት ቤተ ክርስቲያናችን በዞኖቹ ያላትን በጎ ስም አስጠብቀው ለትውልድ እንዲያስተላልፉ አሳውቀዋል።