ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ባዘጋጀው የቤተክርስቲያን ደን ልማት ኮንፈረንስ ላይ ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ።

የቅዱስ ፓትርያርኩ መልዕክት ሙሉ ቃል
እንደሚከተለው ይነበባል፦

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
•ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
•ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
•ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ፤
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት፤
•የተከበራችሁ የኃይማኖት መሪዎች፤
•የተከበራችሁ የመንግስት ኃላፊዎች፤
•የተከበራችሁ አምባሳደሮች፤
•የተከበራችሁ የሲቪል ማህበራት አመራሮች፤
•የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፤
•ክቡራንና ክቡራት፤
እንኳን ደህና መጣችሁ፤
“ወነሥአ እግዚአብሔር ለእጓለ እመሕያው ወሤሞ ውስተ ገነት ከመ ይትገበራ ወይዕቀባ፡-እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም፤ ይጠብቃትም ዘንድ በኤዶም ገነት አኖረው” (ዘፍ 2፡15)
ከዚህ ጥቅስ እንደምናስተውለው እግዚአብሔር አምላካችን በማይመረመር ጥበቡ ከምድር በላይ ከሰማይ በታች የሚገኙትን ፍጥረታት አስቀድሞ ፈጥሮ የሥነ ፍጥረት መደምደሚያ (ጉልላት) የሆነው ሰው ይገለገልባቸው ዘንድ ፈቃዱን ገልጦለታል፡፡ በተለይም ደግሞ በኤዶም ገነት የነበሩትን ዕፀዋት የመጠበቅና የመንከባከብ ሓላፊነትን ሰጥቶታል፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያንም ይህን አምላካዊ አደራ ተገንዝባ ለዘመናት በዙሪያዋ አገር በቀል ዕፅዋትን እየተከለች በመንገድ የደከሙ የሚያርፉበት ጥላ፤ ለተራቡት ምግበ ሥጋ፤ መኖሪያ የሌላቸው የሚያድሩበት መጠለያ ይሆኑ ዘንድ ጠብቃና አስጠብቃ ቆይታለች፡፡

ለአብነትም ያህልም በሀገራችን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩና ለአካባቢ አየር ጥበቃ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው አገር በቀል ደኖች የሚገኙት በቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ ነው፡፡
እነዚህ ደኖች ቅዱሳን ባሕታውያን የሚጸልዩባቸው ብቻ ሳይሆኑ በየዘራቸው፣ በየዓይነታቸው፣ በየወገናቸው፣ በየመልካቸው፣ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው እንስሳትና አራዊትም ደኑን ዓለማቸው አድርገው የሚኖሩበትና የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ የሚገለጽበት ነው ደን ማለት፡፡

ዓለመ ደን ጥቅሙ ለሰብአዊ ፍጡር ብቻ አይደለም ለፍጥረቱ ሁሉ ነው እንጂ፡፡

ከጥንት ጀምሮ ቤተክርስቲያን በረሃማነትን ለመቀነስ በደን ጥበቃ በኩል ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም በአለንበት ዘመን ከሕዝብ ቁጥር መጨመር እና ከልዩ ልዩ ምክንያቶች ጋር ተያይዞ የደን መመናመን ይታያል፡፡

ስለሆነም እግዚአብሔር አምላክ ለሕይወታችን እንደሚያስፈልገን አውቆ አስቀድሞ ፈጥሮ አዘጋጅቶ የሰጠንን ሀብት እንዳናጣ መንከባከብና ባረጁት ዕፅዋትም ምትክ አዳዲስ ችግኞችን መትከል ይገባናል፡፡ ይህን ስናደርግ ምድራዊ ሕይወታችን የተስተካከለና የተደላደለ ይሆናል፡፡

በአንጻሩ ዕፅዋትን በአግባቡ ካልተንከባከብን አፈራችን በጎርፍ ተጠራርጎ፣ በአውሎ ነፋስ ተሸርሽሮ የምድሪቱን ልምላሜ የምናጣ ከመሆኑም ባሻገር ፀሐይና ድርቅ ይበረታል፤ የአካባቢያችን አየር ይለወጣል፤ ድርቅ እና ረሃብ ይበዛል፤ ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ለከፋ ችግር ይጋለጣሉ፡፡

በመሆኑም እግዚአብሔር እንድንጠቀምባቸው የሰጠንን ዕፅዋት የመጠበቅና የመንከባከብ ሓላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ ለመወያየት እንዲሁም አለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ይቻል ዘንድ ይህ መርሐ ግብር እንዲዘጋጅ ለደከሙ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የዚህ ጉባኤ ተሳታፊዎች የሆናችሁ በሙሉ ሰላም የሰፈነባት፣ ልምላሜ የሞላበት፣ የጥይት ድምጽ የማይሰማባት፣ ሰው በሰውነቱ ብቻ ተከብሮ በነፃነት የሚኖርባት ሀገርን ለትውልድ የማስተላለፍ የታሪክ አደራ የሚጠብቃችሁ መሆኑን በማስታወስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አስተባባሪነት የተዘጋጀው የቤተክርስቲያን ደን ልማት ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት በይፋ መከፈቱን በእግዚአብሔር ስም እናበስራለን፡፡

እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

አባ ማትያስ
ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት
ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ
ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