ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም
+ + +

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከጥቅምት 24-27 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ሐዋርያዊ ጉዞ አድርገዋል። ብፁዕነታቸው የቅዱስ ላሊበላ ደብር የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የእድር አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በመሪ እቅድ አተገባበር፣ በቅርሱ ጥገናና እንክብካቤ ዙሪያ አወያይተዋል። የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት መጠለያ አለመነሣቱና የቅርሱ ጥገና መዘግየት እንዲሁም በአካባቢው የሚተኮሰው ከባድ መሣሪያ ያስከተለው ንዝረት በቅርሱ ህልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ተሳታፊዎች አንሥተዋል።

የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ አስተዳዳሪ መ/ር አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ (ቆሞስ) በበኩላቸው አካባቢው የጦርነት ቀጠና ቢሆንም ቤተክርስቲያኗ በመንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የአስተዳደር ዘርፎች ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት እንድታስፋፋ ታልሞ የተዘጋጀውን መሪ እቅድ ለማሳካት ደብሩ የአስተዳደር ደንብና መዋቅር እያጠና መሆኑን አብራርተዋል። በደብሩ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠትና መዋቅራዊ አደረጃጀቱን ለማሻሻል የሚያግዝ የአስተዳደር ደንብ በባለሞያዎች እየተዘጋጀ ስለመሆኑም አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት የማጠቃለያ አባታዊ መልእክት በፈተናዎች ውስጥ ብንሆንም እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ የተዘጋጀውን የሀገረ ስብከት ሥልታዊ እቅድ እስከ አጥቢያ ድረስ ማውረድ ተችሏል ብለዋል። በዘርፉ ከፍተኛ ዕውቀትና ልምድ ባላቸው ምሁራን የተዘጋጀውን የ10 ዓመት መሪ እቅድ ተገንዝበን መተግበር ከቻልን ኹሉም ጥያቄዎቻችን መልስ ያገኛሉ ብለዋል ።

በቅዱስ ላሊበላ ቅርስ ደኅንነት፣ በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መንግሥት ስምምነት የተጀመረው የዘላቂ ላሊበላ ቅርስ ጥገና ፕሮጀክት መዘግየት፣ በመዳረሻ ልማትና ማስተዋወቅ ዙሪያ ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ባለፈው ሳምንት ውይይት በማድረግ የመፍትሔ አቅጣጫ መቀመጡንም ብፁዕነታቸው ተናግረዋል። ብፁዕነታቸው ለሦስት ቀናት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት፣ በማስተማርና አባታዊ መመሪያ በማስተላለፍ በቅዱስ ላሊበላ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ አጠናቀው ወደ መንበረ ጵጵስናቸው በሰላም ተመልሰዋል።

የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው