ጥር 7 ቀን 2016 ዓ.ም
==============
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱና ዋነኛው ነው። በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የአደባባይ መንፈሳዊ በዓላችን የጥምቀት በዓል ዘንድሮም በታላቅ ሥነሥርዓት የሚከበር ሲሆን በዓሉ በደመቀና ባማረ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሰብሳቢነት ዐቢይ ኮሚቴ ተጀራጅቶ በየዘርፉ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል።

በዚህም መሰረት በዛሬው እለት የጠቅላይ ቤተክህነት አሰሰተዳደር ጉባኤ የእያንዳንዱን ኮሚቴ የሥራ አጻጸም በመገምገም በቀሪዎቹ ቀናት መሠራት በሚገባቸው ሥራዎች ዙሪያ አቅጣጫ ሰጥቷል።

የበዓሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም በሚገባ እየተከናወኑ ሲሆን የባጅ ዝግጅት፣ የስቴጅና የሳውንድ ሲስተም እንዲሁም ጃንሜዳን የማስዋብ ሥራዎች፣ የመርሐ ግብርና የመጽሔት የሕትመት ሥራዎች ተከናውነዋል። በአጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ በተሳካ ሁኔታ በመከናወን ላይ ሲሆኑ በዓሉ በደመቀና በተዋበ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከመቼውም በላይ ክርስቲያናዊ ሥነምግባርን በተላበሰ መልኩ በዓሉን ለማክበር በነቂስ መውጣት እንደሚገባው ቀደም ሲል ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በሰጡት መግለጫ ማሳወቃቸው ይታወሳል።

በተለያዩ ቦታዎች የሚከናወኑ የጥምቀት በዓል ዝግጅቶችን መረጃ በተከታታይ የምናቀርብ መሆኑንም ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።