መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም
ፕሪቶሪያ
==============
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤውን በፕሪቶሪያ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምህረት ማካሔድ ጀምሯል።

ጉባኤው በብጹዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀድያ ስልጤ የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቡራኬና በጸሎተ ወንጌል ቡራኬ ተከፍቷል።

ብፁዕነታቸው በጉባኤው መክፈቻ ባስተላለፉት ቃለ ምእዳን “በባዕድ ሀገር የምናገለግል አገልጋዮች በአገልግሎታችን ቤተክርስቲያን የሰጠችንን ተልዕኮ በትጋት በመፈጸምና በዚህ ጉባኤ በንቃት በመሳተፍ የሀገረ ስብከታችንን ተግባራት ማዘመን አለብን ለአዲሱ ትውልድና ለደቡብ አፍሪካ ዜጎችም ተስፋ መሆን ይገባናል” ብለዋል።

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማዕምራን ብርሀኑ ተክለያሬድ በበኩላቸው “አገልግሎታችን በህግና በሥርዓት እንዲሁም በተገቢው አስተዳደራዊ መዋቅር እየተመራ መፈጸም አለበት ይህንን ስናከናውን እግዚአብሔርንም ሰውንም ማስደሰት እንችላለን” ብለዋል።

በዛሬው የጠዋት መርሐ ግብር ቤተክርስቲያኗ በደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት በ2016 ዓ.ም የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት በሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ስዩማን ሰሎሞን ገብረ መስቀል ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም በሚጠናቀቀው ጉባኤ፥ የሁሉም አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ የሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርትና ዋና ጸሓፊዎች፣ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን ደቡብ አፍሪካ ማዕከል ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

መረጃው የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ነው