ሰኔ 5 ቀን 2016 ዓ.ም.
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
==============
ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ መንፈሳዊ ማኅበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ለሚገኙ ማኅበራት ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠት ይቻል ዘንድ ያጸደቀውን ደንብና መመሪያ አሟልቶ በመገኘቱና ለአንድ ዓመት ያህል በማኅበሩ ዙሪያ በተደረገው ጥናት ማኅበሩ ዕውቅና ቢሰጠው በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት የራሱን በጎ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ስለታመነበት የዕውቅና ምስክር ወረቀቱን ሊያገኝ እንደቻለ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው፣ የደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት እና በመንበረ ፓትርያርክ የቅርሳ ቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሙዚየም መምሪያ እና የማኅበራት ማደራጃ፣ ምዝገባና ቁጥጥር መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በዕለቱ ገለጹ።
በዚሁ ጊዜ የፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ መንፈሳዊ ማኅበር ቅድስት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተጣለበት የገለጹት ብፁዕነታቸው ማኅበሩ የቤተክርስቲያናችንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ሥርዓት እና ትውፊትን ጠብቆ ሊሠራ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ብፁዕነታቸው አክለውም የማኅበራት ማደራጃ፣ ምዝገባና ቁጥጥር መምሪያ ባለፉት ወራት ለ12 መንፈሳውያን ማኅበራት እውቅና መሰጠቱን ገልጸው የዕውቅና የምስክር ወረቀቱም ለሦስት ዓመታት ብቻ የሚያገለግል መሆኑን ጠቁመው ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ መንፈሳዊ ማኅበርን ጨምሮ ሌሎች መንፈሳውያን ማኅበራት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውጪ የሆኑ ተግባራትን ፈጽመው ከተገኙ የተሰጣቸው የዕውቅና ምስክር ወረቀት
እንደሚሰረዝም ገልጸዋል፡፡
የፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ መንፈሳዊ ማኅበር መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ መጋቤ አእላፍ ጸጋዬ ደበበ በበኩላቸው ለማኅበሩ የዕውቅና የምስክር ወረቀት መሰጠቱ እንዳስደሰታቸው በመግለጽ ቤተክርስቲያን የጣለችባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ኦርቶዶክሳዊያን ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም መንፈሳዊ ማኅበሩ በቀጣይ ከሚያከናውናቸው መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ደረጃውን የጠበቀ የሚዲያ ተቋም ለመገንባት እና ቅድስት ቤተክርስቲያንን የሚጠቅሙ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ማቀዱን መጋቤ አእላፍ ጸጋዬ ደበበ ጨምረው ገልጸዋል።
መጋቤ አእላፍ ጸጋዬ ደበበ ባለፈው ወር ከማኅበሩ መዝሙራትና የመዝሙር መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ውዝግብ በማስመልከት በመገናኛ ብዙሃን በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማኅበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ከማግኘቱ በፊት በመንፈሳዊ፣
በማኅበራዊና ልማታዊ ተግባራት ዙሪያ በመሰማራት ገዳማትን በመርዳት፣ አዳዲስ የሚተከሉና እድሳት የሚደረግላቸውን አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ በመገንባት፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመደጎምና በማገዝ፣ የካህናት ማሰልጠኛዎችንና መንፈሳዊ ኮሌጅችን በጀት መድቦ ጭምር በመደገፍና በቤተ ክርስቲያናችን የሚደረጉ ተቋማዊ ሥልጠናዎችን ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈንና የቤተ ክርሰቲያናችን የሚዲያ ተቋማትን ስቱዲዮ በመገንባት መንፈሳዊ ግዴታውን በብቃት የተወጣና በመወጣት ላይ የሚገኝ ማኅበር ነው።