ግንቦት ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
+++++++++++++++++++
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባህርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ “ተደራሽነት ያለው የሕዝብ ግንኙነት ለኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን “በሚል ርዕስ ለአህጉረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊዎች በጁፒተር ሆቴል በተዘጋጀው ሥልጠና መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው አባታዊ የሥራ መመሪያ አስተላለፉ።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዚሁ ጊዜ እንደ ገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ሥራችን ከላይ አስከ ታች ተናቦና ተሳስሮ መስራትን የሚጠይቅ የሥራ ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው የአህጉረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ከጠቅላይ ቤተክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ጋር በዚህ መልኩ ተሳስረውና ሐቅን መሰረት አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ሕዝብ ግንኙነት ሥራዎቻችን ዘመኑን በሚመጥንና ተዐማኒነትን መሰረት ባደረገ አግባብ ተቋማዊ በሆነ መልኩ መከናወን ይኖርበታል ያሉት ብፁዕነታቸው ሁል ጊዜ ችግር ፈቺ ሃሳብን ይዘን ካልተራመድን የትም መድረስ አንችልም ካሉ በኋላ ሥራችን ችግሮችን የሚፈታ፣ የሚያቀራርብ፣ጤናማ እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስም የቤተክርስቲያናችን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ይህ ስልጠና በመዘጋጀቱ አመስግነው ሥራዎች ሁሉ ዘመኑን በዋጀ አግባብ መከናወን ይችል ዘንድ ይህን የመሰለ ሥልጠና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።በመጨረሻም ስልጠናው የተሳካና ውጤታማ እንዲሆን ተመኝተዋል።