“ጠቡ መለያየቱ መጨካከኑ ለኔ ለኔ መባባሉ ከረምንበት፤ ሆኖም ያመጣልን ነገር ቢኖር ሁለንተናዊ ውድመት ብቻ ነው”
“ዓለም የጉልበተኞችና የባለ ሀብቶች ብቻ እንድትሆን የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ከባድ የፍትሕ መዛባት አጋጥሞአታል”
“በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በተከሠተው የድርቅና የሰው ሰራሽ ምክንያት በችግር ላይ የወደቁ ወገኖች በርካታ ናቸው። ”
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
• በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፡-
በፍጹም ፍቅሩ እኛን ወደ ሰላም ለማምጣት በእኛ ሰውነት በዚህ ዓለም የተወለደው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በደኅና አደረሳችሁ!
“ትእምርተ ሰላምነ ወልድ ተወልደ ለነ የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነው ወልድ ወይም ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ተወለደልን” (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)
ዓለም ሁሉ በተለይም የክርስቲያኑ ዓለም በትክክል እንደሚያውቀው ቅዱስ መጽሐፍ በሰዎች የቋንቋ ዘይቤ የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ ርእዮት ቋንቋ የመልእክት ማስተላለፊያና መግባቢያ መሳሪያ እንደሆነ ይታወቃል እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ መልእክቱን በዚህ መንገድ ለሰዎች ሲያስተላልፍ ኖሮአል የሚያስተላልፈውም መልእክት እንዲሁ ተሰምቶ እንዲቀር ሳይሆን እንዲታወቅ፣ እንዲታመን፣ እንዲተገበርና ሰዎች እንዲጠቀሙበት ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ጌታችን የተዋሐደው ሰውነት የወዳጁ አልነበረም የጠላቱ እንጂ፤ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልፅ “ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን” ይላልና ነውከሚፈለገው ጥቅም ለመድረስም ሰዎች መልእክቱን በሚገባ መረዳት የግድ ይሆናል ሰዎች እንዲረዱት ደግሞ በቋንቋቸውና በባህላቸው ዘይቤ ሊነገራቸው ይገባል።
በመሆኑም እግዚአብሔር ቃሉን በሰዎች ቋንቋ ባህላዊ ዘይቤ መልእክቱን ለዓለም ሲያስተላልፍ ኖሮአል፤ ቤተክርስቲያንም ይህንን መሠረት አድርጋ የእግዚአብሔርን ቃል በሰው ቋንቋ ዘይቤ ታስተምራለች፤ ከዚህ አንጻር በሰው ልማዳዊ የዘይቤ ቋንቋ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “የሰላም ሰንደቅ ዓላማ” የሚል ቅፅል ተሰጥቶታል፤ ምክንያቱም ንጉሥም ወታደርም ተራው ሕዝብም የሀገሩ ነጻነትና ክብር፣ አንድነትና ሉዓላዊነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ተከትሎ ስራ ይሰራል ክብሩንም ይገልፃልና ነው።ተከተል አለቃህን ተመልከት ዓላማህን የሚለው ብሂልም ይህንን ያንፀባርቃል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
ምእመናንና ምእመናት!
ጌታችን በመድኅንነቱ የሁላችን የሰላም ሰንደቅ ዓላማ በመሆኑ መምህራችን ቅዱስ ያሬድ “የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነ ልጅ ተወለደልን” ብሎ ይገልፀዋል፤ጌታችን በዛሬው ዕለት በቤተ ልሔም ሰውነታችንን ሰውነት አድርጎ መወለዱ ራሱ የሰላም ማሳያ ምልክት ነው።ምክንያቱም ሳይወደን አይቀርበንም፤አይዋሐደንምና ነው።በልደቱ ዕለት “ለዕጓለ እመሕያው ሠምሮ የሰው ልጅን ወደደው” ተብሎ በቅዱሳን መላእክት የተዘመረበትም ምክንያት ይኸው ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ጌታችን የተዋሐደው ሰውነት የወዳጁ አልነበረም የጠላቱ እንጂ፤ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልፅ “ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን” ይላልና ነውእንደ እውነቱ ከሆነ ጌታችን የተዋሐደው ሰውነት የወዳጁ አልነበረም የጠላቱ እንጂ፤ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልፅ “ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን” ይላልና ነው።በዚህ ዓለም የኖረውም ከሚያሳድዱት፣ ከሚከሱት፣ ስሙን ከሚያጠፉና ሊገዱሉት ከሚከጅሉ ጋር እንጂ ከወዳጆቹ ጋር ብቻ አልነበረም፤እሱ ግን ሁሉንም በፍቅር ይቀበል ነበረ፣ ይፈውስና ያድን ነበረ፣ ያስተምርም ነበረ፤ለሁሉም ስርየተ ኃጢአትን ሰጠ፤ ለጠላቶቹም ጸለየ፤ ጌታችን በዚህ ሁሉ ለኛ አርአያና የተግባር መምህር በመሆኑ የሰላም ሰንደቅ ዓላማችን ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
ምእመናንና ምእመናት!
