ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም
===============
አዲስአበባ -አበበ
“””””””””””””””””””””””
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማት እና በእርጅና ምክንያት በፈረሰው በተለምዶ መሐሙድ ሙዚቃ ቤት በመባል በሚታወቀው “በጽርሐ ምኒሊክ” ሕንጻ ምትክ ዐዲስ ሁለገብ ሕንጻ ገንብቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስረከበ። ሕንጻውን ያስረከቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሲሆኑ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ሕንጻውን ተረክበዋል ።
በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ; ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የደቡብ ምሥራቅ ትግራይና የራያ አህጉረ ስብከት፣ ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ወጪው ሙሉ በሙሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሸፍኖ የተገነባው አዲሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሁለገብ ሕንጻ በኮሪደር መልሶ ማልማት እና ሕንጻው በእርጅና ምክንያት የተጎዳ በመሆኑ በአዲስ መልክ ባለ 7 ወለል ሕንጻ የቀድሞው ሕንጻ ምትክ ሁኖ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ እንደሆነ ተገልጿል ። ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በምረቃ እና በርክክብ መርሐ ግብር ላይ ”ልማት የበጎ ሐሳብ ውጤት ነው ”በማለት ንግግራቸው የጀመሩ ሲሆን ይህን የመሰለ ዘመናዊና ሁለገብ ሕንጻ በመገንባት ላስረከቡን ክብርት ከንቲባና ባለድርሻ አካላት ሁሉ በከፍተኛ ደስታ ምስጋናቸውን አቅረበዋል ።
ቅዱስ ፓትርያርኩ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር “የቄሳርን ለቄሳር ስጡ” በማለት የጀመሩ ሲሆን የእግዚአብሔር የሆነ ነዋይ በክብር ስላስረከባችሁን እናመሰግናለን በማለት ምስጋናቸውን አቅረበዋል ። ቅዱስነታቸው ቃልን በሥራ ለመተግበር የተከናወነው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን የተገለጹ ሲሆን በቤተክርስቲያንዋ ለክብርት ከንቲባዋ እና ከተማ አስተዳደሩ የዕውቅናና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት “መልዕክት ዘመኑ የዋጀ ለቀጣይ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነው ከአከባቢው ጋር የሚስማማ ዘመናዊ ሕንጻ ነው ሲሉ ” ገልጸዋል ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በከተማው በተለያዩ ቦታዎች ለኮሪደሩ ልማት እያደረገችው ያለችውን አስተዋጽኦ በማውሳት ምስጋናቸውን አቅርበዋል ። በከተማ አስተዳደሩ በሕንጻው ግንባታው በሙያቸው ሲወጡ ሲወርዱ የነበሩ አካላት የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ።
ሁለገብ ሕንጻዉ በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ በተለምዶ መሐሙድ ሙዚቃ ቤት በመባል በሚታወቀዉ የቤተክርስቲያኗ ይዞታ ላይ የተገነባ ነዉ።