አስተርአየ ዘኢያስተርኢ — የማይታየው ታየ

«አስተርአየ ዘኢያስተርኢ — የማይታየው ታየ»

(ድጓ ዘዘመነ አስተርእዮ)

መግቢያ

ዘኅቡእ እምኅቡኣን ወልዑል እምልዑላን ከተሠወሩት የተሠወረ፥ ከልዑላን በላይ ልዑለ ባሕርይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ባሕርዩን በባሕርዩ ሠውሮ የኖረ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን ሲያስረዳ፦ «ወአስተርአየ በደኃሪ መዋዕል በእንቲኣነ — በኋለኛው ዘመን ስለእኛ ተገለጠ» በማለት። ቅድመ ዓለም ባሕርዩን በባሕርዩ ሠውሮ ይኖር የነበረ ስለእኛ (እኛን ለማዳን) የተገለጠ መሆኑን አስረድቷል። (1ጴጥ. 1፥20)

የማይታየው ፈጣሪ ዓለምን በመፍጠሩ ተገልጿል። ዓለምን ከፈጠረበት ጀምሮ በተለያየ ጊዜ በልዩ ልዩ ምሳሌ በፍጹም ሃይማኖት፥ በምስጋና፥ በጸሎት፥ በትሕትና፥ በንጽሕና፥ በቅድስና ሁነው ለሚሹትና ለሚፈልጉት ሁሉ በየጊዜው ተገልጿል።

በየጊዜው ሲገለጽም በራእይ፥ በሕልም፥ በአምሳል፥ በረድኤት በመሳሰለው ለወዳጆቹ የተገለጸላቸው ሲሆን፤ በኩነት የተገለጸው ግን በዘመነ ሥጋዌ ነው። ይህም በቅደም ተከተል እንደሚከተለው በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ ተዳሷል። በመሆኑም፦

  1. ዘመነ አስተርእዮ ምን ማለት ነው?
  2. አስተርእዮ በጥንተ ፍጥረት
  3. አስተርእዮ በማኅበረ መላእክት
  4. አስተርእዮ በዘመነ አበው
  5. አስተርእዮ በዘመነ መሳፍንት
  6. አስተርእዮ በዘመነ ነገሥት
  7. አስተርእዮ በትንቢተ ነቢያት
  8. አስተርእዮ በዘመነ ሥጋዌ
  9. አስተርእዮ በባሕረ ዮርዳኖስ
  10. ማጠቃለያ፥ በሚሉ ንኡሳን አርእስት በቅደም ተከተል በአጭሩ ይቀርባል።

 

1) ዘመነ አስተርእዮ ምን ማለት ነው?

«ዘመነ አስተርእዮ» የሚለው ሐረግ ከሁለት የግእዝ ቃላት የተገኘ ሲሆን፤ «ዘመን» ማለት በቁሙ ዘመን፥ ዓመት፥ ሴኮንዶች ደቂቃዎችን፥ ደቂቃዎች  ሰዓታትን፤ ሰዓታት ዕለታትን፥ ዕለታት ሳምንታትን፥ ሰምንታት ወራትን፥ ወራት ዘመንን ያስገኛሉ። አንዱ ዘመን ዘመነ መፀው፥ ዘመነ ሐጋይ፥ ዘመነ ጸደይ ዘመነ ክረምት ተብሎ በ4ት ተከፍሏል። ከአንዱ ዘመን ውስጥም ዘመነ ጽጌ፥ ዘመነ አስተምህሮ፥ ዘመነ ስብከት፥ ዘመነ ልደት፥ ዘመነ አስተርእዮ፥ … ወዘተ. እየተባለ ተሰይሟል። ስለዚህ «ዘመን» የሚለውን ቃል የግእዝ መዝገበ ቃላት በቁሙ ዘመን፥ ዓመት፥ ጊዜ፥ ወራት በየስሙና በየክፍሉ ብሎ ተርጒሞታል። (መጽ.ሰዋ.ወግስ ገጽ 4)@3)

«አስተርእዮ» ማለት ደግሞ መታየት፥ መገለጥ ማለት ነው። ሁለቱ ቃላት ሲናበቡ «ዘመነ አስተርእዮ» የሚለውን ሐረግ ይሰጡናል፤ ዘመነ አስተርእዮ የሚለው ሐረግም ሲተረጐም የመታየት ዘመን፥ የመገለጥ ጊዜ … ተብሎ ይተረጐማል። በሌላ ቃልም «ኤጲፋንያ» ወይም በጽርዕ «ሄፒፋንያ» የሚለውን ቃል በተመሳሳይ ትርጓሜ አስተርእዮ መታየት፥ መገለጥ፥ ዕለተ ጥምቀት በማለት ይተረጒመዋል። (መጽ.ሰዋ.ወግስ ገጽ 2)%)

ቅዱሳን ሐዋርያትም በመጽሐፈ ዲድስቅልያ «ግበሩ በዓለ ኤጲፋንያ ዘውእቱ በዓለ ጥምቀት፥ ወይኩን በኀቤክሙ ክቡረ፥ እስመ ቦቱ ወጠነ እግዚእነ ከመ ያረኢ ስብሐተ መለኮቱ አመ ተጠምቀ በውስተ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ — የኤጲፋንያ (የአስተርእዮ) በዓልን አድርጉ፥ እርሱም በዓለ ጥምቀት ነው፤ በእናንተም ዘንድ የከበረ ይሁን። ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ የጌትነቱን ክብር ያሳይ ዘንድ ጀምሮበታልና» ሲሉ፥ የበዓሉን ታላቅነት ገልጸው ትእዛዝ አስተላልፈዋል። (ዲድስቅልያ አንቀጽ @9)

ስለዚህ ጌታ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፥ አብ በደመና ላይ «የምወደው ልጄ ይህ ነው» ብሎ ሲመሰክርለት፥ መንፈስ ቅዱስም በራሱ ላይ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ሲቀመጥ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ስለሆነ ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል።

በመሆኑም ከዚህ አስቀድሞ ለወዳጆቹ በየጊዜው እንዴት ይገለጽላቸው እንደነበር በመጠኑ መግለጽ አስፈላጊ ይሆናል።

 

2) አስተርእዮ በጥንተ ፍጥረት

ዓለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ የማይታይ የማይመረመር የነበረው ጌታ ዓለምን በመፍጠሩ ፈጣሪነቱ፥ ህልውናው፥ አምላክነቱ፥ ጌትነቱና ክብሩ በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ታውቋል። ይህንንም ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን የተባለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር «ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ይትዐወቅ በፍጥረቱ በሐልዮ ወበአእምሮ ወከመዝ ይትአመር ኀይሉ ወመለኮቱ ዘለዓለም — ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፤ ከሃሊነቱ፥ የዘለዓለም ጌትነቱም እንዲህ ይታወቃል» ብሏል። (ሮሜ 1፥@፤ መዝ. 08፥1)

ስለዚህ «ሥነ ፍጥረት» የመጀመሪያው የእግዚአብሔር መገለጥ መሆኑን በዚህ እንገነዘባለን።

 

3. አስተርእዮ በዓለመ መላእክት

የሥነ ፍጥረትን ምሥጢር አምልቶ አስፍቶ የጻፈው ኤጲፋንዮስ የተባለው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ አክሲማሮስ በተባለው መጽሐፉ እንደገለጸው፥ ጌታ በመጀመሪያ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ለባውያን ነባብያን ሁነው የተፈጠሩ ቅዱሳን መላእክት ናቸው። ጌታ እነርሱን ፈጥሮ ተሰውሯቸዋል።

ትጉሃን መላእክትም በአእምሮ በለብዎ ተፈጥረዋልና፥ ማን ፈጠረን? ከወዴትስ መጣን? እያሉ ሲመራመሩ፥ አቡሃ ለሐሰት የተባለው ሐሰተኛው መልአክ ድምፃቸውን ሰምቶ ወደላይ ቢያዳምጥ የሚሰማው ድምፅ ቢያንጋጥጥም የሚያየው ገጽ ስለአጣ እኔ ፈጠርኳችሁ … በማለት ለማሳሳት ሲሞክር መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል «አምላካችንን እስከምናገኘው ድረስ በያለንበት እንቁም (እንጽና)» ብሎ አጽንቷቸዋል። በዚህ ጊዜ አምላከ ብርሃን እውነተኛው የብርሃን ጌታ እግዚአብሔር በብርሃን ተገልጾላቸዋል። «ወውእቱ ብርሃነ ኮኖሙ ጥበበ ወአእምሮ እንዳለው ሊቁ … በዚህ ብርሃን አንድነቱን ሦስትነቱን ገልጾላቸው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር … ብለው አመስግነውታል። (መቅ.ወን. አክሲማሮስ፥ ሥነ ፍጥረት)

 

4. አስተርእዮ በዘመነ አበው

ጌታ በዘመነ አበው በየዘመኑ ለአባቶቻችን በልዩ ልዩ ራእይ ተገልጿል። ይኸውም በገሃድ፥ በራእይ በሕልም በልዩ ልዩ አምሳል መገለጹን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ። ለማስረጃም፦

  • ለአባታችን ለአዳም በበደለ ጊዜ ለዘለፋ፥ ንስሓ በገባ ጊዜ ለውሂበ ተስፋ መገለጹ፥ (ዘፍ. 3፥9፤ መጽሐፈ ቀሌምንጦስ)
  • ለአቤል መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ መገለጹ (ዘፍ. 4፥4)፥ ለሄኖክ ወደ ደቂቀ ሴት በላከው ጊዜ መገለጹ፥ (ሄኖ. 4፥$9)
  • ለኖኅ ቅድመ ማየ አይኅ መርከብ እንዲሠራ ባዘዘው ጊዜ፥ ድኅረ ማየ አይኅ ኖኅ መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ መገለጹ፥ (ዘፍ. 6፥03፤ 7፥1፥ 8፥@1፥ 9፥1፥ @2፥04)
  • ለአብርሃም በተደጋጋሚ መገለጹ፤ ይልቁንም በአምሳለ እንግዳ በቤቱ (በድንኳን) ማረፉ፥ (ዘፍ. 02፥1፤ 7፤ 05፥1፤ 08፥#3)
  • ለይስሐቅ መገለጹ፥ (ዘፍ. @6፥@4፤ ለያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ መገለጹ በመጽሐፍ ቅዱስ የተመከረ ሐቅ ነው፥ (ዘፍ. @8፥02-05፤ #2፥#)

ቀደምት አበው እግዚአብሔር አምላክ በልዩ ልዩ ራእይ፥ ሕልም፥ አምሳል እየተገለጸላቸው ያለ ምንም መምህር እርሱን ሲያመልኩ ኑረዋል። ድምፁን ሰምተዋል፤ ቃል በቃልም ተነጋግረዋል።

 

5. አስተርእዮ በዝመነ መሳፍንት

ከዘመነ አበው ቀጥሎ ያለው ዘመነ መሳፍንት ይባላል። ጌታ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ምድር ሲወጡ ጀምሮ መንፈሳዊ ምግብናውን ለካህን፥ ሥጋዊ አስተዳደሩን ለመስፍን ሰጥቶ፥ ካህን ሲሞት ካህን፥ መስፍን ሲሞት መስፍን እየተካ ለብዙ ዘመናት መርቷቸዋል። በዚያ ዘመንም በተለያየ ራእይ በየዘመኑ እየተገለጸላቸው ሲመራቸውና ሕጉን፥ ትእዛዙን ሲገልጽላቸው ኑሯል። ለዚህ ማስረጃ በመጠኑ ለማሳየት ያህል፦

  • ለመጀመሪያው መስፍንና ሊቀ ነቢያት ሙሴ በተለያየ ጊዜ፥ በተለያየ ራእይ መገለጹ፥ (ዘፀ. 3፥1-07፤ 09፥@፤ #4፥@8)
  • ለኢያሱ፥ (ኢያ. 1፥1)
  • ለጌዴዎን፥ (መሳ. 6፥@3፤ 7፥2-0)
  • ለዮፍታሔ፥ (መሳ. 01፥@9)
  • ለሳሙኤል፥ (ሳሙ. 3፥4) … ለመሳሰሉት ሁሉ መገለጹን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ።

6. አስተርእዮ በዘመነ ነገሥት

ከዘመነ መሳፍንት ቀጥሎ ያለው ዘመን፥ ዘመነ ነገሥት ይባላል። በዚህ ዘመን፥ ንጉሠ ነገሥት፥ እግዚአ አጋእዝት፥ መኰንነ ኵሉ ፍጥረት የተባለው አምላካችን እግዚአብሔር በልዩ ልዩ መገለጥ ታይቷል። ይኸውም፦

  • ሥርወ መንግሥት ለተባለው ለንጉሥ ዳዊት መገለጡ፥ ይህ ልበ አምላክ የተባለው ነቢዩና ንጉሡ ዳዊት «ዘልፈ እሬእዮ ለእግዚአብሔር ቅድሜየ ውእቱ በኵሉ ጊዜ እስመ በየማን ውእቱ ከመ ኢይትሀወክ ለዓለም — ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ በቀኜ ነውና አልተውክም» በማለት እግዚአብሔር የተገለጠለት መሆኑን ገልጿል፥ (መዝ. 05፥8)
  • ለጥበበኛው ንጉሥ ለሰሎሞን መገለጹ፥ (ነገ.ቀዳ. 3፥5)
  • ለሌሎችም አበው ቀደምት ነገሥት በየጊዜው በገሃድ፥ በራእይ፥ በሕልም፥ በረድኤት፥ በተአምራት በመሳሰለው ሁሉ ተገልጧል።

7. አስተርእዮ በዘመነ ነቢያት

አስተርእዮ በዘመነ ነቢያት የሚለው ንኡስ ርእስ እጅግ ብዙ መጠነ ሰፊ ዳሰሳ የሚያስፈልገው ነው። ምክንያቱም ጌታ ለቅዱሳን ነቢያት በየዘመናቸውና በየጊዜያቸው በተለያየ ምሳሌ ያልተገለጸለት ነቢይ የለም። የጻፉትም እርሱ የገለጸላቸውንና ያናገራቸውን ነው። በዚህ ጽሑፍም በመጠኑ ለማሳየት ያህል፦

  • ልዑለ ቃል ለተባለው ነቢይ ለኢሳይያስ (ኢሳ. 6፥1-7)፥
  • ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለመረጠው ለነቢዩ ኤርምያስ፥ (ኤር. 1፥4-9)
  • ለነቢዩ ሕዝቅኤል በፈለገ ባሕር፥ (ሕዝ. 1፥1-@8) …
  • በባዕድ ሀገር ሁኖ አምልኮቱን አጽንቶ ለኖረው ዳንኤል፥ (ዳን. 7፥9)

በመሳሰለው ሁሉ በየጊዜው ለወዳጆቹ ተገልጿል።

ይህ ሁሉ አስተርእዮ የተስፋ፥ የረድኤት፥ የተአምራት፥ የትንቢት፥ የራእይ፥ የሕልምና የመሰለው አስተርእዮ ነው። ዋናውና አማናዊው አስተርእዮ የተስፋውና የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ በዘመነ ሥጋዌ የተደረገው አስተርአዮ ነው።

 

8. አማናዊ አስተርእዮ በዘመነ ሥጋዌ

«እግዚአብሔር እግዚእ አስተርአየ ለነ ግበሩ በዓለ በትፍሥሕት በኀበ እለ ያስተሐምምዎ … ጌታ እግዚአብሔር ተገለጸለን፥ በዓልን በደስታ አድርጉ …»  በማለት ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረው፥ የእግዚአብሔር መገለጥ በብሉይ ኪዳን ምን እንደሚመስል፥ ማለትም በረድኤት፥ በተስፋ ድኂን፥ በምሳሌ፥ በትንቢት፥ በራእይ፥ በሕልም፥ በገሃድ … በመሳሰለው ሁሉ እንዴት እንደተገለጸ በመጠኑ አይተናል። (መዝ. )08፥@7)

ይህ ሁሉ በተስፋ ሲጠበቅ የነበረው ጊዜ ሲደርስ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ፤ ይህንም ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን የተባለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፦ «ወአመ በጽሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት ወገብረ በሕገ ኦሪት — ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ላከ፥ ከሴትም ተወለደ፤ በኦሪት የታዘዘውንም ፈጸመ» (ገላ. 4፥4፤ ኤፌ. 1፥0)

ይህ በቀጠሮው ጊዜ የተፈጸመው ተስፋ አበው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ከሰማይ መላእክትን፥ ከምሥራቅ እጅ መንሻ የሚያቀርቡ ነገሥታትን፥ ከቅርቡ መንጋቸውን የሚጠብቁ ኖሎትን (እረኞችን) በአንድ አሰባስቦ በተአምራት በብርሃን ስቦ አንድ መዝሙር እንዲዘምሩ አደረገ። (ሉቃ. 2፥6)

በዚህ ጊዜ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት «ይገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ፥ ነገሥተ ተርሴስ ወደሰያት አምኃ ያበውኡ ነገሥተ ሳባ ወዐረብ ጋዳ ያመጽኡ ወይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ ነገሥተ ምድር — በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ፥ የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የሳባና የዐረብ ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀርባሉ፤ ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል» ሲል የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ (መዝ. &1፥9-01፤ ማቴ. 2፥1-02)። ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያውም የዚሁ አማናዊ አስተርእዮ በረከት ተካፋይ ሁናለች። ቀድሞ ንግሥተ ሳባ ለሰሎሞን ንጉሥ ገጸ በረከት እንደሰጠችው እውነተኛው ንጉሥ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜም የኢትዮጵያው ንጉሥ ባዜን እጅ መንሻውን ለጌታ ካቀረቡት ነገሥታት አንዱ እንደነበረ አበው ሊቃውንት በትርጓሜ ዳዊት ገልጸዋል። (መዝ. 71፥9-11)

 

9. አስተርእዮ በፈለገ ዮርዳኖስ

እንዲህም አድርጎ «በበሕቅ ልህቀ በ# ክረምት በዮርዳኖስ ተጠምቀ …» እንዲል በየጥቂቱ አደገ፤ # ዓመት ሲሞላው በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠመቀ።

ኮከበ ሊቃውንት፥ ጥዑመ ልሳን ቅዱስ ያሬድ ይህን አስተርእዮ ሲሰብክ «ሐዳፌ ነፍስ ለጻድቃን ቀተስፋ ቅቡጻን ክርስቶስ አስተርአየ ውስተ ዓለም እምድንግል ተወልደ ክሡተ ኮነ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ ከዊኖ ሰብአ በዮርዳኖስ ተጠምቀ — ነፍሳትን የሚያሻግር፥ ተስፋ ለቆረጡት ተስፋቸው ክርስቶስ በዓለም ተገለጠ፤ ከድንግል ተወለደ፥ ለዘመዶቹ ሲታዘዘ ተገልጦ ታየ፥ ሰው ሁኖ በዮርዳኖስ ተጠመቀ» በማለት ይሰብከዋል። (ድጓ ዘዘመነ አስተርእዮ)

ስለዚህ በፈለገ ዮርዳኖስ ስለተፈጸመው አማናዊ አስተርእዮ ነቢዩ ዳዊት አስቀድሞ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት «ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ — ባሕርም አይታ ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ» በማለት ዘምሯል። (መዝ. )03፥3)

የባሕረ ዮርዳኖስ ትንቢታዊ ምሳሌና ምሥጢራዊ ትርጒም ከዚህ አስቀድሞ በወጣው የጥምቀት መጽሔት በሰፊው ስለተገለጸ ከዚህ ላይ አልፈዋለሁ።

 

ማጠቃለያ

ከላይ በርእሱ እንደተገለጸው ታላቁ የዜማ አባት ኢትዮጵያዊው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ይህ የመገለጥ በዓል እንደሚከተለው ገልጾታል «አስተርአየ ዘኢያስተርኢ ኮነ እሙነ አስተርእዮቱ ለመድኀኒነ ክርስቶስ  — የማይታየው ታየ፤ የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መታየቱ እውነት ሆነ። በማለት ስለዚህ ታላቅ የመገለጥ በዓል ዘምሯል (ድጓ ዘአስተርእዮ)፤ ይህንም እንዲሁ ከልቡናው ብቻ አቅንቶ አልተናገረም፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር መገለጥ የተጻፈውን መሠረት አድርጎ እንጅ።

ስለዚህ የአስተርእዮ (የመገለጥ በዓል) ከላይ በመጠኑ እንደተገለጸው አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፥ ምሳሌ ተመስሏል። ልበ አምላክ የተባለው ነቢዩ ዳዊትም ስለዚህ በዓል፦ «ርእዩከ ማየት እግዚኦ፥ ርእዩከ ማየት ወፈርሁ ደንገፁ ቀላያተ ማያት ወደምፃ ማያቲሆሙ — አቤቱ ውኃዎች አዩህ፥ ውኃዎችም አይተው   ሸሹ፤» ብሏል። ይህም በብሉይ በሙሴ ዘመን በባሕረ ኤርትራና በኢያሱ ዘመን በባሕረ ዮርዳኖስ የተፈጸመውን ድንቅ ተአምር የሚያስረዳ ሲሆን፤ በሐዲሱ ሲተረጐም ደግሞ ጌታ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የተፈጸመውን ድንቅ ተአምር ያስረዳል። (መዝ. &6፥06)

ሐዋርያውም እግዚአብሔር  ለምን (ስለ ምን) እንደተገለጸ ሲያስረዳ «ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስዐር ግብሮ ለሰይጣን … ስለዚህ ነገር የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ» ብሏል። (1ዮሐ. 3፥8)

ከዚህ ከሐዋርያው ትምህርት እንደምንረዳው ይህ የአስተርእዮ (የመገለጥ) በዓል፦

 

  1. ይህ በዓል እግዚአብሔር ወልድ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ በትሕትና ሲጠመቅ የታየበት የትሕትና በዓል ነው፥
  2. ይህ በዓል እግዚአብሔር አብ በደመና ሁኖ «የምወደው ልጄ ይህ ነው …» ብሎ ፍቅርን የሰበከበት የፍቅር በዓል ነው፥
  3. ይህ በዓል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ወርዶ ሲቀመጥ የታየበት፥ በዚህ ዕለት በቅንነት ላገለገለ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በሰፊው የሚገኝበት፥ … በአጠቃላይ ምሥጢረ ሥላሴ በገሃድ የተገለጠበት የነገረ ድኅነት መሠረት፥ የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር የሆነችው ምሥጢረ ጥምቀትን ጌታ በተግባር የፈጸመበት (ያስተማረበት) ዕለት ስለሆነ በዓሉ እጅግ ታላቅ በዓል ነው።

