ታኅሣሥ ፲፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም

በሸገር ማረሚያ ቤት የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ማረሚያ ቤቱ ለአምልኮ ቦታ በሚል በሰጣቸው ቦታ ላይ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በማስተባበር ልዩ ስሙ ዳለቲ በተባለ ቦታ የማርያም ቤተክርስቲያንን በማነጽ ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ በማረሚያ ቤት የሚገኙ የሕግ ታራሚዎችን ለማጽናናትና ለማስተማር በያዘው ዕቅድ መሰረት ታኅሣሥ ፲፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም በማረሚያ ቤቱ በመገኘት የማጽናኛ ትምህርት በመስጠት የታራሚዎችን የልማት ሥራ ጎብኝቷል።

የመምሪያው የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣የመምሪያው ዋና ኃላፊ መ/ሰ ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ( ዶ/ር) ማረሚያ ቤቱን በጎበኙበት ወቅት በሕግ ታራሚዎቹ እየታነጸ የሚገኘውን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተዛውረው ከተመለከቱ በኋላ በሕግ ታራሚዎቹ እየተሰራ ያለውን መልካም ሥራ በማድነቅ በመምሪያው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንደሚደረግላቸው ቃል ገብተዋል።

በዚሁ ጊዜም ትምህርተ ወንጌል በመምሪያ ኃላፊው የተሰጠ ሲሆን ቀመምሪያው ሊቀ ጳጳስም ቃለ በረከትና ቡራኬ ተሰጥቷል።የጉብኝቱ ዓላማም ስብከተ ወንጌልን በማረሚያ ቤቶች ጭምር ለማዳረስ ነው።

የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ኢኒስፔክተር ቀበና ለሕግ ታራሚዎቹ የአምልኮ ቦታ የተሰጠው ታራሚዎቹ ከቤተክርስቲያን በሚያገኙት የወንጌል አገልግሎት በስነምግባር የበለጠ የሚታነጹበት አእድል እንደሚፈጠር ተቋማቸው ስለሚያምን መሆኑን ገልጸው ይህ ቤተክርስቲያን እንዲታነጽ መቀቀዱንና በፍጥነት ቤተክርስቲያኑ ታንጾ አገልግሎት መስጠት ይችል ዘንድ የሚመለከታቸው ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ በሌሎች ማረሚያ ቤቶችም ተመሳሳይ ጉብኝት እኔደሚያደርግና የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱንም በተጠናከረ መልኩ ለመቀጠል ዕቅድ መያዙ የሚታወቅ ሲሆን በሸገር ማረሚያ ቤት በመታነጽ ላይ ለሚገኘው ሕንጻ ቤተክርስቲያንም በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ቃል መገባቱን ከመምሪያው ዋና ኃላፊ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።