የጠቅላይ ቤተክህነትና የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባዔ አባላት በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ የጋራ ጉባዔ በማድረግ ላይ ናቸው።

ኅዳር ፲፰ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
=================
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ጉባኤ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ጋር በሁለትዮሽ የአሰራር ሒደት፣በመልካም አስተዳደር፣በሕግ ፣ደንቦችና መመሪያዎች አከባበር በአጠቃላይ ሥራዎችን በተቋማዊ አሰራር ሒደት በማከናወን ዙሪያ የጋራ መድረክ ተዘጋጅቶ ውይይት እንዲደረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ዛሬ ኅዳር ፲፰ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ የጋራ ጉባኤ በማካሔድ ላይ ናቸው።

በጉባኤው መክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት፣ቃለ በረከትና ቡራኬ በቤተክርስቲያናችን ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ሁላችንም እናውቀዋለን።ማስተካከልም እንችላለን ብለዋል።

እኛ በቤተክርስቲያናችን የሚስተዋለውን ችግር ለማስተካከል የምንቸገረው ልባችን ስላልተስተካከለ ነው።ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ ራሳችንን ሳናስተካክል ሌላውን ማስተካከል ስለማንችል ቅድሚያ ራሳችንን ለማስተካከል ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል ብለዋል።

አያይዘውም ሁላችንም የቆምነው ለቤተክርስቲያናችን እንጂ ለሌላ ዓላማ አይደለም።ያሉት ቅዱስነታቸው ችግሮቻችንን ለመፍታት መወያየት ተገቢ ነው።”ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” እንደሚባለው ሁሉ ችግሮቻችንን ለመፍታት ከልብ ከተነሳን የሚያስቸግር ነገር ይኖራል ብለን እናምናለን ካሉ በኋላ ከተጠያቂነትና ከተወቃሽነት ለመዳን፣ቤታችንን ለማቅናትና ለማስተካከል የሚጎለን ምንድነው ?ያሉት ቅዱስነታቸው ይህን ለማድረግና ቤተክርስቲያናችንን ለመጠበቅ ሙሉ ሥልጣንና ኃላፊነት እያለን መቸገራችን ያስገርማል ብለዋል።

ዘወትር ሁላችንም ራሳችንን መመርመር አለብን የት ነው ያለነው፣ምንድነው የምንሰራው፣ወዴት ነው የምንሔደው ብለን ራሳችንን በመጠየቅ ያለፈውን ጊዜ ችግሮች ማሰብና በተሰጠን መንፈሳዊ ኃላፊነት ልክ በመስራት ቤተክርስቲያንን መጠበቅና ምዕመናንን የሚያረካ ተግባር መፈጸም ይኖርብናል ያሉት ቅዱስነታቸው ሁላችንም ራሳችንን በአግባቡ በመመርመር ራሳችንን እናስተካክል ካሉ በኃላ በአንድነትና በጽናት ለቤተክርስቲያናችን እንቁም።በመመካከር አንድ ሆነን በመቆም ለቤተክርስቲያን ህልውና በጋራ እንስራ እኛ ተመካሪዎች አይደለንም መካሪዎች እንጂ ስለዚህ መመካከር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚጠቅም ስለሆነ ተመካክረን እንስራ ችግሮችንም በግልጽ በማውጣት ለችግሮቻችን መፍትሔ በማበጀት ለውጤት ልናበቃው ይገባል በማለት አባታዊ መልእክታቸውን በማጠናቀቅ ጉባኤውን በይፋ ከፍተዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት፦ መልካም አስተዳደርን ለማምጣትና ችግሮችን ለመፍታት ውይይት ወሳኝ ነው።ቅዱስነትዎም በቤተክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የዘወትር ምኞትዎና ጸሎትዎ እንደሆነ ይታወቃል።

በዚህ ጊዜ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በጋራ ተወያይተን መፍታትና የቁጥጥር ሥርዓታችንን በማጥበቅ ችግሮችን በአግባቡ መፍታት አለብን ብለዋል አያይዘውም ህገወጥ ቅጥርና ዝውውርን በተመለከተ እየተከናወነ የሚገኘውን ህገ ወጥ ቅጥርና ዝውውር በማረም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በቀረበው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት መስራት ይኖርበታል ብለዋል።

ሀገረ ስብከቱና ጠቅላይ ቤተክህነቱ ተናበውና ተግባብተው መስራት በሚገባቸው ጉዳዩች ላይም ሕግንና ሕግን መሰረት አድርገን መስራት ስለሚገባቸው ይህን መድረክ ለማዘጋጀት ተገደናል ያሉት ብፁዕነታቸው የዚህ መድረክ ዓላማ ለመወነጃጀል ለመነቃቀፍና ለመተቻቸት ሳይሆን በመወያየትና በመግባባት በሀገረ ስብከቱ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት ነው በማለት የመክፈቻ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።

ጉባኤው በዛሬው እለት በሚያካሒደው ጥልቅ ውይይት ሕግ፣መመሪያ፣ደንቦችና ተቋማዊ አሰራሮችን በጠበቀ መልኩ ሥራዎችን በማከናወን ማዕከላዊነትን ባለማክበር ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት ተቋማዊና ሕጋዊ አሰራሮችን በመተግበር በሀገረ ስብከቱና በጠቅላይ ቤተክህነት መካከል መዋቅራዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር የሚያስችሉ ልዩልዩ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።