በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ላይ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻውን ሥርዓተ ጸሎት ከፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ ሰንብቷል፡፡
በመሆኑም ምልዓተ ጉባኤው ስለ ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ እየተከሰቱ ስላሉት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች እንዲሁም ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት በስፋት በመወያየት ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
1. የ2016 ዓ.ም. የመንበረ ፓትርያርክ ዓለም አቀፍ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ያሳለፈውን የጋራ የአቋም መግለጫ በመመርመርና አስፈላጊውን ማሻሻያዎች በማድረግ የበጀት ዓመቱ የቤተ ክርስቲያናችን የሥራ መመሪያ እንዲሆን ጉባኤው አጽድቆታል፡፡
2. ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መዋቅራዊ አደረጃጀቱን የበለጠ ተደራሽ በማድረግ ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን መወጣት ትችል ዘንድ በአዲስ እንዲደራጁ ተጠንተው የቀረቡትን የአህጉረ ስብከት ይደራጅልን ጥያቄዎችን በመመርመር፡-
ሀ. የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት፣
ለ. የሰሜን ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት
ሐ. የጎፋና ባስኬቶ ዞን ሀገረ ስብከት
መ. የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ሀገረ ስብከት እራሳቸውን ችለው ሀገረ ስብከት ሆነው ተደራጅተው እንዲቀጥሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
3. ቤተ ክርስቲያናችን የመንፈሳዊ ኮሌጆቿን ቁጥር ከፍ በማድረግ የአገልጋይ መምህራንን ቁጥር ለማሳደግ ባላት እቅድ መሠረት ተጠንተው ከቀረቡት መካከል በ2016 ዓ.ም. የበጀት ዓመት በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ፣ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ደብረ ታቦር ከተማ ላይ ሁለት መንፈሳዊ ኮሌጆች እንዲቋቋሙ፣ በማዕከላዊ ጐንደር ሀገረ ስብከት ርእሰ ከተማ ውስጥ ለሚገኙት የምስክር ጉባኤ ቤቶች በኮሌጅ ደረጃ በጀት እንዲመደብላቸው እና በከንባታ ሐድያ ስልጤ ሀገረ ስብከት ሆሣዕና ከተማ ላይ አንድ የካህናት ማሠልጠኛ እንዲከፈት ጉባኤው ወስኗል፡፡
4. ቤተ ክርስቲያናችን ከውስጥና ከውጭ እየደረሱባት ያሉት ከፍተኛ የሆኑ ፈተናዎችን ተቋቁማ ሕልውናዋን አስከብራ መቀጠል ትችል ዘንድ ፡-
ሀ. ውስጣዊ ችግሮቻችን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በጠበቀ በውይይት እንዲፈቱ፣
ለ. ውጫዊ ችግሮችንና የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ በችግሮቹ ዙሪያ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመነጋገር ችግሮቹ እንዲፈቱ እና የቤተ ክርስቲያናችን መብትና ሕልውና ተጠብቆ እንዲቀጥል እንዲደረግ፣
ሐ. ለቤተ ክርስቲያናችን ሕልውና አደጋ የሆኑና ሊሆኑ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን አስመልክቶ በአግባቡ ተጠንተውናበማስረጃ ተተንትነው ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
5. ትላንት በሰሜኑ ኢትዮጵያ የሀገራችን ክፍል በተካሄደው ጦርነት በጠፋው የሰው ሕይወትና በወደመው ንብረት ከደረሰብን ሐዘን እኛ ኢትዮጵያውያን ገና ሳንጽናና ዛሬም በሀገራችን ኢትዮጵያ በበርካታ አካባቢዎች የተከሰቱት ጦርነቶች፣ ግጭቶችና አለመግባባቶች እያስከተሉት ያለው የንጹሐን የሰው ሕይወት መጥፍትና የንብረት ውድመት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን በእጅጉ አሳዝኖታል፡፡ በመሆኑም ችግሩ በውይይትና በስምምነት እንዲፈታ የፌዴራልን የክልል መንግሥታት፣ እንዲሁም በግጭቱ ተሳትፎና ድርሻ ያላችሁ በሁሉም አካባቢ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሙሉ የበኩላችሁን ሚና በመወጣት እናት አገራችን ኢትዮጵያ ሰላሟና አንድነቷ ተጠብቆ ይቀጥል ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአደራ ጭምር በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
6. በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየተከሠተ ያለው ችግርና ፈተና የሚወገደው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነትና በሕብረት ለችግሮቹ መፈታት ድርሻ እንዳለን አውቀን እንደየእምነታችን አስተምህሮ በጸሎትና በምሕላ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር በንስሓ መመለስ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያምናል፡፡ በመሆኑም ስለ ሀገራችን ሰላምና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት በመላው ዓለም በሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ከህዳር 15 ቀን 2016 እስከ ታህሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ጸሎትና ምሕላ እንዲፈጸምና መላው ሕዝበ ክርስቲያንም በአንድነትን በሕብረት ከላይ በተጠቀሱት ዕለታት በቤተ ክርስቲያን በመገኘት የበረከቱና የሥርዓተ ጸሎቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
7. የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክና ለሀገረ መንግስት ምሥረታና እድገት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በማዕከል ደረጃ በማስረጃ አስደግፎ በመጻፍና በማደራጀት ትውልዱ እንዲረዳው በማድረግ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሕልውና አደጋ የሆነውን የሐሰት ትርክት መከላከል ይቻል ዘንድ የዝግጅት ሥራው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል በሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ተቆጣጣሪነት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንና የታሪክ ተመራማሪዎችን በማሳተፍ ተግባራዊ እንዲሆን ጉባኤው ወስኗል፡፡
8. ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ላይ ስለሚኖራት ተሳትፎና ሚና በተመለከተ ጉባኤው በስፋት የተወያየ ሲሆን ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ ችግራችንን እንደሚፈታና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚነገሩትን የሐሰት ትርክቶች ሁሉ የሚታረሙበት እንደሚሆን ጉባኤው በጽኑ ያምናል፡፡ በመሆኑም በምክክር ሂደቱ ላይ ስለሚኖረን ተሳትፎና ሚና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል እየተጠና አስፈላጊው ሁሉ እንዲፈጸም ሆኖ የምክክር ኮሚሽኑም ይህን የቤተ ክርስቲያናችን እቅድ በመርሐግብሩ በማካተት ቤተ ክርስቲያናችን የድርሻዋን እንድትወጣ እድሉን እንዲያመቻችልን ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፡፡
9. የመረጃ ቋት መዋቅራዊ አደረጃጀትን በሁሉም ክልል አህጉረ ስብከት ደረጃ በማቋቋም እና እለት እለት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚከሰቱትን ችግሮችና የመብት ጥሰቶች በመረጃና ማስረጃ አስደግፎ ለዋናው ማዕከል የመረጃ ቋት በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ በአንዱ ቦታ ችግር ሲደርስ በመላ ሀገሪቱ እና በውጭው ክፍለ ዓለማት ባሉት አህጉረ ስብከት በአንድነት ድምፅ መሆን ይቻል ዘንድ ተጠሪነታቸው ለዋናው ማዕከል የሆኑ የመረጃ ቋት ማዕከላት በሁሉም አህጉረ ስብከት ተቋቁመው ወደሥራ እንዲገቡ ጉባኤው ወስኗል፡፡
10. የቤተ ክርስቲያናችን ሀብትና ንብረት የሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ የሚዳሰሱና እና የማይዳሰሱ ቅርሶችንና በአጠቃላይ ንዋየ ቅድሳቶቻችን ግለሰቦች እና ተቋማት በሕገወጥ መንገድ አትመውና አሳትመው በማሠራጨትና ትክክለኛ ቅጅውን አዛብቶ በማተም ቤተ ክርስቲያናችን ለሐሰተኛ ትርክት እንድትዳረግ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ በደል እየተፈጸመባት መሆኑን ጉባኤው በጽኑ ያምናል፡፡ በመሆኑም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በኩል የተጀመረው የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና የቤተ ክርስቲያኒቱ መብትና ጥቅም እንዲከበር ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
11. በውጭው ክፍለ ዓለማት በሚገኙት አህጉረ ስብከት ሥር የተቋቋሙት አብያተ ክርስቲያናት የሚተዳደሩበት እራሱን የቻለ ሕግና ደንብ ባለመኖሩ በመዋቅራዊ አስተዳደራችን ላይ ከፍተኛ ክፍተት ሲፈጥር የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ ለውጭው ክፍለ ዓለማት አህጉረ ስብከት እና አብያተ ክርስቲያናት እራሱን የቻለ መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጅቶ የፀደቀ በመሆኑ በውጭው ክፍለ ዓለማት በሚገኙት ሁሉም አህጉረ ስብከትና አብያተ ክርስቲያናት በጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ ብቻ ሥራቸውንና አገልግሎታቸውን እንዲያከናውኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
12. የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ኮሌጆች ወጥ የሆነ የጋራ መተዳደሪያ ደንብ እንዲኖራቸው በማሰብ ጉባኤው አስቀድሞ ተዘጋጅ እንዲቀርብ ባዘዘው መሠረት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ መርምሮ በማጽደቅ በሁሉም በተቋቋሙትም ሆነ ወደፊት በሚቋቋሙት ኮሌጆች ሥራ ላይ እንዲውል ጉባኤው ወስኗል፡፡
13. ገዳማትና ገዳማዊ ሕይወት፣ የአብነት መምህራን እና ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በአጠቃላይ ክብረ ክህነት እና ትምህርተ ኖሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል እየተጠና አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍና ክትትል እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡
14. የቤተ ክርስቲያናችን ሕጋዊ፣ ተቋማዊ፣ ሃይማኖታዊና ማህበራዊ መብቶች መከበርና የእምነት ነጻነታችንን እና የምእመናንን ደኅንነት በሕግ አግባብ ማስከበር ይቻል ዘንድ ልክ እንደ ዋናው መሥሪያ ቤት በሁሉም ክልሎች ውስጥ ባሉት አህጉረ ስብከት የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ ጉባኤው ወስኗል፡፡
15. ወጣቱ ትውልድ በእምነቱ ጸንቶና በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ በእውቀትና በሥነምግባር ይታነጽ ዘንድ በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ተዘጋጅቶ የቀረበው ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር እና አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆን ጉባኤው ወስኗል፡፡
16. የ2016 ዓ.ም. ዓመታዊ በጀትን አስመልክቶ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል ተዘጋጅቶ የቀረበውን የበጀት ድልድል ጉባኤው መርምሮ በማጽደቅ ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
17. የቤተ ክርስቲያናችን የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱት እና የልማት ተቋማት የሚጠናከሩት ዘመኑን የዋጀ መዋቅራዊ አደረጃጀት በመፍጠር እና በእቅድ ተደግፎ በእውቀት ላይ የተመሠረተ የሀብትና የንብረት አስተዳደር ማስፈን ሲችል መሆኑን ጉባኤው በጽኑ ያምናል፡፡
በመሆኑም በባለፈው ጉባኤ የጸደቀው የ10 ዓመት የመሪ እቅድ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገለት የመሪ ዕቅዱ አፈጻጸም እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም.
ኢትዮጵያ አዲስ አበባ