በዓለ አስተርእዮ የመገለጥ በዓል ስለሆነም ታቦተ ሕጉ ከቤተ እግዚአብሔር ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርዶ፥ በካህናት በሊቃውንት፥ በመዘምራንና በምእመናን ታጅቦ ከባሕረ ጥምቀቱ ሲደርስ በተዘጋጀለት ድንኳን ያድራል።

ለበዓሉ የሚገባው አገልግሎት ሲፈጸም አድሮ ቅዳሴ ከተቀደሰ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱ ይባረካል። ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ሕዝቡ ከተጠመቀ በኋላ ታቦተ ሕጉ በከፍተኛ ድምቀት በያሬዳዊ ዜማና በልዩ ልዩ አገልግሎት ታጅቦ ወደ መንበረ ክብሩ ይመለሳል።

በዚሁ በዘመነ አስተርእዮ ከሚከበሩ በዓላት መካከል የእመቤታችን የዕረፍቷ በዓል «አስተርእዮ» ይባላል።

 

በጥምቀቱ ውኃን ለጥምቀታችን የቀደሰልን አምላካችን ይክበር ይመስገን፤ አሜን።

 

መጋቤ ምሥጢር ፍሬ ስብሐት ዱባለ

የሊቃውንት ጉባኤ ም/ሰብሳቢ

ጥምቀት በተዋሕዶ

መግቢያ

“ወአገሐዶ ዮሐንስ ወአጥመቆ በውስተ ዮርዳኖስ ተመከረ በገዳም ወተዐውቀ ከመ እግዚአብሔር ውእቱ’ ‘ዮሐንስ ገለጠው ፤ በዮርዳኖስም አጠመቀው ፤ በገዳም ተፈተነ ፤ እርሱም የባህርይ አምላክ አንደ ሆነ ታወቀ” (ሃይ.ም.7ገጽ 30)

ጥምቀተ ክርስቶስ ለምንና እንዴት እንደ ሆነ ቅዱስ ሄሮኔዎስ “ዮሐንስ ገለጠው ፤ በዮርዳኖስም አጠመቀው….” በማለት “ጥምቀት” የመገለጥ በዓል እንደ ሆነና በሥጋ የተገለጠው ወልደ እግዚአብሔር ወልደ እጓለ እመሕያው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን በመገለጡ ተዋናይና ምሥክር የሆነው ደግሞ መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ነው። ጥምቀት በግእዙ ተጠምቀ ተጠመቀ ፤ ተዘፈቀ ፤ ብቅ ጥልቅ አለ ማለት ነው። በግርከኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎችም “አጲፋንያ” “ኤጲፋኒ” (epiphaneia/ἡ ἐπιφάνεια/Epyphany) የሚለው ቃል መገለጥ ፤ መታየት ማለት ነው። ትንቢቱ ሲፈጸም ፤ ጊዜው ሲደርስ የተገለጠው ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ:- “ወአንሰ ኢያአምሮ ዳእሙ ከመ ያእምርዎ እስራኤል በእንተዝ መጻእኩ አነ ከመ አጥምቅ በማይ’ ‘እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ”(ዮሐ.1:31) ይላል። የጥምቀት ክብረ በዓልን ዐውድ ስንመለከት የአደባባይ በዓልና ከስሙ ትርጉም ጋር የሚዛመድ ነው። ጥምቀት ዘርፈ-ብዙ ምሥጢራት የሚተነተኑበት ኃይለ ቃል ሲሆን በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው ግን “ጥምቀት በተዋሕዶ” በሚል ርእስ በሥሉስ ቅዱስ የተገለጠውና ለአማንያን የተሰጠው “አንድነት”ን ብቻ የሚመለከት ይሆናል።

 

1. የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጥምቀት

ሥላሴ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የሦስትነት ስም ነው። በቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ አግዚአብሔር አምላክ ስነ ፍጥረትን መፍጠር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአንድነትና በሦስትነት ሲጠራ አንደ ነበረ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አስረግጠው ይናገራሉ። ለምሳሌ “እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” (ዘፍ.1:26) ፤ “እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” (ዘፍ.3:21) ሲል ከአንድ ቁጥር በላይ መሆኑን ሲያመለክት የሚከተሉት ጥቅሶች ደግሞ ሦስትነቱን ያረጋግጣሉ። “ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ ”(ዘፍ.18:1) የሚለውና “አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” (ኢሳ. 6፡3) ተብሎ የተጻፈው ነው።

በባህረ ዮርዳኖስ የታየው ምሥጢረ ሥላሴ ግን ልዩ መገለጥ ነው፡፡ ይኽም ወልድ በተለየ አካሉ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ ፤ አብ በደመና ሆኖ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ብሎ ሲናገር ፤ መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲቀመጥ መታየቱ ነው። “ወወረደ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌሁ በሥጋ በርእየተ ርግብ…..መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ” (ሉቃ.3:22) እንደሚለው በተለየ አካል ፤ በተለየ ስም ፤ በተለየ ሥፍራ መገለጡ በጥምቀተ ክርስቶስ አንድነቱን በሦስትነት ፤ ሦስትነቱን በአንድነት የሚያሳይ ዕፁብ ድንቅ ምሥጢር ነው፡፡

ይኽ የሦስትነትና የአንድነት መገለጥ እስራኤል ዘሥጋ እንዲያውቁትና ከነርሱ ወገን ከሆነችው ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ፤ በተዋሐደው ሥጋ መከራ መስቀልን ተቀብሎ የሰው ልጅን ከዲያብሎስ ግዞት ነጻ የሚያወጣው እርሱ እንደ ሆነ የአብን ምሥክርነት ሰምተው እንዲያምኑበት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ለሊሁ ወረደ መንፈስ ቅዱስ ሠለስቲሆሙ እለ እሙንቱ እለ ይከውኑ ሰማእተ›› (ድጓ ዘጥምቀት) አንዲል፡፡

የሥላሴ ሦስትነትና አንድነት በምእመናን ሕይወት ጥልቅ ትርጉም አለው። ጥምቀተ ክርስቶስ እኛ ብዙዎች ስንሆን በእርሱ አንድ ሕዝብ መሆናችንን ፤ ልጅነት የምታሰጥና የአንድነታችን ምሥጢር የሆነችውን ጥምቀት በጥምቀቱ የመሠረተልን መሆኑን የምንማርበት ነው። “…ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን” (ሮሜ.12:5)። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ” (ዮሐ.17:23) በማለት በሥሉስ ቅዱስ ያለው አንድነት በክርስቲያኖችም ሕይወት የሚታይ መሆኑን አስተምሮናል።

 

2. የመለኮትና የትስብእት አንድነት በጥምቀት

በናዝሬት ተፀንሶ ፤ በቤተልሔም የተወለደውና በናዝሬት ያደገው የአብ ልጅ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ፅንሰቱ በተአምር ፤ ልደቱና እድገቱ እንደ ማንኛውም የሰው ልጅ ሆኖ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለጠባቂዋ ለጻድቁ ዮሴፍ እየታዘዘ ፤ በልጅነቱ ተአምራትን እያደረገ ማደጉን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ ሠላሳ ዓመት ሲሆነው ለእስራኤል ይገለጥ ፤ ዘንድ ፤ የተቆጠረው ሱባኤና የተነገረው ትንቢትም እንዲፈጸም ራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ ‹አፍቂሮ ኪያነ መጽአ ኃቤነ ዘነቢያት ሰበኩ ለነ በዮርዳኖስ ተጠምቀ›› እንዲል። የክርስትና ሃይማኖት እውነተኝነትን ከሚያረጋግጡት መካከል ኢየሱስ ክርስቶስ ገና በማኅፀነ ማርያም ሳይፀነስ ከቅድስት ድንግል  በቤተልሔም አንደሚወለድና በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ አስቀድሞ በቅዱሳት መጻሕፍት መረጋገጡ ነው።

ስለዚህ ትንቢተ ነቢያት፤ የዘመናት ምኞትና የአበው ተስፋ ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡ የተጠመቀው ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ በተዋሕዶ ነው፡፡ የመለኮትና የትስብእት ተዋሕዶ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ድል የተነሣበትና የሰው ልጅ የከበረበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ የክርስቶስ በፍጹም ተዋሕዶ መገለጥ የውሉደ ጥምቀትን አንድነት ፤ በኃጢአት ወድቆ በክርስቶስ ሞት የተነሣው ሰው በአግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ሥፍራ ያሳየበት ነው። ቅዱስ ቄርሎስ “ወረደ ከመ ያዕርገነ ለነ ኀበ ሀገሩ አርያማዊ ኀበ ሀሎ አቡሁ’ ‘የባሕርይ አባቱ ካለበት ሰማያዊ ሀገሩ ያገባን ዘንድ እርሱ ወደ እኛ ወረደ” (ሃይ.አበው) እንዳለ የሰውን ልጅ ከወደቀበት ኃጢአት ለማንሳትና ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ እርሱ ወደ ምድር ወረደ። እኛን ሆኖ እኛን ለማዳን አካላዊ ቃል ሥጋን ገንዘብ አደረገ። ከቅድስተ ቅዱሳን ፤ ከንጽሕተ ንጹሐን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ፤ ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ በመወለዱ የሰው ልጅን አከበረ። “እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል ፤ የቃል ገንዘብ ለሥጋ ሆነ የሥጋ ገንዘብ ለቃል ሆነ” ብሎ ቅዱስ ቄርሎስ እንደ ተናገረ። ቅዱስ ሉቃስም “…እንዘ ዘመዱ እንከ ንሕነ ለእግዚአብሔር…እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን..” (የሐ.17:27-28) በማለት እግዚአብሔር አምላክ እኛን ከፈጠረበት ይልቅ እኛን ያዳነበት ምሥጢር እጅግ ታላቅ መሆኑን ያረጋግጥልናል።

 

3. የሕዝብና የአሕዛብ አንድነትበጥምቀት

በቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ ሕዝብ የተባሉት እስራኤል ዘሥጋ ሲሆኑ እነዚህም ሱባኤን የቆጠሩ አበው ፤ ትንቢትን የተናገሩ ነቢያትና ሕዝበ እግዚአብሔርን የመሩ ነገሥታት ከመካከላቸው የተገኙ የአብርሐም ልጆች ናቸው። አሕዛብ የተባሉትም ከዚህ ታሪክ ውጭ ሆነው በአምልኮ ባዕድ ይኖሩ የነበሩት ናቸው። ሁለቱም በጥምቀት ዳግም ተወልደው የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች ለመሆን በቅተዋል። “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” (ዮሐ.3:3) ይላልና። በጥምቀተ ክርስቶስ የሁለቱም የዕዳ ዳብዳቤአቸው ተደምስሶላቸዋል። የሁለቱም የባርነት ታሪክ ተሽሮ በአዲስ ምዕራፍ በወልደ እግዚአብሔር በማመንና በአንዲት ጥምቀት በመጠመቅ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነዋል። “ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና” (ሮሜ.3:22) በማለት ከክርስትና በኋላ አንድነት እንጂ ልዩነት እንደሌለ አረጋግጦልናል።

በዘመነ አሪት ሕዝብና አሕዛብ የሚለዩበት ልዩ መታወቂያ “ግዝረት” ነበረ። “የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል” (ዘፍ.17:11)። በዘመነ ሐዲስ ግን ግዝረትን ተክቶ ለክርስቲያኖች መለያ ፤ ለመንግሥተ ሰማያት መግቢያ መሥፈርትና የመዳን ምልክት የሆነው “ጥምቀት” ነው። “ያመነ የተጠመቀም ይድናል” (ማር.16:16) እንዲል። ጥምቀት እንደ ግዝረት የአብርሐም ዘሮችን ብቻ ከአሕዛብ የሚለይ ድምበርና በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል የቆመ የቃል ኪዳን ምልክት ሳይሆን ሕዝብና አሕዛብን አንድ መንጋ አድርጎ ለእግዚአብሔር መንግሥት የመግቢያ ብቃት ሆኖ የሚያገለግል ነው። ይኽ በጥምቀተ ክርስቶስ ያገኘነው ጥምቀተ ክርስትና ከአለም መለያችን ብቻ ሳይሆን የአንድነታችን ማሳያ “አረቦን” ነው። “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና” (ገላ.3:27) ይላል።

የእግዚአብሔር ቃል የሚያረጋግጥልን ክርስቲያን ከየትኛውም ብሔር ፤ ነገድ ፤ ቋንቋ ፤ ልማድና ሥርዓት ይምጣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ የመንግሥቱ ዜጋ ከሆነ በኋላ ባለቤት እንጂ ባዕድ አይደለም። የበላይነትም ሆነ የበታችነት ሥሜት አይኖረውም። አንዱን ዝቅ ሌላውን ከፍ አድርጎ የሚያይበት አለማዊ ዓይንም የለውም። ይልቁንም ለክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን አንድ ክፍል ሆኖ የተገነባ ስለ ሆነ በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካሉት ሁሉ ጋር አንድ ነው። ስለዚህ በክርስቲያኖች መካከል ሊኖር የሚገባው አንድነትና የማይፈታ ምሥጢራዊ ትስስር በጥምቀት ዳግም ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ያገኘነው አምላካዊ ስጦታ እንጂ በጥቅምና በጊዜ የተገደበ ፤ በጥላቻና በፖለቲካ የሚዘወር ሕይወት አይደለም።

 

4. በክርስቶስ ሞት አንድነት በጥምቀት

ብርሃነ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እኛ እኛን ሆኖ የእኛን ኃጢአት በእንጨት ላይ ተሸክሞ የእኛን ሞት ከሞተው ከክርስቶስ ሞት ጋር እንደምንተባበርና ስለ እኛ የሆነውን መከራ-መስቀል የእኛ የምናደርግበትን ምሥጢር እንዲህ ሲል ይናገራል። “ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” (ሮሜ.6:4)። ሐዋርያው በዚህ ቃል የክርስቶስን ቤዛነት ለማሳየት “ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ” (1.ጢሞ.2:6) በማለት ጥምቀትና ሞትን በምሳሌነት ተጠቅሟል። በሞትና በጥምቀት ምሳሌም ክርስቲያኖች ስለሚያገኙት ድኅነትና ሰማያዊ በረከት አስተምሮናል። ይኽን እጅግ ጠቃሚና አስገራሚ ምሳሌ በጥቂቱ ዘርዘር አድርገን እንመልከት:-

4.1  የሞቱ ምሳሌ በጥምቀት

ጥምቀት ለክርስቶስ ሞትና መቃብር ምሳሌ ሆኖ መቅረቡ ሰው ሲጠመቅ ራቱቱን ሆኖ መጠመቁና ሲሞትም ራቁቱን ሆኖ መገነዙ ነው። ሰው ያለውን ሁሉ ትቶ ራቁቱን ወደዚህ ዓለም እንደ መጣ እንዲሁ ራቁቱን ወደ አለመኖር ይመለሳል። ከእግዚአብሔር ጸጋና ክብር የተራቆተውን የሰው ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ክርስቶስ ዕርቃኑን በመስቀል ላይ ዋለ። ወደ እርሱ  ክብር ሊያገባን በእኛ ሥፍራ እኛን ተክቶ እርሱ ተገኘ። “ዘዚአነ ሞተ ነሥአ ወእንቲአሁ ሕይወተ ወሀበነ” (ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ) እንዳለ የእኛን ሞት እርሱ ሞቶ የእርሱን ዘለዓለማዊ ሕይወት ሰጠን። ይኽን ዘለዓለማዊ ሕይወት ለማግኘት የሰው ልጅ ሁሉ ክርስቶስን በማመን ፤  አምኖ በመጠመቅ የክርስቶስን ሞት የራሱ ማድረግ ነው። “ከሞቱ ጋር መተባበር” የሚለውም ክርስቶስ የከፈለለትን መከራ-መስቀል አምኖ መቀበልና በክርስቶስ ያለውን ሕይወት ወርሶ መኖር ማለት ነው። “ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው” (ቲቶ.3:6)

4.2 የአዲስ ሕይወት ምዕራፍ በጥምቀት

ከሞት በኋላ ሌላ አዲስ ሕይወት አዲስ ዓለም አንዳለ ሁሉ ከጥምቀት በኋላ ሌላ አዲስ ሕይወት ፤ አዲስ ምዕራፍ ነው። ሐዋርያው ይኽን ሲያረጋግጥልን “እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” ይላል። መጠመቅ ዳግም መወለድ የሆነውም ለዚህ ነው። “ወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ” እንዲል። ሰው አምኖ ሲጠመቅ አሮጌው ማንነቱን ትቶ ወደ አዲስ ማንነት ስለሚመጣ አዲስ ሕይወት ነው። ጥምቀት ኃጢአትን ስለምታስተሠርይ ኃጢአተኛው ከኃጢአት እሥራት ተፈቶ አሁን እንደ ተወለደ ሕጻን አዲስ ምዕራፍ የሚጀምርበት ነው። በመሆኑም ጥምቀት አዲስ ሕይወት ፤ የለውጥ ምዕራፍ ስለ ሆነ ስንጠመቅ አዲስ ስም ፤ አዲስ ዜግነት ይሰጠናል።

4.3 የማኅበረ ምእመናን አንድነት በጥምቀት

ጥምቀት ለአንድ ምእመን በእግዚአብሔር መንግሥት ፤ በክርስትና ሕይወት የመኖር ዋስትናና ሁለንተናዊ መገለጫው ነው። የክርስቶስን ሞት የራሱ ለማድረግና በክርስቶስ ሞት ምክንያትም በአዲስ ሕይወት ለመመላለስ በክርስቶስ አምኖ መጠመቅ የግድ በማስፈለጉ “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል” (ዮሐ.3:7) ብሎ አስተምሮናል። ጥምቀት አንድን ምእመን በክርስቶስ ሞት በመተባበር ለአዲስ ሕይወት የምታበቃ ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የመግቢያ በር ቁልፍ ስትሆን በሌላ መልኩ የማኅበረ ምእመናንም የአባልነት/የአድነት መታወቂያ ፓስፖርት ናት። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ፤ ክርስቶስም የቤተ ክርስቲያን ራስዋ ሲሆን እያንዳንዱ ምእመን የክርስቶስ አካል በሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገነባ አንዱ ክፍል ነው። ስለሆነም የተጠመቁት ሁሉ ከአንዱ መንፈስ ቅዱስ የተወለዱ በመሆናቸው የክርስቶስ ማኅበር ናቸው። “ማኅበራኒሁ ለክርስቶስ” እንዲል። ቅዱስ ዮሐንስ ስለዚህ ኅብረት ሲናገር “እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው” (ዮሐ.1:3) ይላል።

በዘመናችን ክርስቲያን ክርስቲያን ወንድሙን ሲያሳድድ ፤ የእርሱ ባልሆነው የአረማውያን ጠባይ ወገኑን አፈናቃይና ገዳይ ሆኖ መታየቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው። በውኑ በዚህ ድርጊት የተሠማሩት ወገኖች በሃይማኖቱ ስም የሚጠሩ ወይስ በሃይማኖቱ የሚኖሩ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ግድ ይሆናል። በሃይማኖት ስም መጠራትና ሃይማኖትን መኖር የተለያዩ ናቸውና። ሐዋርያው “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ” ይላል። የክርስትና ሃይማኖት የፍቅር ሃይማኖት እንጂ የመገፋፋት ፤ የመጠላላት ሃይማኖት አይደለም። የክርስትና ሃይማኖት መሠረቱ ክርስቶስ ፍቅር ስለሆነ የምንወደድበት ማንነት ሳይኖረን እርሱ እኛን ወዶ ወደ እኛ መጣ። ‹‹አፍቂሮ ኪያነ መጽአ ኃቤነ ዘነቢያት ሰበኩ ለነ በዮርዳኖስ ተጠምቀ›› ይላልና። በሃይማኖት የሚኖሩት ክርስቲያኖችም መታወቂያቸው ፍቅር እንደ ሆነ እርሱ ባለቤቱ አስተምሮናል። “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” (ዮሐ.13:35)።

 

2. ማንነትና እኩልነት በጥምቀት

ከጥምቀት ትሩፋት አንዱ ጥምቀት የማንነትና የእኩልነት ማረጋገጫ ማኅተም ሆኖ መሰጠቱ ነው። “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና”(ገላ.3:27-28) ይለናል። ውሉደ ጥምቀት በክርስቶስ የክርስትናን ማንነት የለበሱ የቀድሞ የዝቅታና የከፍታ ማንነታቸውን አስወግደው በእኩልነት የሚያምኑና በእኩልነት የሚያመልኩ ናቸው። አንዱ ሌላውን ባርያ ፤ ጨዋ ብሎ አያገለውም። ሁለቱም በክርስቶስ አካል ውስጥ ሥፍራ ተሰጥቶአቸው በክርስቶስ ክቡር ደም የከበሩ ስለሆኑ በእነርሱ ዘንድ የክብር ፤ የማንነት ጥያቄ አይነሳም። በክርስቶስ አካል ውስጥ ሆኖ የበታችነት ወይም የባዕድነት ሥሜት የሚሰማው ምእመንም እንዳይኖር ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም” (ኤፌ.2:19)።

ይኽን የከበረና የታወቀ የክርስትና አስተምህሮን ገንዘብ ካደረግንና በሃይማኖት የምንኖረው ከሆነ ጥላቻን ፤ ግፍን ፤ መለያየትን ከመሐላችን ልናርቅ ይገባል። በክርስትና ሕይወት “አንድነት” ሲባል አንዱን በአንዱ መጨፍለቅና መዋጥ ሳይሆን “አንድነት” ማለት የእኩልነት መብት ፤ የማንነት ክብር የሚረጋገጥበት የጋራ ዋስትና የሆነ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ይኽን “አንድነት” የነገድ ፤ የቋንቋ ፤ የጾታ ልዩነት አይገድበውም። የተጠራነው ከተለያየ ነገድና ቋንቋ ሲሆን ማንም በማንነቱ የተለየ ብልጫ ሳይኖረው በክብር ፤ በእኩልነት የሚታይበት ማኅበረ ክርስቶስ ነው። “…..ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው..” (ራዕ.5:10) ይላልና። ክርስቲያኖች ቋንቋንና ነገድን መሠረት ባደረገ ፖለቲካ መጠፋፋት ማለት የተዋጀንበትን የክርስቶስን ክቡር ደም ከንቱ ማድረግ ማለት ነው። አኮ በወርቅ ኃላፊ ዘተሳየጠነ አላ በደሙ ክቡር ቤዘወነ ወለደነ በጥምቀቱ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ የገዛን አይደለም፥ በከበረው ደሙ አዳነን እንጂ ቅድስት ለሆነች ቤተ ክርስቲያንም አካል እንሆን ዘንድ በጥምቀቱ ወለደን እንዳለ (ቅዱስ ያሬድ፤ 1.ጴጥ.1:18)።

 

ማጠቃለያ

“ጥምቀት በተዋሕዶ” በሚል ርእስ በመጠኑ ያየነው በጥምቀተ ክርስቶስ የተገለጠውን የሥሉስ ቅዱስ ሦስትነትና አንድነት ፤ የትስብእትና የመለኮት በተዋሕዶ መገለጥ ፤ የሕዝብና የአሕዛብ አንድነት እንዲሁም ጥምቀት የክርስቶስን ሞት መሞትና በአዲስ ሕይወት መመላለስ ፤ የማንነትና የእኩልነት መብት ማረጋገጫ ማኅተም መሆኑን ነው። ጥምቀተ ክርስቶስ ወደ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ለምታስገባን ጥምቀተ ክርስቲያን መሠረት መሆኑንም በጥቂቱ ለመገንዘብ ሞክረናል። በአንዲት ሃይማኖት ፤ በአንዲት ጥምቀት አንድ እንሆን ዘንድ ስለ እኛ የተጠመቀው አምላክ በአንድነት ለአንድነት ጠርቶናል።

በእውነት ጸድቀን ፤ በሃይማኖትና በምግባር አብበን የጽድቅን ፍሬ እንድናፈራ ዐፀደ ወይኑ በሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተክሎናል ፤ የሕይወት ውኃ የሆነውን ቅዱስ ቃሉን እያጠጣን በዓለሙ የክፋትና የፈተና ሐሩር እንዳንጠወልግ ለዘለዓለማዊ መንግሥቱ ይጠብቀናል። ‹‹እግዚእ ክርስቶስ ለሊሁ ዘተከለነ ወሰቀየነ  በማይ መንፈሳዊ ማእከለ ተኩላት›› (ቅዱስ ዮሐንስ ፈወርቅ) እንዲል። ስለሆነም ራሳችንን ከዚህ ዓመጻና ሸንገላ ከሞላበት ዓለም ፤ መጠፋፋትን ጥበቡ ካደረገው ከዚህ ክፉ ትውልድ ለመዳን ፤ ዓለሙንም  ለማዳን እንድንችል ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን!

