ኅዳር ፲፰ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የጠቅላይ ቤተክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአስተዳደር ጉባኤ አባላት በዛሬው እለት ባደረጉት የጋራ ጉባኤ ተስማሙ።

ሀገረ ስብከቱ ለጠቅላይ ቤተክህነት በይግባኝ የቀረቡ አቤቱታዎችና ለጉባኤው በአጀንዳነት የቀረቡት ሰነዶች  በሸኚ ደብዳቤ እንዲደርሰው ተደርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደሚሰጥበት እንደሚያደርጉ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገለጹ።

በዚሁ የጋራ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብና ጥብቅ የሥራ መመሪያ ከእንግዲህ በኋላ በሀገረ ስብከቱ የአሰራር ስህተትና መመሪያን አክብሮ ባለመስራት ምክንያት የሚያለቅሱ ካህናት እምባቸው እንዲታበስ፣ማንም ሰው አያልቅስ፣ፍትህ እንዲነግስ፣የተበደለ እንዲካስ፣ቤተክርስቲያንን ብቻ ማዕከል በማድረግ እንስራ ፣የሚደረግ ዝውውርና የሚሰጥ ሹመት በህግና በመመሪያ ብቻ እንዲከናወን፣
የማንኛውም የሥራ ኃላፊና የአድባራት ወገዳማት አክተዳዳሪዎች ዝውውር ሥራን ማዕከል ባደረገ አግባብ ብቻ እንዲከናወን፣የሚከናወኑ ዝውውሮች ሁሉ በምክንያት ብቻ እንዲሆኑ፣ማንም ሰው ሲያድግም ሆነ ሲዛወር በሥራ አፈጻጸሙ ማለትም የሚያድግ ባሳየው የሥራ እድገት፣የሚዘወርድ ደግሞ ባስመዘገበው የሥራ ድክመት ብቻ እንዲሆን፣በተደጋጋሚ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤና በቋሚ ሲኖዶስ በተሰጠው መመሪያ መሰረት ከሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጅ አገልጋዮች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ ወደ ሥራ መደባቸው እንዲመለሱ የመጨረሻና ጥብቅ መመሪያ ሰጥተዋል።

በሀገረ ስብከቱ በኩል ከጠቅላይ ቤተክህነት የሚሰጡ መመሪያዎችን ሁሉ “ጠቅላይ ቤተክህነት ምን አገባው” በሚል ሰንካላ ምክንያት የሚደረገው መመሪያን ያለማክበርና ያለመፈጸም ተግባር  ችግሮችን ላለማባባስ ሲባል በትዕግስት ስናልፈው ቆይተናል ያሉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ከዚህ በኋላ ይህ አይነቱ ተግባር ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና በትዕግስት የምናልፈው ጉዳይ አይደለም  ብለዋል።

አያይዘውም ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መመሪያ መሰረት ሀገረ ስብከቱ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ቤተክህነቱ መሆኑን ታሳቢ ባደረገ አግባብ ሕግና ሕጋዊ አሰራርን ብቻ በመከተል ሥራውን ማከናወን እንደሚገባው ገልጸው በጅምላና ምክንያታዊ ባልሆነ አግባብ የሚደረግን ዝውውርና እድገት ጠቅላይ ቤተክህነቱ በፍጹም የማይታገሰው መሆኑን በመረዳት ሀገረ ስብከቱ ሕግን አክብሮ መስራት ይገባዋል ብለዋል።

በሀገረ ስብከቱ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር በብፁዕ አቡነ አብርሃምና በብፁዕ አቡነ ሔኖክ መካከል የተፈጠረ ችግር በመኖሩ የተፈጠረ  በማስመሰል ለህገወጥ ድርጊቶች ሽፋን ለመስጠት መሞከር ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የገለጹት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በእርሳቸውና በብፁዕ አቡነ ሔኖክ መካከል ምንም አይነት ልዩነትና ጸብ የሌለ መሆኑን ጠቁመው እየተጋጨ ያለው ሥራው በህግና በመመሪያ ተደግፎ ማዕከላዊነትን ባልጠበቀ አግባብ በመከናወኑ ስለሆነ መፍትሔውም ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣውን ደንብ አክብሮ መስራት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

የምንሰራው ሥራ መንፈሳዊ አገልግሎት እንደመሆኑ መጠን እውነትንና እውነተኛነትን ብቻ መሰረት ባደረገ አግባብ መከናወን ይኖርበታል ያሉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሀገረ ስብከቱ ካህናትና ምዕመናንን ከሚያሳዝንና በቤተክርስቲያን ላይ አመኔታን ከሚያሳጣ ሥራ በመራቅ ሀቅን መሰረት አድርጎ መመሪያን በማክበር እንዲሰራ የመጨረሻ ያሉትን መመሪያ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም ጉባኤው እንዲህ አይነቱ የጋራ መድረክ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብና በብፁ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የተሰጡ መመሪያዎችን አክብሮና አስከብሮ ለመስራት በመስማማት የዕለቱን ጉባኤ በጸሎት አጠናቋል።