የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ ተጠራ
ሐምሌ ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ እና በአዲስ አበባ አቅራቢያ ያሉ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ለዛሬ ሐምሌ ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም ከቀኑ 10:00 ሰዓት በቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለአስቸኳይ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲገኙ ጥሪውን አስተላልፏል።
የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ከቀትር በፊት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ይህ ጥሪ እንዲተላለፍ ውሳኔውን ያሳለፈው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ባሳለፍነው ሰኞ ወደ ትግራይ ክልል ለእርቀ ሰላም ጉዳይ በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት የተጓዘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልዑካን ቡድን የገጠመውን እክል ከገመገመ በኋላ አሁን ያለው የቤተክርስቲያናችን ወቅታዊ ሁኔታ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውይይትና ውሳኔ እንደሚያስፈልገው በማመኑ ነው።
በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤ በሚደርሰው ስምምነት መሠረት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አህጉረ ስብከት ያሉ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሊጠሩ እንደሚችሉ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አሳውቋል።