 

“ትምህርተ ጥምቀት፣በክልኤ ኪዳናት”

ኪዳን፦ የቃሉ ትርጕም የፍቅር የስምምነት፣ የአንድነት መሐላ፣ ከጥፋት የሚጠብቅ ከለላ& ሰውና እግዚአብሔርን የሚያገናኝ የተጻፈ ውል፣ሰላማዊ ሕግና ትምህርት ማለት ነው ፡፡(ኪ.ወ.ክ)

ክልኤ ኪዳናት፦በሚል የተጠቀሱት ሁለቱ ቃላት ደግሞ የሰው ልጅ ክፉውንና በጎውን ለይቶ በማወቅ፣ ከክፉው በመራቅ እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲኖር፣ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ኑሮው እንዳይናጋ የሚያስተምሩት ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ናቸው፡፡

እነዚህም ኪዳናት ከአንዱ እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት ለተለያየ ሕዝብ የተሠጡ፣ሁለንተናዊ ሐሳቡን የያዙና ወሰን የሌለው ፍቅሩን የሚገልጡ ራሳቸውን ችለው በተስፋ የቆሙ፣በመሐላ የጸኑ መሆናቸው ግልጽ ነው ፡፡

ሁለቱም በጥላና በአካል ፣በጊዜያዊና በዘላለማዊ፣በሥጋዊና በመንፈሳዊ ላይ የተመሠረተ ልዩነት ያላቸው ቢሆንም በየዘመናቸው የእግዚአብሔር ያልሆነውን ሕዝብ የእርሱ እንዲሆን ያደረጉና  የሚያደርጉ ኪዳናት ናቸው፡፡

የእርሱ ያልሆነው ሕዝብ በኪዳኑ አማካኝነት ሕዝቡ እንደሚሆን “ወእትካየድ ኪዳነ ምስለ ኩሉ ወእብሎ ሕዝብየ ለዘኢኮነ ሕዝብየ ወውእቱ ይብለኒ እግዚእየ ወአምላኪየ — ከሁሉም ጋር ቃል ኪዳንን  አደርጋለሁ ለሰባ ዘመናትና ከዚያም በፊት  ወገኔ ያልሆነውን ወገኔ እለዋለሁ እርሱም ጌታየና አምላኬ አንተነህ ይለኛል”  ተብሎ በነቢዩ ሆሴዕ .ተነግሯል ፡፡(ሆሴ -2$24)

በመሆኑም በምሳሌና በፍጻሜ ያላቸውን የትርጕም ይዘት ከልዩነታቸው ጋር የባዕድ (የግል) ምልከታ በሌለበት ከቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ሳንወጣ በንጽጽር ጠቅለል አድርገን እንመለከታለን ፡፡

ከርእሰ ትምህርቱ ጋር የሚገናኘውን ሐሳብ ብቻ በመለየት የምናብራራው ትምህርተ ጥምቀት በቤተ ክርስቲያናችን መተርጕማን እይታ ስምንት ወገን (ዐይነት) ሲሆን አራቱ ምሳሌያት፣አራቱ ደግሞ አማናውያት መሆናቸውን . ሐተታ ትርጓሜው ያመለክታል፡፡ (ትር.ወን.ማቴ 3፥3-7)

የምሳሌውም ሆነ የአማናዊው ጥምቀት መሰረተ ሐሳብ መንፃት ፣መለወጥ፣መተባበርና ወደ አዲስ ሕይወት መግባት የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡(ማር.1÷4-8፤ዮሐ.3÷25፤ሐ.ሥ.22÷16፤1.ቆሮ.1÷13)
አራቱ ምሳሌያትና አራቱ  አማናውያት ጥምቀታትም በየአርዕስታቸው ሲታዩ፦

  • የኖኅ መርከብ፣ (ዘፍ. 7፥17፤1ጴጥ3፥20-21)
  • . ባሕረ ኤርትራናደመናው ፣.(1ቆሮ 10፥1-2).
  • ግዝረት ፣ (ዘፍ17፥ 10)
  • ጥምቀተ ዮሐንስ፣(ማቴ 3፥4)
  • የጌታ ጥምቀት፣(ማቴ3፥16)
  • አንብዐ ንስሐ .፣
  • ደመ ሰማዕታትና ባሕረእሳት የሚሉት ናቸው፡፡

ከዚህ በላይ በስምንት አርዕስት የተገለጹት፣ከትርጓሜ ሐተታው የተገኙት የምሳሌያቱና የአማናዊው አስተምህሮ የክብር ስፍራውን እንደያዘ ሆኖ ለምሳሌያዊውና ለአማናዊው ጥምቀት ትንተና የበለጠ በሚቀርበው“ጥምቀት ሦስት ወገን ነው” በሚለው፣በሌላኛው የትምህርት አቀራረብ ማለትም ፦

  • ጥምቀተአይሁድ፣
  • ጥምቀተዮሐንስ፣
  • ጥምቀተ ክርስቶስበሚሉት ንዑሳን አናቅጽ ምሳሌያቱን በጥላነታቸው፣ አማናዊውን በአካልነቱ  እናያለን፡፡

ጥምቀተ አይሁድ፣ትምህርቱና የአፈጻጸም ሥርዓቱ፦

“ኀጥአ ኢታሕዩ…ኀጢአተኛውን ይቅር አትበል…ሕጉ የተሰጠበትን ተራራ ጫፍ እንዳትነኩ ተጠንቀቁ ተራራውን የነካ ፈጽሞ ይሞታል፡፡እንስሳ ወይም ሰው አይድንም„እያለ በሚያስጨንቅና በደልን በሚያበዛ ሁኔታ በተሠራው በመጀመሪያው ኪዳን (ሕግ).በሥጋ ሥርዓት ይፈጸም የነበረው ጥምቀተ አይሁድ ሥርየተ ኀጢአትን  ማሰጠት የማይችል በመሆኑ የሥጋ ርኩሰትን እንጂ የነፍስ እድፈትን አያነጻም ነበር ፡፡ (ዘጸ.19፥10-13፤ዕብ.9፥10)

ኦሪት በድን የዳሰሰ፣ መቃብር ያፈለሰ ሰው እስከ ሠርክ ርኵስ ነው ስለምትል ለአይሁድ የመንጻት ሥርዓት የሚጠቅሙ ወንጌላዊው “ወሀለዋ ህየ መሳብክት እለ ዕብን በዘያጥህሩ ቦቶን …አይሁድ እንደሚያደርጉት የመንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር”በሚል የገለጻቸው ስድስት ጋኖችና ሌሎችም ንዋያተ ንጽሕ  ነበሩአቸው፡፡(ዮሐ.2÷6)

በእያንዳንዱ ድርጊቶቻቸው፣በዕለታዊ ኑሮአቸው. በመታጠብ ለመንጻት ይፈጽሙት የነበረው ሥርዓትም አዲስ ልደት ለምናገኘበት አማናዊ ጥምቀት ቀጥተኛ ምሳሌ መሆኑ የማያጠያይቅ ክሡት  ግብር ነው፡፡

በመሆኑም እግዚአብሔር ለርስቱ የመረጠው ወገን የመሆን ማሳያ እንዲሆን፣ ከሕዝቡ ተለይቶ ላለመጥፋትና በሕይወትም ለመኖር ጭምር የልብ መገረዝ በሌለበት አፍአዊ በሆነ የሥጋ መገረዝ ብቻ የራስንና የመላ ቤተሰብን ሸለፈት ማስወገድ በጊዜው  ሕጉ የሚጠይቀው ግዴታ ነበር፡፡

በእዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ላቆመው ኪዳን ምልክትነት እንዲፈጸሙ በሕግና በነቢያት ጥቅልሎች (መጻሕፍት) የታዘዙት የመንጻት ድርጊቶች  በከፊል  የሚከተሉት ናቸው፡፡

እነርሱም፦

  • ሕዝበ እስራኤል በአንዱ እግዚአብሔር ለማመናቸውና ለመታዘዛቸው ምልክት እንዲሆን ሸለፈትን መገዘር፣(ኢያ.5÷2)
  • ለቤተ መቅደስ የሰን መታጠቢያዎችን  ማሠራት፣ (1 ነገ.7፥27-45)
  • የሕዝቡን ኃጢአት ተሸክሞ ወደ በረሃ የሚለቀቅውን  እንስሳ ለግል ጥቅሙ ያዋለ (የወሰደ) ሰው ሲገኝ ወደሰፈሩ ከመግባቱ በፊት  በውኃ እንዲታጠብ  ማድረግ፣(ዘሌ16፥26)
  • አጥንቱ የተሰበረውን፣የተገደለውንና የሞተውን ሰው መቃብር የነካ በውኃ በተነከረ ነጭ አበቦች ባሉት ጭራ በሚመስል ሁስጱ (መልካም መዐዛ ባለው ተክል) እንዲረጭ ማድረግ ፣(ዘኁ19፥6–12)
  • ወደ ይሁዲ እምነት የሚመጣውን ሰው አስቀድሞ በውኃ ማጥመቅ ፣(ዘሌ 14፥9)
  • ካህናቱ ልብሰ ተክህኖውን ለብሰው የመታረቂያ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደመገናኛው ድንኳን ሲገቡ እንዳይሞቱ ከጠራ ናስ በተሠራ ሰን ላይ በተሞላ ውኃ የመታጠብ ሥርዓትን መፈጸም ፣(ዘጸ 30፥18-20)
  • አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ከታጠቡ (ከተጠመቁ ) በኋላ በጎ መዓዛ ባለው የተቀደሰ ቅብዐ ዘይትን መቀባት እንደኦሪቱ ትምህርት፣እንደ መቅደሱ ሥርዓት በመፈጸም መንጻት ይጠበቅባቸው  ነበር፡፡

ከላይ በተገለጸው መንገድ  ፍጹም ለሆነው ትምህርተ ጥምቀት ምሳሌ በመሆን ባገለገለው መለኮታዊ ኃይል በሌለው ውኃ በመጠመቅ ይፈጸም የነበረው የአይሁድ ጥምቀት (የመንጻት ሥርዓት) በየምኩራባቱ ሁሉ ዕለት ዕለት ሲፈጸም ቆይቷል፡፡

 ምንም እንኳን ጥምቀቱ ውሳጣዊ ቅድስናን የማያጎናጽፍ፣ ምሳሌያዊና አፍአዊ መነጻትን  ብቻ የሚያስገኝ ቢሆንም ሃይማኖተ አይሁድና ትምህርቱ የክርስትና አበባ የበቀለበት ግንድ፣የአማናዊ ጥምቀት ምሳሌያዊ ዐውድ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡(ዮሐ.4፥22)

ጥምቀተ አይሁድና ትምህርቱ የክርትና አበባ የበቀለበት ግንድ  በመሆን ልጅነት ለሚያሰጠው ጥምቀት በምሳሌነቱ ቢጠቅምም ዘላቂ የሆነ የሕይወት ዋስትና መስጠት ያልቻለ መንፈቀ ፍጻሜ (የግማሽ ድኅነት ሥርዓት) በመሆኑ ሰውን በምልዐት የማጽደቅ ኃይል  አልነበረውም፡፡

ከአማናዊ ጥምቀቱ፣ ከርቱዕ ሥርዓቱ የማነሱም ምክንያት“ኦሪትሰ ጽላሎት ይእቲ ለእንተ ትመጽእ ሠናይት…ኦሪትና ሥርዓተ ጥምቀቷ ለምትመጣው በጎ ነገር (ልጅነት ለምታሰጠው ጥምቀት) ጥላ ናትና ነው፡፡(ዕብ 10፥1)

በመሆኑም በእግዚአብሔርና በእነርሱ መካከል የሚጠብቁት ቃል ኪዳን ሆኖ እንደተሰጣቸው የሚያምኑት ሁሉ (ሕዝቡ) ሕጉን በትምህርት ሰምተው ጥምቀቱን እንደ ሥርዓቱ ቢፈጸሙትም ሊለውጣቸውና ሊያድናቸው ስለአልቻለ የሕጉን አጥር ጥሰው& እግዚአብሔርን ረስተው እስከ ክርስቶስ መምጣት ሁሉም በደለኛ ሆኖ በሞት ግዛት ውስጥ ቆይቷል፡፡(ዘፍ.17÷10-11)

ከላይ እንደተገለጸው በምሳሌነት ይፈጸም የነበረው. የአይሁድ ጥምቀትና የዮሐንስ ጥምቀት ጥምቀተ ክርስትና የሚያስገኘውን ድኅነት አስቀድሞ የሚያመለክት ጽላሎት ነበር፡፡(1ቆሮ 10፥1-4)

ጥምቀተ ዮሐንስ

ጥምቀተ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ„የሚለውን አዋጅ በማወጅ፣ የጌታን መንገድ በመጥረግ ሕዝቡን ለአማናዊ ጥምቀት ለማዘጋጀት የሚፈጸም፣ ወደፊት የሚመጣውን የሚያመለክት የንስሐ ጥምቀት ነበር፡፡ (ማቴ 3፥3-7)

“መንገዴን ያዘጋጅ ዘንድ መልእክተኛዬን አስቀድሜ እልካለሁ„ ተብሎ በነቢዩ ሚልክያስ አስቀድሞ እንደተነገረው የዮሐንስ ጥምቀት በትክክል ሕዝቡን ለጌታ ለማዘጋጀት በቤተ ራባ በማዕዶተ ዮርዳኖስ ይፈጸም የነበረ ጥምቀት እንደሆነ ሰማዕተ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ “የእኔ ደስታ ዛሬ ተፈጸመ እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል፡፡ ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው„በማለት የመሲሑን መምጣት ይናፍቁ የነበሩ ደቀመዛሙርቱንና አስቀድሞ በአፈ ነቢያት ተነግሮለት የተቀበለውን የምስክርነት መክሊት ከነትርፉ በማስረከቡ ታውቋል ፡፡(ሚል 3፥1@ ዮሐ1፥23፤ 3፥29–31)

ስለራሱ ማንነትም “አንተ ማነህ?„ብለው የአይሁድ ካህናትና ሌዋውያኑ ሲጠይቁት “እኔ ጥርጊያውን አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ ነኝ„ በማለት አርከ መርዓዊ (የሙሽራው ሚዜ) በሙሽራው ድምጽ ደስ የሚሰኝ &የደስታው ተካፋይ  እንደሆነ በግልጽ መስክሮአል፡፡

በመሆኑም የአይሁድ ጥምቀትና የዮሐንስ ጥምቀት ዓላማቸው በምሳሌነታቸው መሸጋገሪያ ድልድልይ ሆነው ወደ ፍጽምት ጥምቀት መርቶ ማድረስ ስለነበር ጊዜው ሲደርስ ሥጋን የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያይ ዘንድ ሥርየተ ኀጢአት  ለምታሠጠው ”አኃቲ ጥምቀት“ሥፍራቸውን ለቀዋል፡፡

ምክንያቱም„ እስመ ግዝረትሰ ወኵሉ ትእዛዘ ኦሪት አምሳላት እሙንቱ …ግዝረትና ሁሉም የኦሪት ትእዛዛት ለፍጽምት ጥምቀት፣ለክርስቶስ ሕማማትና ለሞቱ ምሳሌዎች ናቸውና„ የአይሁድ የሥጋ ግዝረት በስሙ ለተጠመቁት ስለማያስፈልግ ነው ስፍራቸውን የለቀቁት ፡፡ (ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ )

በአጠቃላይ የአይሁድ ጥምቀት ለሥጋ መንጻት፣የዮሐንስ ጥምቀት ለንስሐ  ሲሆን የክርስቶስ ጥምቀት ደግሞ ለድኅነት መሆኑን መጻሕፍት አምላካውያት በስፋት ያስገነዝባሉ፡፡(ዮሐ1፥29)

ጥምቀተ ክርስቶስና በእርሱ የተገኘው ፍጹም ድኅነት ፦

ከላይ በምሳሌ ሲገለጽ፣በትንቢት ሲነገር የመጣው ጥምቀተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አንድነትና ልዩ ሦስትነት የተገለጠበት ዐቢይ ምስጢር ፣ ከአይሁድ ጥምቀትና ከዮሐንስ ጥምቀት ፈጽሞ የተለየ ሥርየተ ኀጢአትን የሚያሰጥ ማኅተመ ሕይወት ነው፡፡(ማቴ 3፥16-17)

በሕግ መጻሕፍት፣ በትንቢተ ነቢያት እንደሚመጣ አስቀድሞ  የተነገረለት መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በሥጋ ሰብእ ተወልዶ ፣ግእዘ ሕፃናትን  ጠብቆ በየጥቂቱ አድጎ በሠላሳ ዘመኑ ተጠምቆ የኀጢአት ሥርየትን ፣የነፍስ ድኅነትን እንድናገኝ ይህን ድንቅ ምሥጢር ገለጠልን፡፡

በጥምቀቱም “ተመልሶ ይምረናል ኀጢአታችንንም ወደ ባሕሩ ይጥለዋል„ ተብሎ የተነገረው ቃለ ነቢይ ልጅነትን በሚያስገኝ፣ጸጋን በሚያሰጥ ሁኔታ ከብሮና ተቀድሶ አማናዊ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ (ሚክ 7፥19)

ለፍጥረቱም የነበረው የእግዚአብሔር ፍቅር ተገልጦ፣የሰው ልጅ የመዳን ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ አግኝቶ፣ በትእዛዛት ተጽፎ የነበረው የዕዳ ጽሕፈቱ ተደምስሶ አዲስ የሕይወት መንገድ እንደተከፈተለት በጥምቀቱ የተገኘው ክብረ ሥጋና ክብረ ነፍስ ይመሰክራል፡፡(ዮሐ.3፥3-6)

በግብረ ኀጢአት ጎስቁሎ የነበረው ባሕርያችንም መታደስን አግኝቶ ውበቱ የተገለጠው፣ ለመንፈሳዊ ሀብታት በር በሆነው  እርሱ በሠራልን በዚህ አማናዊ ጥምቀት ነው፡፡

በመሆኑም በማዳኑ ክሂሎት፣ በይቅርታው ብዛት የተሰጠን፣ወደ አዲሱ ሕይወት የገባንበት ጥምቀት ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ፣ አፍአዊ ሳይሆን ውሳጣዊ መሆኑን ታላቁ የነገረ መለኮት ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲናገር “ ተሐጽቦሰ ዘዝየ አኮ ዘሥጋ ዳዕሙ ዘነፍስ…የአሁኑስ መታጠብ የሥጋ ያይደለ የነፍስ መንጻት ነው” ብሏል፡፡

በሌላ በኩል ሞቱን በሚመስለው ጥምቀቱ አሮጌው አዳማዊ ሰውነቱ ከነሥራው ተወግዶ ከውኃና ከመንፈስ የተወለደው ሁሉ “አዲሱ ሰው„ የተባለ ክርስቶስን እንደለበሰ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ማኅበረ ምእመናን በጻፈው መልእክቱ “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው ፡፡ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል„ በማለት ወደር በማይገኝለት ምህሮ “የምሥራቹን„ ፍጹም በሆነ የልብ ደስታ ገልጦታል፡፡(2ቆሮ 5፥17)

በአስተርእዮተ እግዚአብሔር የተገኘውን  ሰላምና ይህን የምሥራች . የሚያበሥር መልእክተኛ ሲመጣ ማየት፣ድምፁንም መስማት ደግሞ እንዴት ደስ እንደሚያሰኝ ከመልእክቱ ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡

አሮጌው ነገር አልፎ “አዲስ ፍጥረት„ የመሆንን የምሥራች የሰሙት  ሁሉ የልብን ክፉ ሐሳብ በማስወገድ፣በማያቆስለው ሥርዓት በመጠመቅ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በአማናዊ ጥምቀት በመሳተፍ ሀብተ ውልድና፣ሕይወተ ልቡና አግኝተው ከሥጋዊ ግብር የተለዩ መሆናቸውን እናስተውላለን  ፡፡

ከሥጋዊ ግብር ተለይተው የሚኖሩት ውሉደ ጥምቀትም በምን ዐይነት ሁኔታ እንደተወለዱና ባሕርያቸውም ምን እንደሚመስል  ታላቁ መጽሐፍ ሲነግረን “እለ ኢኮኑ እምነ ዘሥጋ ወደም ወኢ እምሥምረተ በእሲ ወብእሲት አላ እምእግዚአብሔር ተወልዱ…እነርሱ ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር አልተገኙም ሴትና ወንድ ተስማምተው ከሚሠሩትም ሥራ አልተወለዱም” ይለናል፡፡(ዮሐ1÷13)

በመሆኑም ከማይጠፋው ዘር የተወለዱት ውሉደ ጥምቀት የተወለዱበትን ምሥጢር በሥጋዊ አስተሳሰብ ልንደርስበት (ልንረዳው)የማንችለው በመንፈሰ ኅሊና ብቻ የሚታይ ረቂቅ ኃይልና የጽድቃችን ማኅተም ነው፡፡(1ጴጥ 1፥23)

ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይህን ረቂቅ ልደት ከድንግል ማርያም የሥግው ቃል መወለድ ምሥጢር ጋር እያነጻጸረ ሲያስተምር፦ “ወተወልዶሰ እምጥምቀት ይመስል ልደተ እምድንግል በከመ ክርስቶስ ተወልደ እማርያም ወእምድኅረ ተወልደ እምኔሃ ተረክበ አንቀጸ ሥጋሃ እጽወ በማኅተመ ድንግልናሃ ወከማሁ ዘሂ ተወልደ እምከርሠ ጥምቀት ወጺኦ እማይ ኢተረክበ አሠረ  በዓቱ ወጸአቱ ውስተ ከርሠ ምጥማቃት…በጥምቀት መወለድስ ከድንግል መወለድን ይመስላል፡፡ክርስቶስ ከድንግል ማርያም እንደተወለደ ከእርሷም ከተወለደ በኋላ አንቀጸ ሥጋዋ በድንግልናዋ ማኅተም ታትሞ እንደተገኘ ምሥጢሩም ረቂቅ እንደሆነ እንደዚሁ ከጥምቀት ማሕፀን የተወለደ ሰው ከውኃ ወጥቶ ወደ መጠመቂያው ውስጥ የመግባቱና የመውጣቱ ምልክት አይገኝም፣ በሥጋዊ ግብርም አይያዝም„ በሚል የገለጠበት ምሳሌያዊ የትምህርት አቀራረብ እጅግ የረቀቀና የሚደንቅ ነው፡(መጽ.ምሥጢር )

ዳግመኛም ይኸው ሊቅ ጥምቀተ ክርስቶስ ዕርቃናችንን የከደነ፣ ልጅነትን የተጎናጸፍንበት ድንቅ ምሥጢር መሆኑን ሲነግረን፦ወህየንተ ቆጽለ በለስ ዘሰፈየ አዳም ወገብረ ሎቱ መዋርዕተ ወከደነ ዕርቃኖ ወከማሁ አነሂ ተከደንኩ በመርዓ ጥምቀቱ ዘውኅዘ እምገቦ ወልድኪ …አዳም ሰፍቶ፣ መከለያ አድርጎ ዕርቃኑን በሰወረበት የበለስ ቅጠል ፈንታ እንዲሁ እኔም ከልጅሽ ጎን ከፈሰሰው የጥምቀት ውኃ ተከደንሁ ልጅነትንም አገኘሁ” እያለ ስብሐተ ጥምቀቱን በመቅረዘ ትርጓሜው ከፍ አድርጎ አመስጥሮታል፡፡(አርጋኖን ዘሰኑይ)

በመሆኑም ከሥጋ ወላጆቻችን አንድ ጊዜ እንድምንወለድ ሁሉ ዳግመኛ ጥልቅ በሆነ ምሥጢር የምንወለድበት ጥምቀተ ክርስትናም ንጽሐ ነፍስን ፈጽሞ የሚያሰጥ በመሆኑ  አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም የማይደገም ምሥጢር ነው፡፡

ጥምቀተ ክርስትና የማይደገም ምስጢር ስለመሆኑ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት፦

ጥምቀተ ክርስትና አንድ ጊዜ ፈጽሞ ጥሙቃንን በቀጥታ ውሉደ እግዚአብሔር እንዲሆኑ የሚያደርግ  የሕይወት ማሕፀን በመሆኑ ክሂለ አንጽሖ እንዳልነበረው የአይሁድ ጥምቀት በየጊዜው የሚፈጸም ሥርዓት አይደለም፡፡

በአንድ ጊዜ መጠመቅ ፍጹም የሆነ ድኅነትን እንደሚሰጥ ያልተረዱ፣እውቀት ከማጣታቸው የተነሳ የተጎዱ አንዳንድ ስሑታን ግን እንደ አይሁድ ሥርዓት ዳግመኛ ይጠመቃሉ፣ ያጠምቃሉ፡፡(ሆሴ 4$6)

መያጢተ ጸጋ ወጽድቅ ከሆነችው ከፍጽምት ጥምቀት ባሕርይ ጋር የማይስማማው ይህም ድርጊት በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ሲታይየቀና ሥርዓት እንዳልሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “አሐዱ እግዚአብሔር፣አሐቲ ሃይማኖት ፣ወአሐቲ ጥምቀት…አንድ ጌታ፣ አንዲት ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት „በማለት አስተምሮናል፡፡(ኤፌ 4፥5)

በተመሳሳይ የምሥጢር አንድነት ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም“ ሁለተኛ መጠመቅስ ልዩ ልዩ የሚሆን ጥምቀት የአላቸው የአይሁድ ሃይማኖት ጥምቀት ነው፡፡እናንተም ሁለተኛ ልትጠመቁ ትወዳላችሁ?…ወይእቲ ምዕረ አሐቲ…እርሷ ፈጽማ የማትደገም አንዲት ናት” በማለት ገልጦታል ፡፡

ሁለተኛ መጠመቅም  ክርስቶስን መስቀል  እንደሆነ ሲናገር “ዳግመኛ እጠመቃለሁ የሚል ሰው ጌታን ስለ እርሱ ሁለተኛ ይሰቅለው ዘንድ ይወዳል”፡፡ ምክንያቱም “እስመ ማየ ጥምቀት ስቅለት ውእቱ…ጥምቀት በሞቱ የተገኘ የሞቱ ምሳሌ ነውና” ይላል፡፡ (ድር.9)

በጉባኤ ቁስጥንጥንያ የተገኙት ቅዱሳን አባቶቻችንም በአንቀጸ ሃይማኖት ፍጽምት ጥምቀት አንድ ጊዜ በሚፈጸመው ሥርዓቷ ልጅነትን በማሰጠት ለመንግሥተ ሰማያት የምታበቃ ስለሆነች  ከማይደገሙት ምሥጢራት መካከል  መሆኗን “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት …የኀጢአት ሥርየትን በምታሰጥ አንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡„ በሚለው ትምህርትና  ቀኖና አጽንተውታል፡፡(ጸሎተ ሃይማኖት)

በአጠቃላይ ለሕጽበተ ዳግም ልደት  የተሰጠን ጥምቀተ ክርስቶስ የጽድቅ ሁሉ ፍጻሜ  መሆኑን እንድናስተውል “መጽአ ወተጠምቀ እምኃበ ዮሐንስ ከመ ይፈጽም ኵሎ ጽድቀ…ጽድቅን ሁሉ ሊፈጸም  ወደእኛ መጣ በዮሐንስም ዘንድ ተጠመቀ„በማለት ባለመኃልዩ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በማያሻማ ሁኔታ ገልጦታል፡፡(መዝሙር ዘሰንበት)

ከዚህም ጋር የትምህርተ ምስጢራትን ልዩነት በክልኤ ኪዳናት በውል ተረድተን በሚያሰጡት ሀብታት እንድንቀደስ “መፍትው እንከ ነገረ ኅቡአት ከመ ታእምሩ …ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የሚያሰጡ ምስጢራትን በውል ልትረዱ ይገባል„ ተብሎ ተጽፎአል ፡፡ (መጽሐፈ ኪዳን)

በመሆኑም ነገረ ኅቡአትን የተረዳችው፣ የገሃነም ደጆች ላያነዋውጧት በዐለት ላይ የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምታምነው እምነትና የምስታስተምረው ትምህርት  በብዙ ኅብረ ምሳሌያት አስቀድሞ የታየና የተነገረ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የተመሳከረ  ፍኖተ ጽድቅ ነው፡፡(መድሎተ ጽድቅ)

ስለሆነም በሐሊበ ንጽሕ የሚያድጉት ልጆቿ በጥምቀት የሚገኘውን የጽድቅ ጥሩር ለብሰው በመንፈስና በእውነት እያመለኩ፣ የዲያብሎስን ሽንገላ እየተቃወሙ፣ እንዲኖሩ የመዳን በር የሆነውን ምሥጢረ ጥምቀት ሐዋርያዊ በሆነው ትውፊቷ እየፈጸመች፣ ተዝካረ ጥምቀቱን በየዓመቱ ለበረከት እያከበረች በደሙ ለዋጃት ሙሽራዋ ሁለንተናዋን በማስገዛት ትኖራለች፡፡( ዮሐ 4፥23 ፤ኤፌ 5፥24፤ 6፥11-14)

በመጨረሻም በሕጽበተ ዳግም ልደት የተወለድነው  እኛ ኦርቶዶሳውያን ለጠላት አሠራር የተጋልጥን እንዳንሆን እግዚአብሔር ከእኛ በሚፈልገው ልክ በአንድ ልብ ሆነን& አንድነታችንን አጽንተን በሰማይ ላለችው ማኅበር አረቦን (ምልክት) የሆነች ቤተ ክርስቲያንችንን በትረ ክህደታቸውን ቆርጠው ከተነሱ& ለመንጋው ከማይራሩ ጨካኞች በትጋት እንድንጠብቅ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ እርሱ ይርዳን  ፡፡(የሐ.ሥ 20፥ 28 ፤ 2ቆሮ 13፥11)

 

መንክር ስብሐተ ጥምቀቱ

መጋቤ ብርሃናት አባ ተክለያሬድ ጎርጎርዮስ

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ

 ዋና ኃላፊ

ብሔር አይለየንም

ብሔር የሚለው ቃል ከግእዝ የተገኘ ቃል ሲሆን፤ ሲተረጐምም ብዙ ሐተታ አለው። ከአሉት ሐተታዎች መካከል ለግንዛቤ ያህል በአጭሩ፦

1ኛ) ብሔር «ቦታ» ተብሎ ሲተረጐም፥ (ኢሳ. 49፥20፤ ኢዮብ 28፥1)

2ኛ) ብሔር «ግዛት» (አውራጃ) ተብሎ ሲተረጐም፥ (ዮናስ 1፥8፤ ኤር. 1፥1-2)

3ኛ) ብሔር «ነገድ» (ወገን) ተብሎ ሲተረጐም፥ (1ኛነገ. 14፥24፤ 1ሳሙ. 14፥24)

4ኛ) ብሔር «ሰዓት» ሲሆን፥ (የሐዋ.ሥራ 2፥15)

5ኛ) ብሔር «የመጽሐፍ ክፍል» ሲሆን፥ ብሔረ ኦሪት፥ ብሔረ ነገሥት ይባላል።

6ኛ) ሰማይና ምድር በሙሉ ማለት ሰማይ ከነግሱ፥ ምድር ከነልብሱ፥ በጠቅላላ መላው ዓለም ላዩም ታቹም የአንድ አምላክ ግዛት ስለሆነ በምሳሌ «ብሔር» ተብሎአል። «ከመዝ ይቤ እግዚአ-ብሔር — የዓለም ጌታ (ፈጣሪ) እግዚአብሔር እንዲህ አለ» (ኢሳ. 66፥1)።

ከዚህ በላይ ከተራ ቍ. 1-6 ከሰፈረው በመነሣት «ብሔር» የሚለው ቃል በልዩ ልዩ መልክ ሊተረጐም እንደሚችል  በግልጽ መረዳት ይቻላል።

በመሆኑም በዓለም ላይ ያለ ሰው ሁሉ ብሔሩ አንድ ነው፤ የተለየ ብሔር የለውም፤ ምክንያቱም የአንድ እግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ። ልበ አምላክ ዳዊት እንዲህ ይላል፦ «ሰማየ ሰማያት ለእግዚአብሔር ምድርሰ ወሀበ ለዕጓለ እመሕያው — ሰባቱ ሰማያት የእግዚአብሔር ማደሪያ ሲሆኑ፤ ምድር ግን ለሰው ልጅ ሁሉ መኖሪያ ልትሆን ፈጥሮ ሰጠ» (መዝ. 113፥24)።

ይህ ከላይ የተጠቀሰው ኀይለ ቃል ዓለም (ምድር) በመላዋ ለሰው ልጅ ሁሉ ብሔር ሳይለይ የጋራ መሆንዋን ነው። በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሔር የተሰጠን የበረከት ምድር ባለቤቶች እንደመሆናችን ተመስገን ይህን የሰጠኸን ብለን ልናመሰግንና መላዋ ቅድስት ኢትዮጵያ ሀገራችን የሁላችን፥ የጋራችን ናት ማለት አለብን።

ለምሳሌ ከዚህ በታች ያሉትን የቦታ መዳረሻዎች እንይ፦ ከሐረር እስከ ጎንደር፥ ከመቀሌ እስከ ባሌ፥ ከጎሬ እስከ ሽሬ፥ ከአኵስም እስከ ጎጃም፥ ከወሎ እስከ ደምቢዶሎ፥ ከጎዴ እስከ ጠገዴ፥ ከሲዳሞ እስከ ደብረ ዳሞ፥ ከሸዋ እስከ አድዋ፥ ከመተሐራ እስከ ሑመራ፥ ከአዲግራት እስከ ክብረ መንግሥት፥ ሌሎችም ስማቸው ያልተጠሩ በርካታ ቦታዎች በሙሉ የቦታ መጠሪያ ስምን (መለያን) እንጂ የሰው ተፈጥሮን ወይም የብሔር ልዩነትን አያመለክቱም።

ሰው በመላው አንድ ቅርጽ አንድ ባሕርይ ያለው፥ ከአንድ አባት ከአንድ እናት (አዳምና ሔዋን) የተገኘ የምድር ገዥ ነው። ቋንቋም በኋላ የመጣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከሆነ የቋንቋ ልዩነት የተፈጠረው በኋላ በቅጣት መልክ ከእግዚአብሔር የተሰጠ (ዘፍ. 11፥7-10) እንጂ ልዩነቱ ቀድሞ የነበረ አይደለም። ቋንቋ የሰዎች መግባቢያ መሣሪያ እንጂ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፤ ምክንያቱም ቋንቋ በምንም ዓይነት መመዘኛ ብሔር የለውምና ነው።

 

ቋንቋና ሃይማኖት

ቋንቋና ብሔር የተለየ ሃይማኖት የላቸውም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቋንቋ በብሔር፥ በዘር በጎሳ ሳትለይ ሁሉንም በአንድ ዐይን በመመልከት በእኩል ታስተምራለች። በስመ ሥላሴ አምኖ የተጠመቀ ከቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሥጋ ወደሙ ለመቀበል ሲቀርብ አንተ ማን ነህ? አንቺስ ማን ነሽ? ምን ቋንቋ ትናገራለህ? ትናገሪያለሽ? ሳትል፦ ወለዘሂ መጽአ ኀቤየ ኢይሰድዶ ወኢያወጽኦ አፍኣ — ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም» (ዮሐ. 6፥37) የሚለውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ እንኳን ኢትዮጵያዊ ይቅርና የውጭ ዜጋም ቢሆን አማኝ ሆኖ የተገኘ ሁሉ ፆታ (ወንድ ሴት)፥ ዕድሜ (ሕፃን ሽማግሌ)፥ አፍሪካዊ አውሮፓዊ፥ ቀይ ጥቁር፥ አጭር ረጅም ሳትል፥ የሕይወት ታሪካቸው፥ ተጋድሎአቸውና ቃል ኪዳናቸው በሙሉ በክብር መዝገብ ማለትም በስንክሳር ላይ፥ እንዲሁም ገድል፥ ድርሳንና ተአምር እየጻፈች ለትውልድ ታስተላልፋለች፤ በቃል ኪዳናቸውም ትማጸናለች።

 

ገዳማትና አድባራት

በስማቸውም ገዳማትና አድባራት በመመሥረት፥ በስማቸውም በሚፈልቁ ማየ ጸሎትና በሚከሰቱ አስደናቂ ተአምራቶች ይከሰታሉ፥ ይደረጋሉ ተብለው የማይታሰቡ፥ የማይፈወሱ ናቸው ተብለው በምድራዊ ሕክምና የሚታመኑ ሕመሞች ሳይቀሩ ሲፈወሱና ሲድኑ ይታያሉ። ምክንያቱም በሰው ዘንድ እንጂ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይቻል የለምና ነው (ማር. 9፥23፤ 11፥23)። ፍጹምና ጥርጥር የሌለው እምነት ይዘን ከተገኘንም የተመኘነውን ሁሉ የማግኘት ዕድላችን የሰፋ ነው። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በልቡአ ሙሉነት በክብረ ቅዱሳን ላይ አምና የምታስተምረው።

 

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ መሥራችዋና እንደ ፈጣሪዋ እግዚአብሔር ሰው ለሆነ ሁሉ ብሔር፥ ቋንቋ፥ ዜጋ፥ ቀለም፥ ወንድ ሴት፥ ሕፃን ሽማግሌ ሳትል በእኩል ዐይን እንደምታይና እንደምትወድ ሁሉ፥ እኛ ኢትዮጵያውያንም ከላይ በመግቢያው ላይ የጠቀስናቸው በተለያየ ስም የሚጠሩ ቦታዎች በሙሉ የጋራችን መሆናቸውን ከልብ በመረዳትና እንደ ጥንቱ ብሔር የማይለየን መሆኑን አምነን በመቀበል እንደ አንድ ልብ መካሪ፥ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሁነን ሀገራችንንና ሕዝባችንን በሰላምና በፍቅር ለመጠበቅ እንድንችል የፍጥረታት አስገኝ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን የ2015 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት የሰላምና የፍቅር በዓል ያድርግልን፤ አሜን።

 

ርእሰ ደብር መሓሪ ኀይሉ

የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት

 ዋና ሥራ አስኪያጅ

ትምህርት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ትምህርት ለሰው ልጆች መንፈሳዊና ማኅበራዊ ዕድገት በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ‹‹ካልተማሩ አያውቁ፤ ካላወቁ አይጸድቁ›› የሚለው የማኅበረሰብእ ብሂልም ሁሉም  ሰው ለትምህርት ትኩረት መስጠት እንዳለበት የሚያመለክት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በዕውቀት ያልተደገፈ አገልግሎት ሁሉ ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮት ሲገጥመው የመቋረጥ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም በመንፈሳዊ አገልግሎትም ሆነ በማኅበራዊ አገልግሎት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ለምን? ስለምን? ለማን? የሚሉ ጥያቄዎች ከተለያየ አቅጣጫ ሲነሡ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ መመለስ ይገባል፡፡ ይህንም ማድረግ እስከተቻለ ድረስ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ተግዳሮቶችን በቀላሉ ማለፍ ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት እስከ ዛሬ ለትምህርት ቅድሚያ ትሰጣለች ትምህርቱም በቃልና በተግባር የሚከናወን ነው፡፡ በቃልና በተግባር ስለሚከናወነው መንፈሳዊ ትምህርት ከማየታችን በፊት ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ትምህርት አስፈላጊነት ምን እንደሚል እንመለከታለን፡፡

‹‹ወትምህርትከ ዘያጸንዐኒ ለዝሉፉ ወተግሣጽከ ውእቱ ዘይሜህረኒ — ትምህርትህ ለዘለዓለም ያጸናኛል፤ የሚያስተምረኝም ተግሣጽህ ነው (መዝ. 17፥35)፤ ‹‹ሀቦ ለጠቢብ ምክንያተ ወያፈደፍድ ጥበበ አምሮ ለጠቢብ ወይዌስክ ጥበበ — ለጥበበኛ ሰው ትምህርትን ስጠው ጥበብን ያበዛል፤ ጽድቅንም አስተምረው ዕውቀትን ያበዛል፤ (ምሳ. 9፥9) ‹‹ለትምህርተ መጻሕፍት አልቦ ዘይጸግቦን ወፈድፋደሰ እለ ይኄልዩ ጥበበ — የመጻሕፍትን ትምህርት ማንም አይሰለችም፤ ይልቁንም ጥበብን ለተማሩ ሰዎች (ጰላድዮስ ቄርሎስ ምዕ. 1)

ትምህርት ለማን ?

