ዘጋቢ መ/ር ጌታቸው በቀለ
(© EOTC TV ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም አዲስ አበባ)
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ከግንቦት ፲፭-፲፮ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም ለኹለት ቀናት ከመላው ኢትዮጵያ ለመጡ የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ በመንበረ ፓትርያርክ በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ በመክፈቻ መርኸ ግብር ብፁዕ አቡነ አብርሃም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከመላው ኢትዮጵያ የቤተክርስቲያን ጥሪ ተቀብለው በምክክር ጉባኤው ላይ ለተገኙት ሊቃውንት “እንኳን ደህና መጣችሁ” በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም “ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከጥንት ጀምሮ ጠብቀው ያቆዩት አባቶቻችን ሊቃውንት ቅዱስ ሲኖዶስ ባልተቋቋመበት ጊዜ ሁሉ፤ ቤተክርስቲያኗን የሚመሩ የሚጠብቁ ሊቃውንቱ ነበሩ፡፡ ለዚህች ቤተክርስቲያን ጥብቅናቸው የሚያስደስት ነበር” ብለዋል፡፡ ዛሬም “ቅድስት ቤተክርስቲያንን መጠበቅና ማስጠበቅ የእናንተ የሊቃውንቱ ድርሻ ነው” ያሉት ብፁዕነታቸው በጉባኤው ቆይታችሁ ምሁራኑም በሚያቀርቡት ጥናት መሠረት ተወያይታችሁ የምታቀርቡት ምክረ ሐሳብ ለቅዱስ ሲኖዶስ ግብአት እንደሚኾን እንጠብቃለን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መልአከ መዊዕ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ኃላፊ እንደተናገሩት “የአብነት ትምህርት ቤት ለቤተክርስቲያን መሠረት ነው በሚል ቃል ከመላው ኢትዮጵያ ከመጡ መምህራን ጋር ምክክር፣ ውይይት በማድረግ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ክፍተት በመዳሰስ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በተጠናና በተረዳ ነገር እንዲረዱ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡ መልአከ መዊዕ አያይዘውም እነዚህ ሊቃውንት ቤተክርስቲያን ስላለችበት ሁኔታ በመንፈሳዊም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳይ በመወያየት ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የሚደግፍ ምክር ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ በየዓመቱ ግንቦት ወር ላይ ከርክበ ካህናት በፊት፤ ሊቃውንቱ እየተሰበሰቡ እንዲመክሩ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ የመምሪያው ዋና ዓላማም ሊቃውንቱ ቤተክህነቱን እንዲያውቁት፤ ቤተክህነቱም ትውልድ እያፈሩ ያሉትን ሊቃውንቱን እንዲያውቃቸው፣ እንዲረዳቸው፣ እንዲደርስላቸው ማድረግ መኾኑን ጨምረው አስረድተዋል፡፡
በኹተኛው የጉባኤው በማጠናቀቂያው ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት “ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ትውልድ እያፈራችሁ፣ እያስተማራችሁ የቤተክርስቲያን ትምህርት ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፋችሁ ነው፡፡ ለቤተክርስቲያን ያላችሁ ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነትና ጥበቃ ቤተክርስቲያን ምንጊዜም በእናንተ ነው የምትጠበቀው፡፡ ቤተክርስቲያን ቁማ ያለችው በሊቃውንቷ አስተማሪነት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እየጠነከረ እንዲሄድ ጸሎታችን ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ጥሪ ተቀብላችሁ ጉባኤ ማካሄዳችሁ ታሪካዊ ጉባኤ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ጉባኤም መቀጠል አለበት” ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ቅዱስነታቸው ጉባኤ ቤት ለአላቸው የአብነት መምህራን የምስክር ሰርተፊኬት ሰጥተው ጉባኤው ተጠናቋል፡፡