ሰኔ 5 ቀን 2016 ዓ/ም አዲስ አበባ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ገዳማት አስተዳደር መምሪያ ያዘጋጀውና በሀገራችን አራቱም ማዕዘናት የሚገኙ ገዳማት አበ ምኔቶች እና እመ ምኔቶች የሚሳተፉበት የውይይትና የምክክር ጉባኤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሚገኘው ጽርሐ-ተዋሕዶ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
ጉባኤው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጸሎትና ቃለ በረከት የተጀመረ ሲሆን ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተዘጋጀው የውይይትና የምክክር መድረክ አስፈላጊነትኛ ጠቃሚነት ዙሪያ የሥራ መመሪያና አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ መምሪያውም እንዲህ ዐይነት ለሀገርና ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ጉባኤ በማዘጋጀቱ ሊመሰገን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ገዳማት አስተዳደር መምሪያ በዓመቱ ካቀዳቸውና ካከናወናቸው ተግባራት መካከል አንዱ በሆነው በዚህ ሀገር አቀፍ የውይትና የምክክር መድረክ ከቀድሞው ለየት ባለ መልኩ ከገዳማት አበ ምኔቶች በተጨማሪ እመ ምኔቶች እንዲካተቱ ከማድረጉም በላይ የየአህጉረ ስብከቱ የገዳማት አስተዳደር ክፍል ኃላፊዎች እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙ ገዳማት አስተዳዳሪዎችም እዲሳተፉ አድርጓል፡፡
በጉባኤው ለገዳማውያኑ የውይይትና የምክክር መነሻ የሚሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎች በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርቡ ሲሆን ገዳማውያን አባቶችና እናቶችም በሚቀርቡት ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻነት የሚወወያዩ ይሆናል፡፡ መምሪያው ያዘጋጀው ይህ የውይይትና የምክክር ጉባኤ ስለ ሀገር ሰላም የሚጸለይበት ገዳማውያን ስለ አሐቲ ቤተ ክርስቲያን አጥብቀው የሚመክሩበትና መልእክታቸውንም በመላው ዓለም ለሚገኙ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆች እና ለቤተ ክርስቲያናችን ወዳጆች የሚያስተላልፉበት እንደሚሆን የመምሪያው ዋና ኃላፊ መጋቤ ካህናት ቆሞስ አባ ሀብተጊዮርጊስ አሥራት ገልጸዋል፡፡