ስለ ትምህርት ስናወሳ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ  ዕውቀት ማንሣት ግድ ይለናል። በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረውና በልጅነት የከበረው የሰው ልጅ ፊደል የሚያስቆጥረው መምህር፥ የሚማርበት መማሪያ መጽሐፍ፥ የሚመራበት ሕግ ሳያስፈልገው በተፈጥሮ በተሰጠው ዕውቀት እንደ ቅዱሳን መላእክት እያመሰገነ እንዲኖር እንጂ በቀይ በጥቁር ቀለም በተጻፈ መጽሐፍ እንዲማር ሥጋዊ ደማዊ መምህር እንዲያስተምረው አልነበረም፤ ‹‹እስመ ኢተወልደ ሰብእ ለዝ ከመዝ በቀለም ወበማየ ሕመት ያጽንዑ ሃይማኖቶሙ እስመ ኢተፈጥረ ሰብእ ዘእንበለ ከመ መላእክት ከመ ይንበሩ ጻድቃነ ወንጹሓነ — እንደ መላእክት ጻድቃንና ንጹሓን ሁነው እንዲኖሩ ነው እንጂ ሰው ለእንደዚህ ያለ ሥራ አልተፈጠረም ነበርና በቀይ ቀለምና በጥቁር ቀለም ሃይማኖታቸውን ሊያጸኑ ሰው ለእንደዚህ ያለ ሥራ አልተወለደም ነበርና›› (ሄኖክ 19፥24)። የሰው ልጅ አምላኩ እግዚአብሔር የሰጠውን የጸጋ ዕውቀት በምክረ ከይሲ/ሰይጣን ተታሎ በመነጠቁ የሚያስተምረው መምህር፥ የሚማርበት መጽሐፍ፥ የሚመራበት ሕግ የሚያስፈልገው ሁኖተገኝቷል፡፡ ከዚህ የተነሣ የሰውን ድኅነት የሚሻ ልዑል እግዚብሔር ለአዳም ልጅ ሁሉ  የሚማርበትን ፊደል ሰጥቶታል፤ የሚስተምረውንም መምህር ሹሞለታል። የሰው ልጅ ከፊደል ጋር የተዋወቀው በአዳም ሰባተኛ ትውልድ በሄኖስ እንደሆነ በቤተክርስቲያናችን ይታመናል፡፡ በመሆኑም ትምህርት ከድቀተ አዳም በኋላ ለሰው ልጅ የተሰጠ መሆኑን ከቃለ ሄኖክ መረዳት ይቻላል፡፡

ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ ከማንም ያልተቀበለችው የራሷ የሆነ ሀገር በቀል  ሥርዐተ ትምህርት አላት፡፡ ትምህርት ለሰው ልጆች የአእምሮ ማጎልበቻ፥ የችግር መግቻ፥ የሰብአዊነት መታወቂያ፥  ከድንቁርና መላቀቂያ፥ በተግባራዊነቱ መጽደቂያ መሆኑን በመረዳት፥ ባቋቋመቻቸው የአብነት ትምህርት ቤቶችና በአሁኑ ጊዜ ኮሌጆችን ጨምሮ ሕጻናት ከፊደል ጋር እንዲተዋወቁ፥ ካለማወቅ እንዲርቁ፥ በአእምሮ እንዲልቁ፥ በጥበብ እንዲራቀቁ ስታደርግ ኑራለች፤ በአሁኑም ሰዓት እየተገበረችው ትገኛለች፡፡

እስከ ሃያኛው  ክፍለ ዘመን ድረስ ያለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት ትምህርት አይታሰብም ነበር፡፡ ከሁሉም የሚደንቀው እማራለሁ ብሎ ወደ እርሷ የመጣውን ሁሉ በራሷ ፈቃድ ሃይማኖት፥ ጾታ ሳትለይ ከፊደል ጋር አስተዋውቃለች፤ ለንባብም አብቅታለች። ይህንም እውነታ በታሪክ ተረድተናል፤ ከክርስትናው ውጪ ያሉ ወገኖቻችን በመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ሲመሰክሩም ሰምተናል፡፡

ሀ. ትምህርት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በኢትዮጵያ

መዝሙረኛው ዳዊት ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› ሲል ሀገረ እግዚአብሔርነቷን የመሰከረላት ኢትዮጵያ፥ ከልደተ ክርስቶስ በፊት በውስጧ ትምህርትና የአምልኮ ሥርዐት እንደነበር ኢትዮጵያዊው ጀንደረባ እንዲሁም ሊቃውንት ይመሰክራሉ፡፡ ‹‹ሠለስተ ጊዜያተ በዓመት ግበሩ ሊተ በዓለ — በዓመት ሦስት ጊዜ በዓል አድርጉልኝ ባለው ቃል መሠረት›› (ዘፀ. 23፥14) ሥርዐተ አምልኮውን ለመፈጸም ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘውና ሥርዐተ አምልኮውን ፈጽሞ ሲመለስ ‹‹እንደ በግ ሊታረድ መጣ የበግ ጠቦት በሸላቹ ፊት  እንደማይናገር እንዲሁ አፉን አልገለጠም›› እያለ የኢሳይያስን የትንቢት መጽሐፍ እያነበበ በመንፈስ ቅዱስ የተጐበኘው፥ በፊልጶስ የታየው ኢትዮጵያዊው ጀንደረባ (ባኮስ) በኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ለመኖሩ ታላቅ ምስክር ነው፡፡ ምክንያቱም  ትምህርት ቤት ባይኖር ለንባብ የሚያበቃ ዕውቀትን ከማን አገኘ? ኢየሩሳሌም ነው እንዳንል ወደ ኢየሩሳሌም ሂዶ ለፈጣሪው ለመስገድ የተነሣው ከኢትዮጵያ ነው፤ ወደ ኢየሩሳሌም ሂዶ ለመስገድ የሚያስችለውን ዕውቀት ከኢትዮጵያ ካላገኘ ከማን ሊያገኝ ይችላል? እንዴትስ ለመሄድ ተነሣሣ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሣታቸው ግድ ነው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር›› እንዳለ፥  ቀደም ሲል ከታቦተ ጽዮን ጋር  በቀዳማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት  ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ያነበበው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የትንቢቱን መጽሐፍ እያበበ ፅንሰ ሐሳቡን መረዳት ሲሳነው በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት፥ በወንጌላዊው ፊልጶስ አስተማሪነት የብሉዩን ንባብ በሐዲስ ኪዳን የገቢር ትርጓሜ ተርጒሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምኖ በመጠመቅ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና አግኝቶ በልጅነት ከብሮ ደስተኛ ሆኖ ተመልሷል፡፡ (ግብ. ሐዋ. 8፥27-39)

ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ የክርስትና እምነትን በብሔራዊ ደረጃ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን አባትነት በደጋጉ ነገሥታት አብርሃና አጽብሓ መሪነት በአራተኛው ምእት ዓመት በዐዋጅ ለሁሉም ከማዳረሷ በፊት ከኢየሩሳሌም ቀጥላ  ከሁሉም አህጉር ቀድማ  በመጀመሪያው ምእት ዓመት በ34 ዓ.ም በጃንደረባው (ባኮስ) አማካይነት የክርስትና እምነትን ተቀብላለች፤ በብሉይ ኪዳን ‹‹ይወርዳል፤ ይወለዳል … የሚለውን የትንቢት ንባብ ‹‹ወረደ፥ ተወለደ፥ ተጠመቀ፥ መከራ ተቀበለ፥ ሞተ፥ ተነሣ፥ ዐረገ፥ ዳግመኛ ይመጣል›› እያለች በመንፈሰ ረድኤት ያይደለ በመንፈሰ ልደት እየተረጐመች ለምስጋና ወደ እግዚአብሔር የተዘረጉ እጆቿ ሳይታጠፉ  ኑራለች ወደፊት ትቀጥላለች፡፡

ለ. ትምህርት ድኅረ ልደተ ክርስቶስ በኢትዮጵያ

የሐዲስ ኪዳን መዳረሻ ሁኖ ሲያገለግል የቆየው የብሉይ ኪዳን ትምህርት ታቦተ ጽዮንን አጅበው በመጡ ሌዋውያንና ተከታዮቻቸው በየዘመናቱ ሲሰጥ ከቆየ በኋላ በሐዲሱ ዘመን በሐዲሱ ትውልድ እጆቿን ዘወትር ዘርግታ የምታመሰግነውንና የምትማፀነውን የኢትዮጵያን ልመና እግዚአብሔር ተቀብሎ ሰማያዊውን ትምህርት በልጇ ቅዱስ ያሬድ አማካይነት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ሰጣት፡፡

መሪጌታ ልሳነወርቅ ገብረ ጊዮርጊስ ‹‹ጥንታዊ ሥርዐተ ማሕሌት ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ››  በሚል ርእስ በጻፉት መጽሐፋቸው ‹‹አፄ ገብረ መስቀል መስከረም 25 ቀን በ534  ዓ.ም እንደ ነገሡ ቅዱስ ያሬድን የወደደ ሀገሪቱ ኢትዮጵያንም የመረጠ እግዚአብሔር ኅዳር 5  ቀን አሮድዮን የሚባሉ ሦስት ነጫጭ ወፎችን በነግህ /በጧት/  ከገነተ ኤዶም ላከለት፤ ቅዱስ ያሬድ በሚያስተምርበት ስፍራ አንጻር በአየር ላይ ረበው ያሬድ ሆይ፥ የበቃህ ብፁዕነህ አንተን የተሸከመች ማሕፀንና አንተን አጥብተው ያሳደጉ ጡቶች የተመሰገኑ ናቸው ብለው በግእዝ ቋንቋ አመሰገኑት፡፡

ወሶበ ሰምዐ ዘንተ ቃለ ያሬድ አንቃዕደወ ሰማየ ወነጸረ ሠለስተ አዕዋፈ ወይቤሎን እምአይቴ መጻእክን እምገነተ ኤዶምኑ ዘትትናገራ ከመ ሰብእ ወትቤሎ አሐቲ ዖፍ እምሠለስቱ አዕዋፍ ተፈነውነ ኀቤ ከእምገነተ ኤዶም ከመ ንንግርከ ወንዜኑከ ዘከመ ትነሥእ ማሕሌተ እምዕሥራ ወአርባዕቱ ካህናተ ሰማይ ወእንዘ ይትናገራ ዘንተ ተመሥጠ ያሬድ ወእማንቱ አዕዋፍ ቦአ ውስተ ገነተ ኤዶም ወተሠወራ እምአዕንቲሁ —   ያሬድም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ አንጋጦ ሦስቱን ወፎች አየና እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ከወዴት መጣችሁ፥ ከገነተ ኤዶም ነውን አላቸው።

ከሦስቱ ወፎች አንዷ ወፍ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ማሕሌት ሰምተህ እንድታዜም ዕድል የተሰጠህ መሆኑን እንነግርህና አበሥርህ ዘንድ ከገነተ ኤዶም ወደ አንተ ተልከናል አለችው። ይህን እየተነጋገገሩ ሳሉ ወዲያው ያሬድ ወደ ገነተ ኤዶም ተመሠጠ /ተነጠቀ/ ወደ ገነተ ኤዶምም ገብተው ከዐይኑ ተሰወሩ ቅዱስ ያሬድም በዚያ ቁሞ ሳለ እነዚያ ወፎች በረው ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሲገቡ እርሱም ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ገባ፤ በዚያም ሰማይንና ምድርን የፈጠረ እግዚአብሔርን በእንዚራ በአርጋኖንና በመሰንቆ ከፍ ባለ ዜማ ዘወትር ሲያመሰግኑት ሰማ፡፡

ቅዱስ ያሬድም ይህን ማሕሌት በሰማ ጊዜ ካለበት ቦታ ዘሎ ወደ እነርሱ ለመግባት ፈለገ ወደዚያ መግባት አልተቻለውም፡፡ እነዚያ ወፎችም መጡና ከእነርሱ አንዷ ወፍ፦ የሰማኸውን ማሕሌት አላስተዋልክምን ብላ ተናገረችው። ያስተዋልኩት ነገር የለም አላት፡፡  ወትቤሎ አነ «እነግረከ በዘትሌቡ ጸውዕ ስሞ ሐዲሰ ለእግዚአብሔር ዝ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወትነሥእ ማሕሌተ እምዕሥራ ወዐርባዕቱ ካህናተ ሰማይ በበዜማሁ — እኔ በምታስተውልበት ነገር እነግርሃለሁ የእግዚአብሔርን አዲስ ስም ጥራ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤  ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም በየዓይነቱ ዜማን ትማራለህ» አለችው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን ስም ሲጠራ ሰማያዊ ዜማ ተገለጠለት፡፡ ወዲያውም በግእዝ፥ በእዝል በአራራይ ማዜም ጀመረ፡፡

ከዚህ በኋላ ወደሚያስተምርበት ቤተ ቀጢን ተመልሶ ፊቱን በምሥራቅ አቅጣጫ ታቦተ ጽዮን ወደአለችበት አዙሮ ‹‹ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ››   ለአብ ምስጋና ይገባል ለወልድ ምስጋና ይገባል ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል የጽዮን መጀመሪያዋ እግዚአብሔር ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም የድንኳኑን ሥራ እንዴት መሥራት እንዳለበት ለሙሴ አሳየው›› በማለት ልዩ በሆነ ጣዕመ ዜማ አዜመ፡፡ (ዘፀ. 25፥8)

በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ በተበረከተው ሰማያዊ ዜማ ኢትዮጵያ በዕውቀት አበራች፥ ልዕልናዋን በዓለም አሳያች ከራሷም አልፋ የአፍሪካ ኩራት ለመባል በቃች፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በግእዝ ቋንቋ በብራና የተጻፈ ወንጌል ያላት እኮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስተያን ናት ይህች ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ የተግባር ብርሃን ያበራችና እያበራች ያለች መሆኗ እየታወቀ በዘመናችን በቢጽ ሐሳውያን  ኢትዮጵያን ወደኋላ እንደ ጎተተች ተደርጎ መቅረቡ አላዋቂነትን የሚሳይ ጨለምተኝነትን የሚያንጸባርቅ የስሕተት ንግግር ነው፡፡

ትምህርት ለዕውቀት ወይስ ለሕይወት?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕውቀትን ከሕይወት ሕይወትን ከዕውቀት አዋሕዳ ታስተምራለች ሕይወት የሌለው ዕውቀት (ትምህርት) ነፍስ የተለየው በድን ማለት ነው መማርም ሆነ ማስተማር የሚያጸድቀው ሲተገበርነው፡፡ ዕውቀትና ሕይወት የተስማሙለት ታላቁሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ቦኑ በአጽምዖ መጻሕፍት ይጸድቁ በቅድመ እግዚአብሔር አኮኑ ዳእሙ በገቢሮቱ ይጸድቁ — በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይጸድቁምና (ሮሜ 2፥13) እንዳለ፥ ለዕብራውያን በጻፈው መልእክቱም፦ ‹‹እስመ ስሙዓን ንሕነ በከመ ሰምዑ እልክቱ ወባሕቱ ለእልክቱሰ ኢበቊዖሙ ቃል ዘሰምዑ እስመ ኢተቶስሐ ልቦሙ በሃይማኖት ምስለ እለ ሰምዑ — ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምሥራች ተሰብኮልናልና ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም›› (ዕብ. 4፥2)፡፡ በሥርዐተ ቅዳሴውም ‹‹እግዚእነ ወአምላክነ ፈኑ ላዕሌነ ብርሃነከ ወጽድቀከ ወአብርህ አዕይንተ አልባቢነ ወሕሊናነ ወረስየነ ድልዋነ  ንስማዕ ቃለ ወንጌልከ ቅዱስ አኮ ዘንሰምዕ ባሕቲቱ አላ ንግበር በከመ ሰማዕነ ከመ ይፍረይ ላዕሌነ ፍሬ ሠናየ ህየንተ አሐዱ ሠላሳ ወስሳ ወምእተ — ጌታችን አምላካችን ሆይ፥ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክልን፤ የልቡናችንና የሕሊናችን ዐይኖች አብራልን፤ የቅዱስ ወንጌልህን ቃል በመጨከን እንሰማ ዘንድ የበቃን አድርገን፤ የምንሰማ ብቻ አይደለም፤ እንደ ሰማን ልንሠራም  ነው እንጂ ስለአንዱ ፈንታ ሠላሳ፥ ስልሳና መቶም መልካም ፍሬን በላያችን ያፈራ ዘንድ…›› ይላል (ሥርዐተ ቅዳሴ  ቊ. 187)፡፡

ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስገነዝቡን የተማርነውንና የምናስተምረውን ቃል በተግባር ላይ መዋል እንዳለብን ነው የተማርነውን በተግባር ላይ ካላዋልነው  ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ለኢትዮጵያ ዕድገት ካበረከተቻቸው በጥቂቱ

  1. ትምህርት፦ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷ ፊደል፥ ቀመር፥ ሥርዐተ  ትምህርት ያላት በራስዋ ማንነት የቆመች መጽሐፍ ቅዱስን ከሀገር  በቀል ትምህርቷ ጋር አስማምታ የሀገር መሪዎቿን  የአስተዳደር ጥበብን፥ ፍቅረ ሀገርን ፈሪሀ እግዚአብሔርን እያስተማረች አንድነቷን ያስጠበቀች ከእርሷ ተወልደው ከእርሷም ተምረው ባደጉ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ልጆቿ ነው፡፡
  2. ታሪካዊ ቅርስ፦ ከርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ጀምሮ እስከ እንጦጦ ማርያም ድረስ በሁሉም ክልሎች ዕፁብ ድንቅ የሚያሰኙ ዕድሜ ጠገብ የብራና መጻሕፍት፥ የወርቅ፥ የብር፥ የናስና የዕፅ መስቀል፤ ከበሮ፥ ጸናጽልና መቋሚያ፥ ልብሶ ተክህኖ፥ ዘውዶች ወዘተ. በአጠቃላይ በተለያየ ምከንያት ከሀገር የወጡና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ንዋያተ ቅድሳት ከቤተ ክርስቲያን የተገኙ የኢትዮጵያን ሥልጣኔና ዕድገት የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የሚመጡት የኢትዮጵያ  አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ቅርሶቿን ለመጎብኘት የበዓል አከባበር ሥርዐቷን በተለይ በዓለ ልደት፥ ጥምቀትና መስቀልን ለመመልከት እንደሆነ ሁሉም የሚረዳው ሐቅ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ያበረከተች ቤተ ክርስቲያን፦ ኢትዮጵያን አሳደገች እንጂ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ጎተተች እንዴት ሊባል ይችላል?! ==
  3. ነጻነት ከእነ ክብሩ፦ በታሪክ እንደሚታወቀው የአፍሪካ ሀገሮችን ምዕራባውያን እንደ ቅርጫት ሥጋ ተከፋፍለው በቅኝ ግዛት ሲያንበረክኳቸው ኢትዮጵያ ግን ለማንም ወራሪ ያልተበረከከች፥ ባህሏን፥ ታሪኳንና ክብሯን ጠብቃ የኖረች፥ ማንነቷን ያላስደፈረች፥ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገች መሆኗ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ ለነጻነቷ ያገዛት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው፤ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ኢትዮጵያ ‹‹ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለኢትዮጵያ ይዕቀባ እመዓተ ወልዳ›› እያለች በሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት በእያንዳንዷ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን  በጋራ በሚጸለየው ጸሎት ታስባታለች፤ ጸሎቱም ሰይፍ ጋሻ ሁኗት በራሷ ማንነት  ተከብራ  አንድትኖር አስችሏታል፡፡

ሁለተኛው ነጻነቷን ተጋፍቶ ድንብሯን ጥሶ የመጣውን የፋሽሽት ጣሊያን ወራሪጠላት ለመመከት ታቦቷን ይዛ በንጉሠ ነገሥት ዐጼ ምኒልክ መሪነት ሕዝቡ ከንጉሠ ነገሥቱ ጎን ተሰልፎ የሀገር ወራሪን እንዲመክት አስቻላለች፡፡ ከአርባ ዓመት በኋላ የቀደመ ሽንፈቱን ለማካካስ ቢመጣም ሰማዕታተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያንና አቡነ ሚካኤልዘጎሬን ፊት ለፊት አሰልፋ ‹‹ ለሀገራችሁና ለሃይማኖታችሁ መሥዋዕት መሆን አለባችሁ›› በማለት መሥዋዕትነቷን በተግባር አረጋግጣለች፡፡ ‹‹በጎረስኩ እጄን ተነከስኩ›› እንዲሉ የደም ዋጋ ከፍላ የሀገር አንድነትን ያስጠበቀች ቤተ ክርስተያን መከበርና መሸለም ሲገባት ትምህርቷን የሚበርዙ፥ እውነተኛ ታሪኳን የሚሠርዙ፥ በምቀኝነት የደነዘዙ ኢትዮጵያውያን ሁነው የኢትዮጵያን አንድነት የማይወዱ ጎረምሶች እያፋቸሉባት ይገኛሉ፡፡

በመጨረሻም በረከታቸው ይድረሰንና የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት  ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስተያን የታሪክ መጽሐፋቸው ቤተ ክርስቲያናችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተቻቸውን በጽሑፋቸው እንደገለጡት ማጠቃለያ አድርጎ ማቅረብ እውነታውን የሚያረጋግጥ ሆኖ በመገኘቱ እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርቦአል፡፡

  • ሙሉ ትምህርት
  • ፍጹም ቋንቋ ከእነ ፊደሉ
  • ሥነ ጽሑፍ ከነጠባዩ ከነሙያው
  • ኪነ ጥበብ በየዓይነቱ
  • ሥነ ጥበብ በየመልኩ
  • ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ
  • እምነት ከነፍልስፍናው
  • ነፃነት ከነክብሩ
  • አንድነት ከነጀግንነቱ
  • ሀገር ከነድንበሩ ከነፍቅሩ
  • ስም ከነምልክቱ

ይህን ሁሉ ያበረከተች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ብርሃንን አላበራችም፤ ኢትዮጵያን አላሳደገችም ማለት ይቻላል? ዘቦ ዕዝን ሰሚዐ ለይስማዕ (ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ)፡፡

መጋቤ ሐዲስ ኀይለ እግዚእ አሰፋ

የሰ/ብ/ቅ/ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን

ከራድዮን ዖፍ ጸዐዳ

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ከሰማየ ሰማያት የወረደውን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በድንግልና የተወለደውን እግዚአብሔር ወልድን “ለዘተወልደ እምቅድስት ድንግል ምንተ ንብሎ ናስተማስሎ አርዌ ገዳምኑ አንባሳ ወሚመ ከራድዮን ዖፍ ጸዐዳ ንጉሥ አንበሳ  እምዘርዐ ዳዊት ዘመጽአ (ከዳዊት ዘር የመጣውን፤ ከድንግል የተወለደውን ምን እንበለው የዱር አንበሳ፤ ወይስ ከራድዮን የተባለ ጸዐዳ ወፍ)” በማለት አመስግኗል፡፡ ከራድዮን ማለትም ስመ ዖፍ (የወፍ ስም) ነጭ፤ መልከ መልካም ወፍ፤ የክርስቶስ አርአያ፤ የሰውነቱ አምሳል ነው፡፡ ይህ የክርስቶስ ምሳሌ የሆነ ወፍ በሀገራችን ባዋሽ ወንዝ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም ቅድስት ድንግል ማርያምን ሲያመሰግን “ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል ወሱራፌል መጽአ ወኀደረ ውስተ ከርሥኪ(በኪሩቤል፤ በሱራፌል አድሮ የሚኖረው እርሱ ሰው ሆኖ በማሕፀንሽ አድሮአልና፡፡ መፍቀሬ ሰብእ አቅረበነ ኀቤሁ፡፡ ዘዚኣነ ሞተ ነሥአ ወእንቲኣሁ ሕይወተ ወሀበነ (ሰውን የሚወድ ሰው የሚወደው እርሱ የእኛን ሞት ነሥቶ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጥቶ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር አስታረቀን)”፡፡ በማለት  በዐርብ ውዳሴ ማርያም ክፍል ሁለት ላይ የገለጸውን የተዋሕዶ ሊቃውንት ሲተረጒሙ፡-

ታሪክ፡- ከራድዮን የሚባል ጸዐዳ ዖፍ አለ፡፡ ከነገሥታቱ ቤት ይኖራል፡፡ ሰው ሲታመም አምጥተው ከፊቱ ያኖሩታል፡፡ የሚሞት እንደሆነ ፊቱን ይመልስበታል፡፡ የሚድን ከሆነ ቀርቦ አፉን ካፉ አድርጎ እስትንፈሱን ይቀበለዋል፡፡ ነጭ የነበረው ይጠቁራል፡፡ ብርድ ብርድ ይለዋል፡፡ ዋዕየ ፀሐይ ሲሻ ወደ አየር ይወጣል፡፡ ሦስት ሰዓት ዋዕየ ፀሐይ ተመቶ ዋዕየ ፀሐይ ሲሰማው ወደ ባሕር ይወርዳል፡፡ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ ባሕር አድሮ የቀደመ ጠጉሩን መልጦ ታድሶ ይወጣል፡፡ ዖፍ ጸዐዳ (ነጭ ወፍ) የተባለው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቀይሕ በትስብእቱ ጸዓዳ በመለኮቱ እንዲለው፡፡ ድውይ የተባለ አዳም ነው፡፡ ቀርቦ እስትንፋስን እንደመቀበል የአዳምን ባሕርዩን ባሕርይ አድርጓል፡፡ ደዌ በእስትንፋስ ወደ እሱ እንደተመለሰ የአዳምን ባሕርይ ባሕርይ ቢያደርግ በአዳም የተፈረደውን መከራ ተቀብሏል፡፡ በማለት አመሥጥረው ይተርጒማሉ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍም “ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ — በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንም ተሸክሟል” (ኢሳ. 53፥.4) ሲል አረጋግጦልናል፡፡