ዓለም በጌታችን ዕለተ ልደት የተዘመረውን ሰማያዊውን የሰላም መዝሙር መዘመር ከጀመረች እነሆ ዛሬ ድፍን ሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመት ሆነ፤የሰላሙ መዝሙር ዛሬም በመላው ዓለም በሚገኙ ክርስቲያኖች ይዘመራል፤ይሁን እንጂ በዚህ ዓለም ሰላም ሰፍኖ እየታየ አይደለም፤ ይህ ለምን ሆነ ቢባል ደምበኛ መልስ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔርን አለማመንና አለመፍራት ያመጣው ችግር ነው የሚል ነው።
ምክንያቱም ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚአብሔር ከሌለ ፍትሕ ይጐድላል፣ ፍትሕ ከጐደለ ብሶት ይፈጠራል፣ ብሶት ካለ ሰላም ሊኖር አይችልም፤ በሁሉም የዓለማችን ክፍል ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚብሔር እየተዘነጋ በመሄዱ ቀውሱ ተባብሶ ይታያል፤ የሰው ልጅ ኑሮ በየትም ይሁን በየት በስጋት የተሞላ ሆኖአል፤የሚወራው ሁሉ ስለ ግጭት ስለአየር ብክለት ስለ ረኃብና እልቂት ሆኖአል፤ ዓለም የጉልበተኞችና የባለ ሀብቶች ብቻ እንድትሆን የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ከባድ የፍትሕ መዛባት አጋጥሞአታል፤ የዝቅተኛው ማኅበረ ሰብ ሰብአዊ መብት ተዘንግቶአል፤ከዚህ አኳያ ዓለም በዚህ እስከ ቀጠለች ድረስ ሰላም የማግኘቷ ዕድል በጣም አጠራጣሪ ነው። የክርስቶስ ልደት ያስተማረን ግን እንደዚህ አልነበረም፤ ጌታችን የተወለደው በተዋበና ምቹ በሆነ የሀብታም ቤት ሳይሆን በከብቶች በረት ነበረ፤የተገለጠውም ለባለሥልጣኖች ሳይሆን ዝቅተኞች ለሚባሉ እረኞች ነበረ፤ ልዑላኑ ሰማያውያንና ትሑታኑ ምድራውያን በአንድነት አገናኝቶ ስለ ሰላም በጋራ እንዲዘምሩ አደረገ፤ አሳዳጅ ሳይሆን ተሳዳጅ ሆኖ በግብጽ አገር በመንከራተት አደገ፤ ይህን ሁሉ ያደረገው እኛ እሱን እያየን እንደ ሰንደቅ ዓላማ እንድንከተለው ነበር፤ ጌታችን ከባለሥልጣናቱና ከባለሀብቶቹ ይልቅ በድሆቹ ደረጃ የተወለደው ለድሆቹና ለዝቅተኞቹ ትኩረት እንድንሰጥ ለማስተማር ነው።የእኛ ድርጊት ግን ግልባጩ ሆኖ እየተስተዋለ ነው፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ክርስቲያን ነኝ ብሎ፣ በስመ እግዚአብሔር ተሰይሞ፣ መስቀልን በአንገቱ ተሸክሞ የእሱ መሰል በሆነው ወይም መስቀል በተሸከመው ወንድሙ እና እኅቱ እንዲሁም በመሰል ፍጡር ላይ ያለ ርኅራኄ ሲጨክን መታየቱ ነው፤ እንዲህ እየሆነ እንዴት ሰላም ይምጣ? እግዚአብሔርስ እንዴት በረከቱ ይሰጣል? ይህ እጅግ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
ምእመናንና ምእመናት!
እኛ ኢትዮጵያውያን ከእንዲህ ዓይነቱ የሃይማኖትና የሞራል ዝቅጠት በአስቸኳይ መውጣት አለብን፤ ጠቡ፣ መለያየቱ፣ መጨካከኑ፣ ለኔ ለኔ መባባሉ ከረምንበት፤ ሆኖም ያመጣልን ነገር ቢኖር ሁለንተና ውድመት ብቻ ነው።ያስገኘልን ትርፍ ይህ መሆኑ እያወቅን በዚሁ ልንቀጥል አይገባም፤ሰው ችግሩን በልቡ እያወቀ በዓይኑ እያየ እንዴት ገደል ውስጥ ይገባል? ዕርቅና ይቅርታ ማንን ጐዳ? ሰላምና አንድነት ማንን አከሰረ? ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በሆነውም ባልሆነውም ከመተላለቅ ለምን ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በእኩልነትና በስምምነት መኖር አቃተን? ሦስት ሺሕ ዘመናት አብረው የኖሩ ሕዝቦች እንዴት ችግራቸውን በጠባይና በብልሐት ማስወገድ አቃታቸው? ይህ ከቶ ሊሆን አይገባም፤ ሁላችንም ሰከን ብለን እናስብ፤ ለሁሉም የማሰቢያና የመመካከሪያ ጊዜ ፈጥረን ችግሩን በስፍሐ አእምሮ እንፍታው፤ችግርን በምክክርና በይቅርታ መፍታት አማራጭ የሌለው ጥበብ ነው። የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ልኂቃን በዚህ ተግተን ልንሰራ ይገባል፤ መንግሥትና የፓለቲካ ፓርቲዎችም ለዚህ የበኩላቸውን ድጋፍ ያድርጉ፤ በዚህም ሰላማችንን እንመልስ፡፡
በመጨረሻም
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በተከሠተው የድርቅና የሰው ሰራሽ ምክንያት በችግር ላይ የወደቁ ወገኖች በርካታ ናቸው። በመሆኑም የወገን ደራሽ ወገን ነውና ሁሉም ካለው ብቻ ሳይሆን የቀን ቊርሱን ለተቸገሩ ወገኖች እንዲለግስና በመተጋገዝ ረኃቡን እንድንከላከለው ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የልደት በዓል ያድርግልን!!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ታኅሣሥ ፳፰ቀን ፲ወ፮ ዓ.ም.
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