መጋቢት ፲ቀን፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን ተከትሎ የአመራር ብቃትን ለማሳደግና ዘመኑን የዋጀ የአሠራር ሥርአትን በመገምባት በሁሉም ዘርፍ የተገነባች ቤተ ክርስቲያንን ለትውልድ ማስተላለፍን ዓላማው ያደረገ የሁለት ቀናት የምክክር ጉባኤ በመካሔድ ላይ ነው።

በምክክር ጉባኤው ላይ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ፣የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ፣የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል ኃላፊዎች፣የጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያውና የየድርጅቶቹ ኃላፊዎች፣ምክትል ኃላፊዎችና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰባቱ ክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆች ይሳተፋሉ።

በዚሁ ጊዜ ሕግን ጠብቆ አለመስራት የሚያስከትለው ተጠያቂነት በሚል ርዕስ፣የዐሥር ዓመቱ ዕቅድ አተገባበር በሚል ርዕስ፣የዕቅድ አዘገጃጀትና አቀራረብ በሚል ርዕስ፣የሪፖርት አቀራረብ በሚል ርዕስ፣ስለ መረጃ አደረጃጀትና አያያዝ በሚል ርዕስ፣የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት በሚል ርዕስ፣ስለ ፐርሰንት አከፋፈል ከቃለ ዐዋዲው መመሪያ አኳያ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡ ሲሆን ጸሑፎቹም በዘርፉ ከፍተኛ እውቀትና የትምህርት ዝግጅት ባላቸው ባለሙያዎች የሚሰጥ ይሆናል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሥልጠናው መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት የቤተክርስቲያንን ሁለንተናዊ የሥራ ሒደትን በማዘመን ቀልጣፋ ሥራ መስራት ይቻል ዘንድ በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የተገኛችሁ ሁሉ እንኳን በሰላም መጣችሁ ካሉ በኋላ የምክክር ጉባኤው የተሳካና ውጤታማ መሆን እንዲችል ጸሎታችን ነው ብለዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባህርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዚሁ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የምክክር ጉባኤውን አስፈላጊነት በተመለከተ ሠፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።በዚህ ማብራሪያም ቀደምት አባቶችን ዘመኑ በፈቀደላቸው ሁኔታ በርካታ መሰናክሎችን አልፈው ለቤተክርስቲያን ሁሉን አቀፍ እድገት መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ተጋድሎን በሚገባ ተጋድለው ለዚህ ትውልድ አስረክበዋታል። ብለዋል።

አያይዘውም ይህ ትውልድ ከቀደምት አባቶቹ የተረከባትን ቤተክርስቲያን በሚገባ ጠብቆ፣አስጠብቆና አስከብሯታል ወይስ ቤተክርስቲያንን ከመሪነት ሚናዋ አዋርዶ ወደ ታች ጥሏታል? ያሉት ብፁዕነታቸው ቤተክርስቲያናችን አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በመመዘንም አሰራራችንን በማዘመንና ዘመኑን የሚዋጅ በማድረግ የቤተክርስቲያንን ተልዕኮ ለማሳካት መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን በርካታ ፈተናዎች ገጥመዋታል ፈተናዎቹ ግን አላንበረከኳትም ካሉ በኋላ ለፈተና የማይንበረከክ፣ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥና የቤተክርስቲያንን አሰራር በማዘመን ለውጥ የሚያመጣ አመራር ስለሚያስፈልግ ይህ የምክክር ጉባኤ ሊዘጋጅ ችሏል በማለት የጉባኤውን መከፈት አብስረዋል።

ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቀደም ብሎም ሊቀ መዘምራን ሀረገወይን ጫኔ የምክክር ጉባኤውን አስፈላጊነት፣ለምክክር ጉባኤው መዘጋጀት ምክንያት የሆኑ መነሻ ሀሳቦችን በመጥቀስ መልዕክት አስተላልፈዋል።የምክክር ጉባኤው ለሦስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ዙሪያ ውይይት ይደረግባቸዋል።በመጨረሻም ጉባኤው የአቋም መግለጫ በማውጣት የምክክር መድረኩ ማጠቃለያ ይሆናል።