ቅዱስ ያሬድ “ዖፍ ጸዓዳ፤ ንጉሥ አንበሳ፤ ተጠምቀ በማይ በዮርዳኖስ ቀላይ፤ በእንቲአነ ተጠምቀ ወገብረለነ ሰላመ — ነጭ ወፍ፤ ንጉሥ አንበሳ፤ በዮርዳኖስ ወንዝ በውኃ ተጠመቀ፤ ስለእኛ ተጠመቀ፤ ሰላምን አደረገልን” በማለት በምሳሌ አመስጥሮ ዘምሯል፤ አመስግኗል፡፡

ይህም ምሳሌ ጌታ አዳምን ፈጥሮ በነፍስ ሕያው አድርጎ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር ከሰማይ በታች ከምድር በላይ ያለውን ሁሉ ብላ፥ ጠጣ፥ ግዛ፥ ንዳ ብሎ በገነት አኖረው፡፡ ሰባት ዓመት ከሦስት ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በሕጉ ጸንቶ ኖረ፡፡ ከዚህ በኋላ ምክረ ከይሲን ሰምቶ፤ አምላክነትን ሽቶ፤ ዕፀ በለስን በልቶ፤ ከፈጣሪው ተጣልቶ፤ ከገነት ወጣ፡፡ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፤ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነምን ፈረደበት፡፡ ዲያብሎስም የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ በአዳምና በሔዋን ሥቃይ አጽንቶ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ብለው ስመ ግብርናቸውን ጽፈው እንዲሰጡት በማድረግ በሁለት እብነ ሩካብ የጻፉትን አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጣለው፡፡ በዮርዳኖስ የጣለውን ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶላቸዋል፡፡ በሲኦል የጣለውን በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶላቸዋል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ “ወበዝንቱ ተዐውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ (በዚህም እግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነ ለእኛ ታወቀ፤ እግዚአብሔር እኛን መውደዱ ታወቀ፡፡ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነዎ ውስተ ዓለም (ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የባሕርይ ልጁን ወደዚህ ዓለም ሰዶልናልና አለ፡፡ በዘመነ ብሉይ የነበረው ዘመን ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኲነኔ አልፎ እውነት ምሕረት የሰፈነበት የይቅርታ ዘመን እንደመጣ፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ጠፍቶ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ፤ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ እንደተሰጠ ተረጋጋጧል፡፡ የምሕረት ቃል ኪዳን ተፈጽሟል፡፡

እግዚአብሔር ወልድ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁሉን ያስገኘ፤ ሰውን የፈጠረ፤ በሥራው ሁሉ ያለ፤ በሙሴ አድሮ ሕዝቡን ያስተማረ፤ ሕግን የሠራላቸው፤ ለኢያሱ ርስትን የሰጠው፤ ኖኅን የጠበቀው፤ አብርሃምን የመራው ከይስሐቅ ጋር የታሠረ፤ ከያዕቆብ ጋር እንግዳ የሆነ፤ ከዮሴፍ ጋር የተሸጠ፤ በዳዊት አድሮ የተናገረ፤ በነቢያት አድሮ ሕዝቡን ያስተማረ፤ እምቅድመ ዓለም ከአብ እንበለ እም (ያለ እናት) የተወለደ፤ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፤ የዘለዓለም ንጉሥ፤ ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ነፍስና ሥጋን ነሥቶ ፍጹም አምላክ  ወሰብእ የሆነ በሰው ባሕርይ ሰው የሆነ፤ እርሱ ነው፡፡ በመሆኑም የሥጋን አምላክ መሆን፤ የአምላክን ሰው መሆን በዚህ ተረዳን፤ ተገነዘብን፡፡

ጥምቀት ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ነው

ይኸውም “ወአመ በጽሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት ወገብረ በሕገ ኦሪት — የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፡፡)” (ገላ. 4፥4) በማለት አረጋግጦ አስረድቶናል፡፡ የለመኑትን የማይነሣ፥ የነገሩትን የማይረሳ ጌታ ቅድመ ዓለም በልብ ያሰበውን ድኅረ ዓለም በነቢያት ያናገረውን ለመፈጸም ሥጋ ለበሰ፤ ሰው ሆነ፡፡ መምህረ ትሕትና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሠላሳ ዘመን ሲሞላው አብነት ለመሆን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በመሄድ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስእጅ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡ ተጠምቆም የባሕርይ ልጅነቱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አስመስክሮ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፡፡ (ማቴ. 4፥1)

ጌታ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ሄዶ አጥምቀኝ ሲለው ቅዱስ ዮሐንስ “ስመ አብ ብከ፤ ወስመ ወልድ ለሊከ፤ ወስመ መንፈስ ቅዱስ ህልው ውስቴትከ ባዕደ አጠምቅ በስምከ ወበስመ መኑ አጠምቅ ኪያከ — አብ በአንተ ህልው ነው፤ ወልድም አንተ ነህ፤ መንፈስ ቅዱስም በአንተ ህልው ነው ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ፤ አንተን ግን በማን ስም ላጥምቅህ» ቢለው፤ «ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ — ብርሃንን የሚገልጽ የቡሩክ እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ይቅር በለን» «አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ — እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” እያልክ አጥምቀኝ አለው፡፡ (መዝ. 109/110፥4)

ቅዱስ ጳውሎስም “ወደምሰሰ ለነ መጽሐፈ ዕዳነ በሥርዐቱ እምዕድውነ — በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው» በማለት ገለጸልን (ቈላ. 2፥14)። ቅዱስ ያሬድም “ብርሃን ኮነ በልደቱ ወሰላመ ገብረ በጥምቀቱ — በልደቱ ጨለማው ተወግዶ ብርሃን ሆነ፤ በጥምቀቱም ሰላምን ሰጠን ሰላምን አደረገ አለ፤” አብ በደመና ላይ ሆኖ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር — አብ የምወልደው የምወደው የባሕር ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሲመሰክር፤ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ጸዐዳ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ታውቋል፤ ተረጋግጧል (ማቴ. 3፥17)፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ወልድ ለአብም ለመንፈስ ቅዱስም ቃላቸው በመሆኑ አንዱ በአንዱ ህልው መሆኑን በግልጥ አሳይቷል፡፡ እግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የአካል ስሙ፤ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ የግብር ስሙ፤ ልብ ቃል እስትንፋስ የኩነት ስሙመሆኑን ተረዳ፤ ተገለጠ፡፡

ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት ምክንያት፡-

  • ዮርዳኖስ ነቁ (መፍለቂያው ምንጩ) አንድ እንደሆነ ሁሉ፥ የሰው ሁሉ ነቁ አንድ አዳም በመሆኑ ነው፡፡
  • ንዕማን በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ (2ነገ 5፥14)
  • ኤልያስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል፡፡ (2ነገ. 2፥8-14)
  • እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ ((ኢያ. 3፥17)
  • የኤልሳዕ ደቀ መዝሙር ምሳሩ ከዛቢያው ወልቆ ከባሕር ቢገባበት ኤልሳዕ ቅርፍተ ዕፅ አመሳቅሎ ቢመታው መዝቀጥ የማይቻለው ቅርፍተ ዕፅ ዘቅጦ መዝቀጥ የሚገባውን ብረት ይዞት ወጥቷል፡ (2ነገ. 6፥1-7) ይኽም ሞት የማይገባው ወልደ እግዚአብሔር በለበሰው ሥጋ ሞቶ  ሞት የሚገባው አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው፡፡
  • ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ድኗል፡፡
  • ብፁዕ አብርሃም አርከ እግዚአብሔር ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ ዐራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሲመለስ ደስ ቢለው “በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃለከወሚመ ታርእየኒሁ ኪያሃ ዕለተ አው አልቦ ቢለው እሱንስ አታየውም ምሳሌውን ታያለህ አለው፡፡” አብርሃም ዮርዳናስን ተሻግሮ መልከ ጼዴቅ ኅብስተ በረከት ጽዋዓ አኰቴት ይዞ ተቀብሎታል (ዘፍ. 14፥18)፥ በማለት ትርጓሜ ወንጌል ላይ ታትቷል፡፡ ይህ ሁሉ ምሳሌ ምእመናንና ምእመናት አምነው ተጠምቀው ገነት፤ መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ ነው

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሠላሳ ዓመቱ መጠመቁ፥ አባታችን አዳም የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ ሳለ ልጅነቱን ስላስወሰደ ለዚያ ካሣ ለመሆን ነው።፡ በዚህም “አኮ ዘረከበ ጸጋ በተጠምቆቱ አላ ከመ ያብርህ መካናተ ወኀይል ማያተ ለእለ ሀለዎሙ ይጠመቁ ውስቴታ” እንዲል ሃይማኖተ አበው፡፡ (የተጠመቀውም ኀጢአት ኑሮበት፤ ከኀጢአት ለመንፃት ሳይሆን የሰው ሁሉ ጽድቅ እንደመርገም ጨርቅ ሆኖ ነበርና በጽድቁ ጽድቃችንን ሊያድስልን በጥቀቱ ጥምቀታችን ሊቀድስልን በዮርዳኖስ ተጠመቀ እንጂ በጥምቀት የሚያገኘው ጥቅም አልነበረም፤ የለምም፡፡

በመሆኑም ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት፤ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት ሲያድን ቸርነትን፤ ፍቅርን ርኅራኄን ትሕትናን በማስቀደም ነው፡፡ እነዚህም የክርስቶስ የባሕርይ ገንዘቦቹ ለሰው ልጅም ስጦታዎች ናቸው፡፡ “ከመ ንሕዮ በእንቲአሁ (እሱ ስለካሰልን እንድን ዘንድ) ወዝንቱ ውእቱ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር  (የእግዚአብሔር ፍቅሩ ይህ ነው፡፡ፍቅር መሆኑ እኛን መውደዱ ይኽ ነው) አኮ ንሕነ ዘአፍቀርናሁ አላ ውእቱ አፍቀረነ (አስቀድሞ እኛ የወደድነው አይደለም እሱ ወደደን እንጂ) ወፈነዎ ለወልዱ ይኅድግ ለነ ኃጣውኢነ (ፍቅሩ ይህ ነው፡፡ ኀጢአታችን ይቅር ይለን ዘንድ የባሕርይ ልጁን ወደዚህ ዓለም ሰዶታልና) አኀዊነ እመሰ ከመዝ አፍቀረነ እግዚአብሔር ወንሕነኒ ይደልወነ ንትፋቀር በበይናቲነ — ወንድሞቻችን እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁን እግዚአብሔር ወልድን እስከ መስጠት ድረስ ደርሶ እንዲህ ከወደደን እኛም እርስ በርሳችን ፍቅርን ልንይዝ ይገባናል በማለት የከራድዮን ዖፍጸዓዳ ምሳሌ ንጉሠ ይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስ የአንዱን በደል ሌላው እንዲያቃልለትና ይቅር እንዲለው በመፈቃቀር እንዲኖር አዟል (1ዮሐ. 4፥9-10) የጥምቀት ዓላማም ይህ ነው፡፡

ከላይ እንደተገለጸው የጥምቀት መሠረቱ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ትምህርትና ሥርዐት ያላለፉ ወይም ይህን ሥርዐት ያልፈጸሙ ሰዎች ክርስቲያን ተብለው መጠራት እንደማይችሉ የእግዚአብሔር ሕያው ቃሉ ይነግረናል፡፡ አምነው የተቀበሉትን የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣን ሰጣቸው፡፡ (ዮሐ. 1፥12)

ጥምቀት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም መኖሩን፤ አምጻኤ ዓለማትነቱን፤ በሥጋ መምጣቱን፤ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱን፤ በዚህ ዓለም ሠሳሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር መኖሩንና መመላለሱን፤ ይህን ዓለም ለማሳለፍ መምጣቱንና ይኽን ዓለም አሳልፎ መኖሩን የምናውቅብትና የምንረዳበት ምሥጢር ነው፡፡ ወአመርናክሙ ቦቱ ኀይሎ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወምጽአቶ ወሀልዎቶ — የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርሰቶስን ኀይልና መምጣት አስታወቅናችሁ ይላል፡፡ (2ጴጥ. 1፥16)

ስለዚህ ጥምቀት ክርስቲያን ለመሆን የክርስትናን ሃይማኖት፤ ቀኖና እና ትውፊት ተምሮ ዐውቆና አምኖ በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚጠመቁት የሃይማኖት መግለጫና ከእግዚአብሔር የሚወለዱትን ልጅነት መቀበያ ስለሆነ ነሢአ ሐዲስ ልደት፤ኅርየት (መመረጥ) ሕጽበተ ኀጢአት (ከኀጢአት መታጠብ፤ ከኀጢአት መንጻት) ይባላል፡፡ ሰዎች በሥላሴ ስም ተጠምቀው ከሥላሴ አዲስ ልደትን ተቀብለው ውሉደ እግዚአብሔር ሕዝበ ክርስቲያን ይባላሉ፡፡

ወደፊትም በጥምቀታችን በብሉይ ኪዳን የተነገረው ሐዲስ ኪዳን ተስፋ ትንሣኤ ሙታን፤ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህ ሐዲስ ኪዳን በቀለም ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተጻፈ፥ የኵነኔ ሳይሆን የጽድቅ አገልግሎት ፍሬ፥ ለጊዜው ሳይሆን ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር፤ ፍጹም ነፃነት ያለው ለተቀበልነው ሁሉ ማለትም በነፍስ ሕያዋን፤ ዘለዓለማውያን የምንሆንበት በጥምቀት በሚገኘው ንጽሐ ሥጋ፥ ንጽሐ ነፍስ፥ ንጽሐ ልቡና ነው፡፡ “ወብነ ባሕቱ ከመዝ ተስፋ በኀበ እግዚአብሔር በእንተ ክርስቶስ፡፡ ወኢይደልወነ ነኀሊ ለሊነ ለርእስነ ወኢምንተኒ፡፡ እስመ እምኀበ እግዚአብሔር ኀይልነ ዘረሰየነ ላእካነ ለሐዲስ ሕግ ወአኮ በሕገ መጽሐፍ አላ በሕገ መንፈስ እስመ መጽሐፍ ይቀትል ወመንፈስ ያሐዩ (በክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን፤ ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳች እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም”፡፡ (2ቆሮ. 3፥-4-6)

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀቱን ለምን በውኃ አደረገው?

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አማን አማን እብለከ ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይክል በዊዓ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር — ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ ካልተወለደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት አይቻለውም ብየ በእውነት እንደማይቻለው እነግርሃለሁ” ይላል ሕያው ቃሉ (ዮሐ. 3፥5)፡፡ ውኃም በዙፋን ካለ ንጉሥ በማሕፀን እስካለ ፀኑስ ድረስ የሚገኝ (ርኩብ) ነውና፡፡ ውኃ እድፍን ያነጻል፤ ጥምቀትም ኀጢአትን ያነጻል፡፡ በመሆኑም ጥምቀታችን ካህናት ዕለት ዕለት በሚለውጡት ማየ ገቦ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቀትን በዓል የምታከብረውና የምትፈጽመው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በረከተ ጥምቀት ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ዳግም ለማጥመቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵውያን ሊቃውንት በውኃ ተጠምቀን ዳግም ልደት ማግኘታችን መሠረት አድርገው ሲቀኙና ሲፈላሰፉ፡-

ድኅረ ተሰብረ አጽንኦ ለሰብእናነ ልሕኲት 

ለብሓዊ ክርስቶስ በማየ ሐዲስ ጥምቀት፤

ትርጒሙም፡-

«ሸክላ ሰውነታችን ከተሰበረ በኋላ ሸክላ ሠሪው ክርስቶስ በሐዲስ የጥምቀት ውኃ እንደገና ለውሶ ሠራው» በማለት ተራቀው አመስጥረው ተቀኝተውበታል፡፡ ስለዚህ በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት መብትና እድልን አግኝተናል ማለት ነው፡፡

በመሆኑም ጥምቀትን ስናከብር ከዚህ በታች የተጠቀሱትን እውነታዎች ተረድተን ነው፡፡

  • እግዚአብሔር ወልድ በ5500 ዓመተ ፀሐይ መጋቢት 29 እሑድ ቀን በዘመነ ዮሐንስ ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በድንግልና ተፀንሷል፡፡
  • እግዚአብሔር ወልድ በ5500 ዓመተ ፀሐይ ታኅሣሥ 29 ማክሰኞ በዘመነ ማቴዎስ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በድንግልና ተወልዷል፡፡
  • እግዚአብሔር ወልድ በ5530 ዓመተ ፀሐይ ጥር 11 ማክሰኞ ቀን በዘመነ ሉቃስ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ዘካርያስ እጅ ተጠምቋል፡፡
  • ጌታ በ30 ዓመቱ መጠመቁ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40 ቀን ያገኛትን ልጅነት አስወስዶ ነበርና ልጅነቱን እንደመለሰለት ለማጠየቅ በ30 ዓመቱተጠመቋል፡፡
  • ጌታእግዚአብሔር ወልድ በ5534 ዓመተ ፀሐይ መጋቢት 27 ዓርብ ቀን ተሰቅሏል፡፡
  • በበዓለ ጥምቀት ታቦታተ ሕጉ ከየቤተ ክርስቲያኑ ቤተ መቅደስ  ከእየ መንበሩ ተነሥቶ ወደየጥምቀተ ባሕሩ (ወደ ወንዝ) የሚወርድበት ምክንያት ጌታ በእደ ቅዱስ የሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ፈለገ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው፡፡

በአጠቃላይ ጥምቀት ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸው “ወአመ አስተርአየ ምሕረቱ ለእግዚአብሔር መፍቀሬ ሰብእ መድኀኒነ፡፡ አኮ በምግባረ ጽድቅነ ዳእሙ በምሕረቱ አድኀነነ በጥምቀት ዳግም ልደት ወተሐድሶ በመንፈስ ቅዱስ — ነገር ግን የመድኀኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መወደዱን በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለሐዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን” (ቲቶ 3፥4-5) የሚለውን መሠረት አድርገን እኛም በዚህ ዓለም በጥምቀት ሥርዐት በሃይማኖት ይቅር በመባባል በፍቅር፥ በንጽሕና፥ በጽድቅ ጸንተን እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አዞናል፡፡

 

ስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፤ አሜን።

 

ሊቀ ካህናት ደረጀ መንግሥቱ

የብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ

ልዩ ጸሓፊ

ስብከተ ወንጌልና የጥምቀት በዓል

1. የቃላት ትርጒም

“ስብከተ ወንጌልና የጥምቀት በዓል” በሚለው ርእስ ውስጥ በጋራና በተናጠል ትርጒም የሚሹ አራት ቃላት ይገኛሉ፤ እነዚህም ወንጌል፥ ስብከት፥ ጥምቀትና በዓል ናቸው፤ ስብከትና ወንጌል በአንድነት ተጣምረው “ስብከተ ወንጌል” የሚል ሐረግን ይፈጥራሉ፤ ይህ ሐረግም የራሱ ትርጒም ያስልገዋል፤ በተመሳሳይ መልኩ በዓልና ጥምቀት የሚሉት ቃላትም በአንድነት የሚሰጡት ትርጒም ተያይዞ ቀርቧል፡፡

1.1 ወንጌልናስብከተ ወንጌል

ወንጌል ማለት ምን ማለት ነው? ስብከት ማለትስ? ወንጌልና ስብከት የሚሉት ቃላት በአንድነት ተጣምረው ሲነበቡ “ስብከተ ወንጌል” የሚለው ሐረግ ምን ትርጒም ይሰጠዋል?

