የካቲት 5 ቀን 2018ዓ.ም
++++++++++++++
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧
በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ። የሸገር ከተማና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኀላፊ መመሪያ ሰጪነት ድርጅቱ ይዞት የተነሳውን የደንበኛ ተኮር የአስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የገንዘብ አስተዳደሩን ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን በማመን ለተፈጻሚነቱ ተደጋጋሚ ጥረት እያደረገ መሆኑን የተረዳው ወጋገን ባንክ ከድርጅቱ ጋር ለመሥራት አማራጭ ሐሳብ ይዞ መምጣቱን የሚገልጽ ጥናታዊ ጽሑፍ መላው የድርጅቱ አስተዳደር ጉባኤ አባላት በተገኙበት አቅርቧል ።
ውይይቱ በቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ በሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የተመራ ሲሆን የወጋገን ባንክ የሥራ ኃላፊዎችና የቢዝነስ ሥራው ላይ እየሠሩ ያሉ አካላት በቀረበው ጥናት ላይ ከአስተዳደር ጉባኤ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
የድርጅቱ ደንበኞች ያለ ምንም እንግልት ወደ ቢሮ መምጣት ሳይጠበቅባቸው እንዴት መክፈልና ሒሳብ ማወራረድ እንደሚችሉ ፣ በደንበኞች የተያዙና ያልተያዙ ቤቶችን እንዴት ማወቅ እንደሚቻልና ተጨማሪ ክፍያዎችን እንዴት ማስተናገድ እንደሚቻል እንዲሁም በየጊዜው ደንበኞችን ለማንቃት የምንጠቀምበትን መንገድን ቀላልና ምቹ ለማድረግ ሰፊ ጥረት ሲያደርግ የቆየ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በዚሁ መሠረት የድርጅቱን መልካም ጥረት ከግብ ለማድረስ እገዛ ለመስጠት የተለያዩ ባንኮችና ድረጅቶች የመጡ ሲሆን በዛሬው እለትም ወጋገን ባንክ ከድርጅቱ ጋር አብሬ ብሠራ የምሰጣቸው ጥቅሞች ያላቸውን በዝርዝር አቅርቧል።
በመቀጠልም ባንኩ ባቀረባቸው ሐሳቦች ላይ የድርጅቱ አስተዳደር ጉባኤ ባደረገው ውይይት ድርጅቱ ዘመኑን የዋጀ የገንዘብ አስተዳደርና ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ውስጥ መግባት ዘመኑ የሚጠይቀው አስገዳጅ ሂደት መሆኑን አምኖ የተሻለ አማራጭ ላይ አጽንዖት መስጠት እንደሚገባ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን ሌሎች ከቤተክርስቲያን ጋር በአጋርነት የሚሰሩ ባንኮችም በቴክኖሎጂ የታገዘ የክራይ አፈጻጸም ሥርዓትን በመዘርጋትና ተመራጭ የቴክኖሎጂ አማራጭ በማቅረብ መስራት እንደሚጠበቅባቸው በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።









