ሚያዝያ ፳፮ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
በየዓመቱ በበዓለ ትንሣኤ ዋዜማ “በቀዳም ስዑር” የሚከበረው የገብረ ሰላመ በዓል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአከኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት ዛሬ ሚያዝያ ፳፮ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓተ አምልኮ ተከበረ።
በዓሉ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን መፈጸሙ የሚዘከርበት፣ በመስቀል ላይም በፈጸመው የማዳን ሥራ ለዓለም ድኅነትን መስጠቱ የሚታወጅበት ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ነው። በኖኅ ዘመን መጥቶ የነበረው ጥፋት ማብቃቱ ርግቧ ይዛ በመጣችው የወይራ ቅጠል እንደታወቀ ሁሉ በአዳም በደል ምክንያት በሰው ልጆች የውድቀት ዘመን ማብቃቱ የሚታወጅበት ቄጤማም በቅዱስ ፓትርያርኩ ለበዓሉ ታዳሚዎች ሁሉ ከመልካም ምኞት ጋር ታድሏል።
በቅዱስ ያሬድ ለዕለቱ የተዘጋጀው “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ…” የሚለው ቃለ እግዚአብሔርም ለዕለቱ በተመደቡት በመርካቶ ደብረ አሚን ዳግሚት ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሊቃውንት ደርሷል።
በዐሉ ላይም በቅዱስነታቸው መሪነት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ምእመናን ተገኝተዋል።