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ወንጌል የሚለውን ቃል ሲተረጒሙ ወንጌል (ወንጌላት ሲበዛ፥ በጽርዕ/ግሪክ “ዮአንጌሊዎን”፥ በዐረብ ኢንጂል ካሉ በኋላ) “በቁሙ ወንጌል፥ ብሥራት፥ ምሥራች፥ ሐዲስ ዜና፥ መልካም ወሬ፥ ደስ የሚያሰኝ ስብከት፥ አምላካዊ ቃል፥ ሰማያዊ ነገር፥ ምሥጢረ ሥላሴ፥ ምሥጢረ ሥጋዌ” ሲሉ ተርጕመውታል፤ በመጽሐፍነቱ ሲፈቱም፦ “መጽሐፍ፥ የመጽሐፍ ስም፥ የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ፥ እንደ ነገሥት አራት ክፍል ያለው፥ አራት ሰዎች የጻፉት” ይሉና “ፍቺው ብሥራት ማለት ነው” ይሉታል፡፡ ደስታ ተክለ ወልድ በበኩላቸው፦ “ወንጌል-የመጽሐፍ ስም፥ አራት ሰዎች የጻፉት፥ የክርስቶስን አምላክነት የሚያስረዳ መጽሐፍ፥ ትርጓሜው የምሥራች ማለት ነው” ይላሉ፡፡

የክርስቲያን እምነትና ጸሎትም በወንጌል እውነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ሃይማኖቱ “ሃይማኖት ወንጌላዊት”፥ ጸሎቱም “ጸሎት ወንጌላዊት” ተብሎ ተገልጧል ሃይማኖቱን በተመለከተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ “ከእናንተ መካከል ማንም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጸጋ የታጣ (የጠፋ፥ የራቀ) አይሁን፤ ይኸውም የምትመጣዋ ደስታ እና ወንጌላዊት ሃይማኖት ናት” ይላል፡፡

ከላይ የጠቀስናቸው መዛግብተ ቃላትና የሊቃውንት አባቶች ትርጒሞች እንደሚያስረዱን በግእዝና በአማርኛ ወንጌል የምንለው ቃል “ዮአንጌሊዎን” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ትርጒሙም “የምሥራች ቃል” ማለት ነው፡፡ መቅድመ ወንጌልም ቃሉን ሲተረጕም “ወንጌል ብሂል በልሳነ ጽርዕ ወትርጓሜሁ ስብከት” ይላል፤ ትርጒሙም “ወንጌል የሚለው ቃል በጽርዕ/በግሪክ ቋንቋ ነው፤ትርጓሜውም የምሥራች ማለት ነው” ይላል፡፡

ወንጌል ማለት የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን፥ መወለድ፥ ማደግ፥ መጠመቅ፥ አገልግሎት፥ ትምህርት፥ ተአምራት፥ ሞትና ትንሣኤውን፥ ዳግም ምጽአቱን በአጠቃላይ ሰውን ለማዳን ሰው ሆኖ ያደረገውን የማዳን ሥራ የሚያስተምር ትምህርት ነው፤ ስለዚህ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ሰውን ለማዳን ነው በማለት የሚታመን እምነትና የሚታወጅ እውነት ነው፤ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣበት ምክንያት ነው፤ ወንጌል የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ነው፤ ወንጌል ራሱ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ወንጌልን መስበክም ክርስቶስን መስበክ ነው፡፡

ወንጌልን ከጥንቱ ከመሠረቱ ከብሉይ ኪዳን ታሪክና ትምህርት አንጻር ስናየው በታሪክ፥ በሕግ፥ በትንቢት፥ በመዝሙር፥ በቅኔ፥ በምሳሌና በጥበብ መልኩ ሲሰበክ የኖረ ትምህርት ነው፤ በተለይ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ “መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ ዐይቶ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ” በማለት በብሉይ ኪዳን ተሠውሮ ያለውን የወንጌል መልእክት ያሳያል (ገላ. 3÷8) ፤ ክርስቶስም “አብርሃም አቡክሙ ተመነየ ይርአይ ዕለትየ ርእየሂ ወተፈሥሐ” ማለት “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ/ፈለገ፤ አየም፤ ደስም አለው” (ዮሐ. 8÷56) በማለቱ ነቢያት በዐይነ መንፈስ ዐይተው፥ በመንፈሰ ትንቢት አምነውትና ሰብከውት፥ በእርሱ ተደስተው ያለፉ መሆኑን ተናግሯል፤ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ወንጌል ሥረ መሠረቱ ጥንት መሆኑን ነው፡፡

ሆኖም ግን ትንቢቱና ተስፋው ተፈጽሞ አካላዊ ቃል ሰው ሆኖ በወንጌል መጻሕፍት ለመጀመሪያ ጊዜ “ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ” (ማር. 1÷14-15) ተብሎ እንደተጻፈው “ወንጌል” ክርስቶስ፥ ወንጌል ተስፋ መንግሥተ ሰማያት፥ ወንጌል የዘለዓለም ሕይወት እንደሆነ የሰበከው ክርስቶስ ነው፤ ከክርስቶስ የተማሩትን ደቀ መዛሙርቱ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ጸንተው እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ አዳራሱት፤ ይህም ወንጌል እስከ ዛሬ ድረስ እየተሰበከ ከእኛ ዘመን ደርሷል፡፡

1.2. ስብከትና ስብከተ ወንጌል 

ስብከት የሚለውን ቃል ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “ሰቢክ፥ ሰቢኮት” በሚለው ንኡስ አንቀጽ ሲፈቱት “መስበክ፥ ማብሠር፥ ማስተማር፥ በታላቅ ቃል መጮኽ፥ ማሰማት፥ መልፈፍ፥ መለፍለፍ፥ ዐዋጅ መንገር፥ ማዜም፥ መዘመር፥ ማውራት፥ መመስከር” ይሉታል (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፥ ገጽ 845)፤ ወንጌል የሚለውን ቃል ስንተረጒም ወንጌል ማለት ስብከት ማለት ነው ብለን ከመቅድመ ወንጌል ማስረጃ ዐይተናል፤  በዚህም መሠረት ስብከት ማለት ወንጌል፥ ወንጌል ማለትም ስብከት ማለት እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡

ወንጌል የክርስቶስ የማዳን ሥራ፥ ወንጌል ራሱ ክርስቶስ ስለ ሆነ “ስብከተ ወንጌል” የክርስቶስን የማዳን ሥራ መስበክ፥ ማወጅ፥ ማስተማር፥ መመስከር ይሆናል፤ ይህም ማለት ክርስቶስን ክርስቶስን መስበክ ፥ ማወጅ፥ ማስተማር፥ መመስከር ነው፡፡

የጥምቀት በዓላችን የክርስቶስን የማዳን ሥራ የምንሰብክበት፥ የምናውጅበት፥ የምናስተምርበት ሃይማኖታዊ ሥርዐታችን፥ ክርስቶስን የምንሰብክበት ወንጌላችን ነው፤ ስብከተ ወንጌልና የጥምቀት በዓል በሚለው በዚህ አጭር ጽሑፍ ለማሳየት የተፈለገውም ይህን ነጥብ ነው፡፡

1.3. ወንጌልን የመስበክ ኀላፊነት የማነው?

ስብከተ ወንጌል በቤተ ክርስቲያን እንደ እልቅና፥ እንደ ጸሓፊነት ወይም እንደ ሒሳብ ሹምነት/ ሠራተኛነትና እንደ ቁጥጥር ወዘተ አንድ የሥራ ዘርፍ አይደልም፤ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ሥራዎች ሁሉ መሠረትና የሁሉም ምእመናን ኀላፊነት ነው፤በተለያየ መንገድ ሁላችንም ሰባክያነ ወንጌል ነን፤ ስብከተ ወንጌል እምነትንና እውቀትን እንጂ ሹመትን አይጠይቅም፤ ክርስቶስ “ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ብሎ የተናገረው ቃል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለክርስያኖችና ወንጌልን መስበክ ለሚፈልጉ ሁሉ መመሪያ ሆኖ ይኖራል፡፡

ይህ ማለት ግን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ዕውቀት ፥ እምነትና ችሎታ ሳይኖራቸው፥ ሥርዐትንና ሕግን ሳይከተሉ እንደፈለጉ መስበክ ይቻላል ማለት አይደልም፤ ወንጌልን የመስበክ ኀላፊነት ከሁሉም ክርስቲያኖች የሚጠበቅ አምላካዊ ትእዛዝ መሆኑን ለመናገር ነው እንጂ፤ ይህን የተረዳው ሐዋርያ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ።” (1ቆሮ. 9÷6) ሲል የጻፈውም በዚህ ምክንያት መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡

1.4. ጥምቀትና የጥምቀት በዓል

ጥምቀት፦ በዓልም፥ እምነትም ምሥጢርም ነው። በበዓልነቱ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ፥ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን ዓላማ የአደባባይ በዓል አድርገን በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐት መሠረት እናከብረዋለን፤ በእምነትነቱ “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት” ማለትም “ለኀጢአት ሥርየት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” ብለን እንመሰክራለን፤ በምሥጢርነቱ ደግሞ በካህን እጅ፥ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በውኃ ይፈጸማል፤ በዚህም ተጠማቂው ከእግዚአብሔር ዳግም ይወለዳል፤ ይህ የመዳን ምሥጢር የሆነው ጥምቀት“ምሥጢረ ጥምቀት” ተብሎ ከአምስቱ አዕማደ ምሥጢር አንዱ ሆኖ ይቈጠራል፡፡

በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ትምህርት መሠረት በዓል ማለት ለመታሰቢያነት የሚደረግ አፍኣዊ እና ልማዳዊ ሥርዐት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ማዳን የምንሳተፍበት የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ነው፤ የጥምቀት በዓልም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስንማንነትና የሥላሴን ምሥጢር ያወቅንበት፥ ክርስቶስን አምነን ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበት፥ በማዳን ምሥጢሩ የምንሳተፍበት፥ የቤተ ክርስቲያን አካል የሆንንበት ምሥጢር ነው፡፡

2. የጥምቀት በዓልንና ስብከተ ወንጌልን የሚያስተሳስሩ ነገሮች ምን ምን ናቸው?

 

2.1. የጥምቀት በዓል የተመሠረተው በወንጌል ትምህርት ላይ ነው፡፡

አራቱም ወንጌላት ከመዘገቧቸው የወንጌል ታሪኮች አንዱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ነው፤ በማቴ .3÷13-17፤ ማር.1÷9-11፤ሉቃ.3÷21-22 እና ዮሐ.1÷32-34 ተመዝግቦ የምናገኘው የወንጌል ቃል ለዚህ ማስረጃ ይሆናል፤ የጥምቀት በዓል የወንጌል ትምህርት የቤተ ክርስቲያንም ሕይወት መሆኑን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ምእመናንም ሆኑ ከቤተ ክርስቲያን በአፍኣ ያሉ በዓሉን የሚመለከቱ ሰዎች ሁሉ ሊረዱት ይገባል፡፡

 

በጥምቀቱ ሰማያት ተከፍተዋል፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ዐርፏል፤ አብ ከሰማያት “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ተናግሯል፤ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር በዚህ ተገልጧል፤ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቀትን በዓል ስታከብር እምነቷንና ትምህረቷን የመሠረተችበት የወንጌል ትምህርት ይህን ነው፤ በመዝሙሮቿ፥ በቅዳሴዋና በሌሎችም የበዓሉ መገለጫ ሥርዐቶች ሁሉ የምታውጀው ይህን የወንጌል ቃል ነው፡፡

2.2. በጥምቀት በዓል የሚዘመሩ የግእዝ መዝሙሮች የክርስቶስን ወንጌል የሚሰብኩ ናቸው፡፡

ቅዱስ ያሬድ በዜማዎቹ ሁሉ በሦስት መንገዶች ወንጌልን ሰብኳል፤ አንደኛ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል ቀጥታ በመጥቀስና በአስደናቂ ዜማ በማዜም፥ ሁለተኛ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባባት በትርጓሜ በማብራራትና ሦስተኛ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት በሕይወቱ በመኖር ናቸው፤ የጥምቀትን በዓል በሚመለከትም ቅዱሳት መጻሕፍትን ቀጥታ በመጥቀስና ምሥጢራቸውን በማብራራት ካስተማራቸው ዜማዎች በመጥቀስ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀትን በዓል ወንጌል እንደምትሰብክበት ብቻ ሳይሆን ወንጌል አድርጋ እንደምትኖረው ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡

ሀ) “ኀዳፌ ነፍስ ለጻድቃን ወተስፋ ቅቡፃን ክርስቶስ አስተርአየ ውስተ ዓለም ፤ እም ድንግል ተወልደ ክሡተ ኮነ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ ከዊኖ ሰብአ በዮርዳኖስ ተጠምቀ” (ትርጒም) “ለጻድቃን የነፍስ አሻጋሪ/መሪ/አስተማሪ (ጠባቂ)፥ ተስፋ ለቆረጡት ተስፋቸው ክርስቶስ በዚህ ዓለም ተገለጠ፤ ከድንግል ተወለደ፤ለዘመዶቹ እየታዘዘም በግልጥ ታየ፤ሰው ሆኖ በዮርዳኖስ ተጠመቀ”  (ዋዜማ ዘጥምቀት)፡፡

ለ) “ክርስቶስ ተወልደ፤ ክርስቶስ ተጠምቀ፤ ወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ፤ እሙነ ኮነ ለፀሐየ ጽድቅ አስተርእዮቱ አማን መንክር ስብሐተ ልደቱ/ጥምቀቱ፡፡” ትርጒም “ክርስቶስ ተወለደ፤ ክርስቶስ ተጠመቀ፤ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስም ዳግመኛ ወለደን፤ የጽድቅ ፀሐይ (ክርስቶስ) መገለጡ እውነት (የታመነ) ሆነ፤ በእውነት የልደቱ (የጥምቀቱ) ክብር የሚያስደንቅ ነው፡፡” (ምልጣን)

ሐ) “ነአምን በአብ ወነአምን በወልድ ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ፤ እማርያም ዘተወልድ አፍቂሮ ኪያነ መጽአ ኀቤነ ፤ ዘነቢያት ሰበኩ ለነ በዮርዳኖስ ተጠምቀ ከመ ይፈጽም ኵሎ ሕገ ሰብእ ፤ አስተርአየ ገሀደ፡፡” ትርጒም “በአብ እናምናለን ፤ በወልድም እናምናለን፤ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፡፡ ከማርያም የተወለደው እኛን ወድዶ ወደእኛ መጣ፤ ነቢያት የሰበኩልን እርሱ ሕግን ሁሉ ይፈጽም ዘንድ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፤ ተገልጦም ታየ፡፡” (አቡን)

መ) “አስተርአየ ዘኢያስተርኢ፤ ኮነ እሙነ አስተርእዮቱ ለመድኀኒነ ክርስቶስ፤ እሙነ ኮነ አስተርእዮቱ፤ እምድንግል ተወልድ፤ እሙነ ኮነ አስተርእዮቱ፤ በሥጋ ረቂቅ እሙነ ኮነ አስተርእዮቱ፤ በሠላሳ ክረምት በዮርዳኖስ ተጠምቀ በበሕቅ ልኅቀ፡፡” ትርጒም “የማይታየው ታየ፤ መገለጡም የታመነ ሆነ፤ ከድንግል ተወለደ፤ መገለጡም የታመነ ሆነ፤ ረቂቅ የሆነው እርሱ በሥጋ ተወለደ፤ መገለጡም የታመነ ሆነ፤ በሠላሳ ዓመቱ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፤ በየጥቂቱም አደገ፡፡”

ከላይ ያቀረበኋቸው የቅዱስ ያሬድ ዜማዎች በጥምቀት በዓል ከሚዘመሩ መዝሙሮች የተወሰኑትን ለማሳያ ይሆኑ ዘንድ ነው፤ እነዚህ መዝሙሮች ሁሉም በሐዲስ ኪዳን፥ በተለይ ደግሞ በወንጌል ትምህርት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ወንጌልን ያነበበ ሁሉ በቀላሉ ይረዳቸዋል፡፡ መልእክታቸውም፡-

  1. የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ መገለጥ (አስተርእዮ) ይባላል፤ ቅዱስ ዮሐንስ ክርስቶስን በማየ ዮርዳኖስ ሲያጠምቀው ማንነቱን ለእስራኤል እየገለጠው/እያሳወቀ ነበር፤ በዮሐ.1÷32 “ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ” ይላል፤ በቍጥር 31 እና 33 ላይ ሁለት ጊዜ ዮሐንስ “እኔም አላውቀውም ነበር” ብሏል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ክርስቶስነቱ/መሲሕነቱ/ እና የእግዚአብሔር ልጅነቱ ተገለጠለት፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ሲያርፍበት ዐይቶና አብ የምወድደው ልጄ ይህ ነው ብሎ ሲመሰክር ሰምቶ ከዚህ በኋላ “እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬያለሁ” አለ (ዮሐ.1÷34)፡፡ መጀመሪያ ዮሐንስ ለእስራኤል ገለጠው፤ ዛሬ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀትን በማክበርና ወንጌልን በመስበክ ለዓለም ሁሉ ትገልጠዋለች፤ ያመነበትም የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፡፡
  1. የክርስቶስ መጠመቅ እኛን ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም ለመውለድ የተደረገ የማዳን ሥራው ነው፤ “ወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ” ማለትም “ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ወለደን” የሚለው የቅዱስ ያሬድ ትምህርት ይህን ያስረዳል፡፡
  1. የክርስቶስ ጥምቀት የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሦስት አካላት አንድ አምላክነት የተገለጠበት ምሥጢር ነው፤ በወንጌል ክርስቶስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ያረፈበት መሆኑና አብም በደመና የምወድደው ልጄ ይህ ነው ማለቱ ይታወቃል፤ ይህን የወንጌል ትምህርት መሠረት አድርጋ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ የጥምቀት በዓል “ነአምን በአብ ወነአምን በወልድ ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ” እያለች ትዘምራለች፤ በዚህ መዝሙርም ወንጌልን ትሰብካለች፤ እምነቷን ለዓም ሁሉ ትመሰክራለች፡፡
  2. በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ የጠጠመቀው ክርስቶስ አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት የተሰበከውና ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ ነው፤”ነቢያት የሰበኩልን እርሱ ሕግን ሁሉ ይፈጽም ዘንድ በዮርዳኖስ ተጠመቀ” የሚለው የመዝሙሩ ሐሳብ ይህን ያረጋግጣል፡፡

እነዚህ ማሳያ አድርጌ ያቀረብኋቸው መዝሙሮች የጥምቀት በዓል የወንጌል መስበኪያ መድረክ ብቻ ሳይሆን ራሱ ወንጌል እንደሆነ ያመለክታሉ፤ እነዚህ መዝሙሮች የያዙትን ምሥጢር ሊቃውንቱ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑባቸው፥ ለራሳቸው ወንጌልን ሲማሩባቸውና ግእዝ ቋንቋን ለሚሰሙ ተማሪዎቻቸው ሲያስተምሩባቸው እንደኖሩ ሁሉ አሁን ደግሞ ሕዝብ በሚሰማው ቋንቋ በመተርጐምና ከምንጫቸው ከወንጌል ጋር በማስተሳሰር ማስተማር ይገባናል፤ ሁሉም ነገር እያለን የቤተ ክርስቲያንን ጸጋና ሀብት እንደሚገባው ባለማሳወቃችን ሌሎች ባለማወቅም ሆነ በክፉት ቤተ ክርስቲያናችንን ሲያሳንሱ መስማት እየተለመደ ስለመጣ ይህን ተገቢ ያልሆነ ነቀፋ ማራቅ ይገባል፤ ይህ የሚቻለው ደግሞ ይህን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ሀብት በማስተማር ነውና ሁሉም ሊተጋ ይገባል እላለሁ፡፡

2.3. የጥምቀት በዓል ከዘጠኝ ዐበይት (ታላላቅ) የጌታ በዓላት አንዱ ነው፡፡

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን እምነትና ትምህርት  ከምትጠብቅባቸውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ከምታስተላልፍባቸው መንገዶች መካከል የጥምቀትን በዓል የምታከብርበት በዓል አንዱ ነው፤ በወንጌል ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማወቅ ደግሞ ከዘጠኝ ዐበይት (ታላላቅ) የጌታ በዓላት አንዱ ጥምቀት መሆኑ አስረጅ ይሆነናል፤ እነዚህ ዐበይት በዓላትም በመጋቢት 29 ቀን የሚከበረው ትስብእት (ሰው መሆኑ)፥ ታኅሥሥ 29 (ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ 28 ቀን) የሚከበረው ልደት፥ ጥር 11 ቀን የሚከበረው ጥምቀት፥ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበረው ደብረ ታቦር ፥በቀመር የሚገኙት  ሆሳዕና፥ ስቅለት፥ ትንሣኤ፥ ዕርገትና ጰራቅሊጦስ ናቸው። እነዚህ በዓላት ሁሉም እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን በሠራቸው ሥራዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ በዚህም ጥምቀት ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ሰው ሆኖ ከሠራቸው ታላላቅ የማዳን ሥራዎች አንዱ ነውና እንደ ስቅለቱና ትንሣኤው ሁሉ ከፍ አድርገን እናከብረዋለን፤ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለመስበክም ሆነ ለመኖር ከዚህ የበለጠና የከበረ የላትም፡፡

2.4. ጥምቀት በዓል ሰፊ የሆነ የስብከተ ወንጌል መድረክ ነው፡፡

የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል ከመሆን አልፎ በሀገር ውስጥም ሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምትገኝበት ቦታ ሁሉ የምታከብረው በዓል ነው፤ ከዚህም አልፎ በክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች እንኳን ቢሆኑ የእግዚአብሔርን ማዳን ሊያዩና ሊሰሙ የሚችሉበት ሰፊ መድረክ ነው፤ ለዚህም በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ ፥ የባህልና የትምህርት ድርጅት ((UNESCO) መመዝገቡ አንድ ማስረጃ ይሆናል፡፡

በበዓሉ የሚፈጸሙ ነገሮችም በምሳሌነት የሚያስተምሩት ስለ ክርስቶስ ነው፤ በየስፍራው ሁሉም ምእመናን በአንድነት ስፍራ የሚገናኙበት ታቦታትን ከመንበራቸው በማውጣትና ውኃ ባለበት ቦታ በማሳደር፥ በዚያ ቦታም ማኅሌት በመቆምና ቀድሶ በማቁረብ የምንፈጽመው ሃይማኖታዊ ሥርዐት ጌታችን ከገሊላ ዮሐንስ ያጠምቅ ወደ ነበረበት ወደ ዮርዳኖስ በመሄድ የተጠመቀበትን የትሕትና ጉዞ የሚሰብክ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ምንም ነገር ስታደርግ ያለምክንያት አታደርግም፤ በሥርዐተ አምልኮትዋ ውስጥ የምትፈጽማቸው ነገሮች ሁሉ የጌታችንን የማዳን ሥራ ለመግለጥ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡

ወንጌልን ለመስበክ፥ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ ለማወጅ ከዚህ የበለጠ ታላቅ እድልና ሰፊ መድረክ ሊኖር አይችልም፤ አባቶቻችን ሰውን ከእግዚአብሔር ጋርና ሰውን ከሰው ጋር በፍቅር የሚያገናኙ እንደዚህ ዐይነት በዓላትን የሠሩት በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተመሥርተው ለመሆኑ ጥርጥር የለበትም፤ እኛም እግዚአብሔር ለአባቶቻችን የሰጠውን ጥበብ ዐውቀን፥ ይህን ሰፊ እድል እንደሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

3. ማጠቃለያ

የጥምቀት በዓል በቅዱስ ወንጌል ትምህርት ላይ የተመሠረተና ራሱም ወንጌል እንደሆነ ተመልክተናል፤ አባቶቻችን የጥምቀትን በዓል ሲሠሩ ዋና ዓላማቸው ሰዎች ሁሉ የክርስቶስን የማዳን ሥራ ዐውቀውና አምነው ከእግዚአብሔር ጋር እንደኖሩ ለማስተማርና በበዓሉም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ለመሆን ነው፡፡

በዚህ ዘመን ያለን የቤተ ክርስቲያን ልጆችና አገልጋዮችም ይህን ጠንቅቀን ዐውቀን በዓለ ጥምቀትን በወንጌል ቃል እንደ ተገለጠው የክርስቶስ ትምህርት ልናከብረው ይገባል፤ በፍትሐ ነገሥት ለካህናት መስፈርት ሲቀመጥ ከተገለጡት ነገሮች አንዱ “ካህን አምላካውያት መጻሕፍትን ይልቁንም አራቱን ወንጌላት የማያውቅ ይሆን ዘንድ አይገባም” ይላል፤ “ይልቁንም ዐርባእቱ ወንጌላትን ማወቅ አለበት” የሚለው ቃል ካህን በሚሠራው ሥራ ሁሉ የወንጌልን ልዩነትና በቤተ ክርስቲያንም የተሰጣትን ልዩ ቦታ ማገልገል እንደሚገባው የሚያመለክት ነው። ከዚህ አንጻር ካህናት የቤተ ክርስቲያን በዓላት በዋናነት የወንጌል ትምህርት የሚሰጥባቸው፥ ራሳቸውም በተግባር የሚታዩ ወንጌል ሥራዎች መሆናቸውን ተረድተው በበዓላት ወቅት ሌሎች ከበዓሉ ጋር የማይሄዱ ተግባራት በተቻለ መጠን መቀነስ ወይም ማስወገድ ይገባቸዋል፡፡

ወጣቶችም የአባቶቻቸውን መንፈሳዊ ጥበብና ክርስቲያናዊ መንገድ ተከትለው የጥምቀት በዓልን በልዩ መንፈሳዊ ሥርዐት፥ ሙሉ ትኵረታቸውን በክርስቶስ ትምህርትና ትእዛዝ ላይ አድርገው ሊያከብሩት ይገባል፤ በዚህ ዘመን ወጣቱ ከሚደነቅባቸው ነገሮች አንዱ የቤተ ክርስቲያን በዓላትን የሚያደምቅበት ልዩ ሥርዐት ነው፤ ይህ በመንፈሳዊ ትምህርትና ሥርዐት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

በበዓላት ወቅት በፍቅርና በአንድነት መብላት መጠጣት የተለመደና ከጥንት ጀምሮ በእስራኤል ልማድ የሚታወቅ ነገር ቢሆንም ከበዓሉ ጋር የማይሄዱ ስካርና ጭፈራ ዐይነት ተግባራትን ምእመናን ሊርቋቸው ይገባል፤ የበዓለ ጥምቀት ዋና ጉዳይ የክርስቶስን የማዳን ሥራ ማወጅ፥ ክርስቶስን ማመስገን፥ የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር ለዓለም ማሳየት ነውና በዚህ ዋና ጉዳይ ላይ ትኵረት አድርገን ጥምቀትን ልናከር ይገባል በማለት መልእክቴን በዚህ እፈጽማለሁ፡፡

 

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያ ሀገራችንን፥ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!

