ጥር ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም
*****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
+++++++++++++

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኮሪደር ልማት ምክንያት በፈረሱና ከመንግስት በተሰጧት ቦታዎች ላይ ሁለገብና ዘመናዊ ሕንጻዎችን በማስገንባት በአስቸኳይ አገልግሎት ላይ እንድታውል የቅዱስ ሲኖዶስምልአተ ጉባኤ በግንቦቱ ርክበ ካህና ወቅት ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አሶኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጋር በመቀናጀት የሰጡትን ቆራጥ አመራር መነሻ በማድረግ በሚገነቡ ሕንጻዎች አጠቃላይ ይዘት፣ደረጃና ዝርዝር የሥራ ሁኔታዎች ላይ በባለሙያዎች አማካኝነት ጥናት ሲካሔድ ቆይቶ ሕንጻዎቹን ለመገንባት ይቻል ዘንድ ሕጋዊ ጨረታ እንዲወጣ ተደርጎ በዛሬው ዕለት ጨረታውን ካሸነፉ ኮንትራክተሮች ጋር አማካሪ ድርጆቱ EEF በተገኘበት የውል ስምምነት ፊርማ ሥነሥርዓት ተከናውኗል።

በዛሬው ዕለት የፊርማ ሥነሥርዓት ከተከናወነባቸው የግንባታ ሥራዎች መካከል ፒያሳ አካባቢ የሚገነባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዝክረ ቅዱሳን ህንጻ 2B G+7አንዱ ሲሆን የግንባታ ሥራውን ለማከናወን ምንሀር ኮንስትራክሽን የተባለው ሕንጻ ተቋራጭ ሲሆን አራት ኪሎ አካባቢ ከጠቅላይ ቤተክህነት ጀርባ ባለው ስድስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሕንጻ አበው በሚል ስያሜ ለሚገነባው 2B+SBG+12+T ሁለገብ ሕንጻ ደግሞ አተም ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ የተባለው ድርጅተ አሸናፊ በመሆን ከቤተክርስቲያናችን ጋር የግንባታ ውል ስምምነት ተፈራርሟል።

ቤተክርስቲያን በሕንጻ ግንባታ ዘርፍ በርካታ አዳዲስና ዘመናዊ ሕንጻዎችን በመገንባት ለበርካታ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድልን እንደምትፈጥር፣ከሕንጻ ኪራዩ በሚገኘው ገቢም መንፈሰዊ አገልግሎቷን እንደምታስፋፋና እንደምታጠናክር እንዲሁም በከተማችን የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግሮችንም በመፍታት ማኅበራዊ ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በፊርማ ሥነሥርዓቱ ወቅት ገልጸዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ብፁዕ አቡነ አቡነ ሳዊሮስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤተክርስቲያናችን ታሪክ የመጀመሪያና ግዙፍ የሆኑ ሕንጻዎችን መገንባት የሚያስችላትን ሰኬታማ ሥራ መስራት መቻልዎ ዕድለኝነትዎንና የልማት ሰውነትዎን የሚያረጋግጥ ስለሆነ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል ካሉ በኋላ እነዚህን ታሪካዊ ሕንጻዎችን ለመገንባት ከቤተክርስቲያን ጋር ውል የገባችሁ ኮንትራክተሮችም የተጣለባችሁን ከባድ ታሪካዊና መንፈሳዊ ኃላፊነት በትጋትና በታማኝነት በመፈጸም ሥራችሁን በገባችሁት ውል መሰረት በስኬት እንድትወጡ አደራ ለማለት እንወዳለን ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ውል ተገብቶባቸው ወደ ሥራ የገቡት ሁለቱ ግዙፋን ሕንጻዎች በቤተክርስቲያን ታሪክ የመጀመሪያዎቹና በግዝፈትና በጥራታቸው የተዋጣላቸው ሆነው የሚገነቡ ሲሆን ለቤተክርስቲያናችን ኩራትን ለከተማችን ተጨማሪ ውበትን የሚያላብሱ ግንባታዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል።ሕንጻዎቹ በአራት ኪሎ አካባቢ የሚገነባው በሰላሳ ወራት፣ ፒያሳ አካባቢ የሚገነባው ደግሞ በሃያ ወራት ውውጥ የሚጠናቀቁና አገልግሎት ላይ የሚውሉ መሆናቸው ታውቋል።