 

መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር

በመ/ፓ/ ጠ/ቤ/ክህነት ስብከተ ወንጌልና

ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሰባኬ ወንጌል

ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ

፩.ሃይማኖተ ኦሪት

በአንድ እግዚአብሔር ማመን ሃይማኖተ ኦሪት ወይም ሃይማኖተ አይሁድ ይባላል፡፡ኢትዮጵያ ነገደካም፣ ነገደሴም፣ ነገደ እስራኤል(1) የተባሉ ሕዝቦች ከሰፈሩባት ጊዜ ጀምሮ ሃይማኖተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማመን) የታወቀባት ሀገር መሆንዋ ብዙዎች የታሪክ ምንጮች ያስረዳሉ(2) በተለይም ክብረነገሥት ተባለውን ታሪክ መጽሐፍ መሠረት አድርገው የተጻፉ ታሪክ መዛግብት ቀጥተኛ ጊዜውን በመግለፅ በአንድ እግዚአብሔር ማመን በኢትዮጵያ የተጀመረው በአንድሺህ ዐመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ መጀመሪያ በንግሥተ ሳባ እና በልጅዋ በቀዳማዊ ንጉሥ ምኒልክ መሆኑንያስረዳሉ፡፡(3) መጽሐፍ ቅዱስን ግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰለሞንን ለመጐብኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ እንደ ነበረች ያስረዳል፡፡(4) ክብረ ነገሥት የተባለውም የታሪክ መጽሐፍ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አጕልቶ በመግለፅ ንግሥተ ሳባ ከንጉስ ሰለሞን ጸንሳ ወደ ኢትዮጵያ መመለስዋን፣ በኃላም ልጅዋ ምንሊክ ተወልዶ ለአካለ መጠን ሲደርስ ወደኢየሩሳሌም  በመሄድ ከአባቱ ጋር ተገናኝቶ በሚመለስበት ጊዜ በአባቱ መልካም ፍቃድ ከሕዝበ እስራኤል የተወጣጡ የበኩር ልጆች የሰዶቀ ልጅ አዛሪያስን፣ሌዋውያን መምህራን ኦሪትን፣ ካህናትንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ እንደተመለሰና በአክሱም እንደተቀመጠ ዘርዝሮ ያስረዳል፡፡ከዚህጊዜጀምሮየኢትዮጵያህዝብሃይማኖትኦሪትን (ሃይማኖተአይሁድን )አምኖካህናተኦሪት፣ሴማውያን በአክሱም ታቦተ ጽዮንን ያገለግላሉ፣ ሕገ ኦሪትን ያስተምሩ ነበር(5) ይህ ይታወቅ ዘንድ ከ ሕገ ኦሪት ፣ ሥርዐተ አይሁድ፣ ባህለ አይሁድና ልማደ አይሁድ በኢትዮጵያ ህዝብ ሰርጸው ይገኛሉ፡፡(6) ይህ ሃይማኖተ ኦሪት፣ ሥርዐተ አይሁድና አይሁዳዊ ባህል ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብና ሕዝበ ኢስራኤል የረዥምየታሪክ ትስስር እንዲኖራቸው አድርጎአቸዋል ከዚህም ጋር የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ዘመናት ሃይማኖተ ኦሪትን (ሃይማኖተ አይሁድን ) አምኖ መኖሩን ያስረዳሉ፡፡ጠቅለል ባለ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅድመ ሃይማኖተ ክርስትና በሃይማኖተ ኦሪት (ሃይማኖተ አይሁድ) ለረዥም ዘመናት መኖሩን በሁለት ዐበይት የታሪክ ነጥቦች መረጋገጥ ይቻላል፡፡

  1. ከዚህበላይየተገለጹትሕገኦሪት፣ሥርዐተአይሁድናባህለአይሁድበኢትዮጵያህዝብህልው(አኗኗር) ሰርጸውመገኘታቸውነው፡
  2. ሕጽዋ ለንግስት ሕንደኬ (የንግሥት ህንደኬ ጃንደረባ) ለአምልኮተ እግዚአብሔር (ለእግዚአብሔር ለመስገድ ) ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱና ከብሉይ ኪዳን ክፍል ምጽሐፈ ኢሳይያስን ሲያነብ መገኘቱ ነው ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሕዝቦች ቀድሞ በሃይማኖተ እግዚአብሔር የተመሰረተ ስለነበረ ሃይማኖተ ክርስትናን ለመቀበል ያዳገተው አንድም ነገር አልነበረም፡፡

፪. ሃይማኖተ ክርስትና በኢትዮጵያ

፪.፩. ሕጽዋ ለሕንደኬ

በኢትዮጵያየሃይማነተክርስትናታሪክመነሻውበግብረሐዋሪያትምዕራፍ፰፡፹፮-፵የተመዘገበውመልእከተመንፈስቅዱስናሐዋርያዊተልእኮነው፡፡ይህየመጽሐፍቅዱስክፍልህንደኬየምትባልንግስትበአንደኛውመቶክፍለዘመንበኢትዮጵያነግሳእንደነበረ ‹‹ሕጽዋለህንደኬ›› በሚባል የሚታወቅ አንድ የዕቃ ግምጃ ቤት አዛዥ(ሹም) እንደነበራት ያስረዳል የሀው ሕጽዋ ለንግስት ህንደኬ (ንግሥት ህንደኬ ጃንደረባ) እግዚያብሔር ሊሰግድ በ፴፬ ዐ/ም ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር(7) የኢትዮጵያ ሕዝብ ከላይ እንደተገለፀው ከ1000 ዐመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ሕገ ኦሪትን ፣ሥርዐተ ኦሪትን ማክበርና እግዚአብሄርን የማምለክ ልምድ ነበረውና ፡፡ሕጽዋ ለንግስት ህንደኬ ለአምልኮተ እግዚያብሔር ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ጊዜ መልአከ እግዚአብሄር ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ የሆነው ፊሊጶስን ‹‹ከኢየሩሳሌምወደጋዘየሚወስድውንመንገድሂድ›› ብሎት ሲሄድ ይህን ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘው፡፡ ኢትዮጵያዊ የንግስቲቱ ጃንደረባ ለእግዚያብሔር ሰግዶ ሲመለስ በሰረገላው ተቀምጦ መፅሐፈ ኢሳያስ ያነብ ነበር፡፡በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ጃንደረባው የተቀመጠበትን ሰረገላ ተከተለው ብሎ አዘዘ፡፡ፊሊጶስም ይህን የመንፈስ ቅዱስን ትዕዛዝ ተቀብሎ ሮጠ ሰረገላው ደረሰበት፡፡

ፊሊጶስ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ቍ 7-8 ያለውን ቃለ ትንቢት ሲያነብ ሰምቶ ጃንደረባውን ‹‹የምታነውንታውቃለህን›› ብሎ ጠየቀው ጃንደረባውም ያስተማረው ሰው እንዳለ ነበረና የንባቡን ጥልቅ ምስጢር እንደማያውቅ ገልጾ መለሰለት፡፡ፊሊጶስም እንደማያውቅ  ከገለጸለት መነሻ ሐሳብ ከልደቱ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያለውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ አስረዳው፡፡ጃንደረባው ቀድሞውም በሃይማነኖት እግዚአብሔር የሚኖር ነበር፡፡ፊሊጶስ ትምህርት ረክቶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወልዳ እግዚአብሔር እንደሆኑ ወዲያውኑ በፍጹም ልቡ አመነ፤በአፉም መሰከረ፡፡አያይዞም ፊሊጶስ እንዲያጠምቀው ጥያቄ አቀረበ፡፡ ፊሊጶስም ጃንደረባው ለመጠመቅ ሙሉ ፍቃደኛ መሆኑንና በመንፈስ ቅዱስ የተላከበት ዐላማ መሆኑን በመገንዘብ ወዲያውኑ ውሀ ካለበት ወንዝ ወስዶ አጠመቀው፡፡ኢትዮጵያዊው ጃነደረባም የተነገረውን የእግዚአብሔር ቃል

በመረዳቱ፤ ሃይማኖተ ክርስትናን በማመኑና በመጠመቁ ደሰ እያለው ወደአገሩ ተመለሰ8፡፡ይህ በግብረ ሐዋርያት ምዕራፍ ፰፡፳፮የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ነው፡፡

በዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ የተሌዩ መሠረተውያን ነጥቦች መኖራቸውን እንገነዘባለን፡፡ ከነዚህ አንዱ መሠረታዊ ሐሳብ ፈቃደ እግዚአብሔር ነው፡፡ከላይ በተገለፅው የግብረ ሐዋሪያት ክፍል (ግብ.ሐዋ.ም ፰.፹፮) መልአከ እግዚአብሔር ፊሊጶስ ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ወደ ጋዛ እንዲሄድ መንገሩና መንፈስ ክዱስ በዚህ በጋዛ መንገድ ላይ የሚጓዘውን የጃንደረባው ሰረገላ ተከትሎ እንዲሄድ ፊሊጶስን ማዘዙ ክርስትና ሃይማኖትና ጥምቀት ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሐዋሪያት በቀጥታ እንዲተላለፍ የእግዚያብሔር ፈቃድ መሆኑን ያሳያል፡፡ሁለተኛው የዚህ ክፍል መሠረታዊ ሐሳብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖትና የልብ ቅንነት ነው፡፡ኢትዮጵያዊው የንግስት ህንደኬ ጃንደረባ ለእግዚያብሕር ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱና መጽሐፈ ኢሳያስን ሲያነብ መገኘቱ ከሚያሳየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖት በተጨማሪ ፊሊጶስ ጃንደረባውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምስጢረ ሥጋዌ ባስተማረው ጊዜ እንደ አሕዛብ ወይም እንደ አይሁድ ሳይጠራጠር፣ ሳይከራከር በአንድ ጊዜ በፍጹም ልቡ አምኖ፣ በአፉም መስክሮ መጠመቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌላው ዐለም ቀድሞ በሃይማኖተ እግዚያብሔር የተመሠረተ ቅንና ጽኑዕ ልቡና ያለው ሕዝብ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሃይማኖተ ክርስትናን አምኖና ተጠምቆ ወደ አገሩ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኃላ ፊሊጶስ ያስተማረውን ትምህርተ ክርስትና ያጠመቀውን ጥምቀት ከቤተ መንግሥት ጀምሮ በኢትዮጵያ አስተምሮአል፡፡(9) ሕጽዋ ለህንደኬ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ ካስተማረበት ከ፴፬ ዓ/ም ጀምሮ ሃይማኖተ ክርስትና እና ጥምቀት በኢትዮጵያ እንደተመሠረተ የማይጠራጠር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐቅ ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ሊቅ መጽሐፈ ምሥጢር በተባለው ድርሰታቸው ‹‹ጥምቀትን ያመጣልን የንግሥት ህንደኬ መጋቢ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ነው›› በማለት ጃንደረባው አምኖና ተጠምቆ ወደ አገሩ ከመጣ በኃላ ይህን ሃይማኖተ ጥምቀት ማስተማሩን ገልጸዋል(10)፡፡ይህን የአባ ጊዮርጊስ ገለጻ በመከተል የጻፉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ብዙዎች ናቸው፡፡ከነዚህም መካከል አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ የተባሉ ‹‹መርሐ ልቡና›› በተባለ መጽሐፋቸው የሚከተለውን ጽፈዋል፡፡

‹‹ጌታችን ባረገ 3ኛው ዘመን የገርሳሞት ንግሥት (በግብረ ሐዋሪያት ህንደኬ የተባለችው) የእርሷ ባለሟል መኰንን ጃንደረባ ስለጌታችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ ነገር ወደ ኢየሩሳሌም ተልኮ ሄዶ አምኖ ተጠምቆ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሃይማኖትንና ጥምቀትን አስተማረ፡፡(ግብ ሐዋ 8፡26-39)

ነገር ግን በዚያ ጊዜ የተጻፈ ወንጌል ስላላገኘን በቃል ያለ ይረሳል በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል እንደተባለ የወንጌል ትምሕርት በቃል ብቻ ሲነገር ነበረ፡፡እያደረ ግን እየጠፋባቸው እምነትንና ጥምቀትን ብቻ ይዘው እስከ 317 ዓ/ም ተቀመጡ፡፡በ317 ዓ/ም አብርሀና አጽብሐ ሁለት ወንድማማቾች በነገሡ በ11ኛ ዐመት በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ሃይማኖትና ጥምቀት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ሠለጠነ እንጂ አባ ሰላማ ቀድሞ ያልነበረውን ጥምቀት ያመጣ አይመስልም››(11)

በጽሑፍ የገለጸው ይህ ሐሳብ ክርስትና ሃይማኖትና ጥምቀት ከአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በፊት በ1መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ መመሥረቱን ያረጋግጣል፡፡በሌላም በኩል ከተለያየ የዐለም ክፍል የተሰበሰበ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ በበዐለ ሐምሳ ቀን በዐሉን ለማክበር በኢየሩሳሌም በተገኘ ጊዜ ኢትዮጵውያንም በዚያ በዐል ተገኝተው እንደነበሩና በሐዋርያው ጴጥሮስ ስብከት እንዳመኑ ወደ ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያም ተመልሰው ሃይማኖተ ክርስትናን እንዳስተማሩ ዮሐንስ አፈወርቅ በስብከቱ መግለፁን ጠቅሰውየጻፉጥቂቶችአይደሉም(12) በተመሳሳይሁኔታሩፊኖስ፣ሶቅራጥስ፣ቴኦዶሪቶስና ሶዞሚኖስ የተባሉ የታሪክ ጸሓፊዎች በአንደኛ መቶ ክፍለ ዘመን ድሕረ ልደተ ክርስቶስ ማቴዎስ ሐዋርያ ወደኢትዮጵያ መጥቶ ወንጌለ ክርስቶስን ማስተማሩን እንደገለፁ ጠቅሰው የጻፉ ምሁራን አሉ፡፡(13)በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕጽዋ ለህንኬ ትምህርት፣በቅዱስ ጴጥሮስ የበዐለሐምሳው ስብከት በአመኑ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድሕረ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ሃይማኖተ ክርስትናን አምኖ፣ጥምቀተ ክርስትናን ተጠምቆ ይኖር ነበር፡፡ነገር ግን እስከ አራተኛ መቶክፍለ ዘመንድሕረ ልደተ ክርስቶስ ቍርባን፣ክህነት፣ጠቅላላየምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አፈጻጸም አልነበሩትም፡፡ይህይሟላ ዘንድ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት በአጋጣሚ ሳይሆን በጥበበ እግዚአብሔር የሚከተለው ታሪክ ሊፈጸም ችለዋል፡፡

፪.፪.አቡነ ሰላማ ከሳቴብርሃን(ፍሬምናጦስ)

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድሕረ ልደተ ክርስቶስ ሜሮጵዮስ የተባለ ፈላስፋ ፍልስፈናን የሚያስተምራቸው ሁለት ዘመዶቹ ወጣቶችን አስከትሎ ከጢሮስ ወደህንድ ለመሄድ በቀይ ባሕር(ብሕረ-ኤርትራ) በመርከብ ጉዞ ጅምሮ ነበር፡፡

እነዚህ ሁለት ወጣቶች  1.ኤዶስዮስ 2.ፍሬምናጦስ ይባሉ ነበር፡፡ሁሉም በቀይ ባሕር በመርከብ ሲጓዙ በዚያ ጊዜ የኢትዮጵያ የባሕር ወደብ(የባሕር ጠረፍ) በነበረቺው በአዱሊስ አጠገብ ዐርፈው ነበር፡፡ነገር ግን ሜሮጵዮስ የግድያ አደጋ አጋጥሞት እዚው ሞተ፡፡የሜሮጵዮስን ገዳዮች በተመለከተ የተለያዩ የታሪክ አባባሎች አሉ፡፡አንዳንዶቹ የታሪክ ጸሓፊዎች አትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ቅኚ ግዛትን ትቃወም ስለነበረ በዚህ መርከብ ውስጥ የነበሩ ሜሮጵዮስና የመርከቡ ቀዛፊዎች የሮማ ሰላዮች መስለዋቸው የኢትዮጵያ ጠረፍ ጠባቂዎች እንደ ገደሉዋቸው ይገልጻሉ(14)፡፡ሌሎች የታሪክ ጸሓፊዎች ግን ሜሮጵዮስ የገደሉ ሽፍቶች እንደነበሩይተርካሉ(15)ይሁን እንጂ ሁለቱም የታሪክ ምንጮች ሜሮጵዮስን በቀይባሕር ወደብ በአዱሊስ መገደሉን ያረጋግጣሉ፡፡

ሁለቱን ወጣች ግን ኢትዮጵያውያን ሰዎች ከሞት አዳኑአቸው፡፡ወደ አክሱም ወስደውም ለንጉስ አልአሜ አስረከቡአችው፡፡ ንጉሱም በፍቅር ተቀብሎ ኤዶስዮስን የግቢው አዛዥ፣ፍረምናጦስን የጽሕፈት ክፍል ሐላፊና የልጆች አስተማሪ አድርጎ ሾማቸው፡፡ለንጉሠ አክሱም ኢዛና እና ሳይዛና የተባሉ ሁለትሕጻናት ልጆች ነበሩት፡፡ኤዶስዮስና ፍረሚናጦስ ከነዚህ ሁለት ሕጻናት ጋር ሆነው በአክሱም ቤተ ቀጢን በተባለ ቦታ ላይ በነበረው ትምህርት ቤት ግእዝ ቋንቋንና በዚያ ጊዜ የነበረውን የቤተክርስትያን ትምህርት ሁለት ለሰባት ዐመታት ተምረዋል፡፡ በዚህ መካከል ንጉሡ አልአሜዳ ብዙ ሳይቆይ ታምሞ ከዚህ ዐለም ተለየ(ሞተ)፡፡ንግሥቲቱ አሕየዋ(ሶፊያ) ከአልአሜ ሞት በኃላ በልጆቹ በኢዛናና ሳይዛና ስም መንግሰስቱን ታስተዳድር ጀመር፡፡ ታላቁ የንጉሥ ልጅ ኢዛና ለአካለ መጠን ደርሶ ዙፋኑን በወረሠ ጊዜ ፍሬሚናጦስና ኤዶስዮስ ወደ አገራቸው ለመመለስ የስንብት ጥያቄ አቀረቡ፡፡በጥያቄው መሠረትም እንዲሄዱ ተፈቀደላቸው ኤዶስያስ ወደ አገሩ ሄደ፡፡ ፍሬሚናቶስ ግን በአክሱም ሃይማኖተ ክርስትና፣ጥምቀት እንጂ፡፡ቍርባን፣ካህንነትና ምሥጢራተ ቤተክርስትያንን የሚያከናውኑ(የሚፈጽሙ) ካህናት ወደ አብያተ ክርስትያናት ሄዶ ጳጳስ ማምጣት እንደ ሚያስፈልግ በመገንዘብ ይህን ሐሳቡ ለንግስቲቱና ለአብርሀ፣ለአጽብሓ አቀረበላቸው፡፡ንግሥቲቱም ሆነ ወጣቶቹ ነገስታትም ሐሳቡን ተቀብለው ፍሬሚናጦስ የኢትዮጵያን ቋንቋና ባህል በዚያውም ልክ የውጪውን ቋንቋና ባህል ያውቅ ስለነበረ እሱ ወደ እስክንድሪያ ሄዶ ካህናትን ጳጳስን እንዲያመጣላቸው ላኩት፡፡ፍሬሚናጦስም የነገሥታቱን መልእክት ይዞ በ325 ዐ/ም ወደ እስክንድሪያ ሄደ፡፡የኢትዮጵያ ነገስታት የላኩትንም መልእክት ለእስክንድሪያው ፓትሪያርክ ለቅዱስ እስክንድሮስ አቀረበ፡፡ነገር ግን ቅዱስ እስክንድሮስ በወቅቱ ታምሞ ስለነበረ ብዙ ጊዜ ሳይቆይ በ328 ዐ/ም ዐረፈ፡፡ጉዳዩ ግን በእርሱ ለተተካው ለቅዱስ አትናቴዎስ ቀረቦለት ፍሬሚናጦስ መንፈሳዊ ሕይወትና እውቀት ያለው አባት ስለነበረ

በ330 ዐ/ም በቅዱስ አትናቴዎስ አንብሮት እድ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ፡፡ስሙም ፍሬሚናጦስ የነበረው ስሙም አባ ሰላማ ተብሎ ተሰየመ፡፡(16)

ዝኒ ከማሁ

አቡነስላማማዕርገጵጵስናንተሾሞወደአክሱምበመጣጊዜነገሥታቱኢዛናናሳይዛናበክብርበደስታ ተቀበሉት፡፡ አቡነ ሰላማ ጵጵስናን ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ወንጌለ ክርስቶስን የማስተማር ሥራው ተያያዘው፡፡ በመጀመሪያ ነገሥታቱ ኢዛናንና ሳይዛናን ከበፊቱ በበለጠ አስተምሮ አጥምቆአቸዋል፡፡የክርስትና ስማቸውንም ‹‹ኢዛናን አብርሀ እና ሳይዛናን አጽብሐ›› ብሎ ሰይሞአቸዋል፡፡ቤተክርስትያን በዐራቱ የኢትዮጵያ ማዕዘን እንድትሰፋ፣ወንጌለ ክርስቶስ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደርስ ከፍተኛ ሐዋሪያዊ ትጋት አድርጎአል፡፡የወንጌል የእወቅት ብርሃን በኢትዮጵያ ስለአበራም የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹ከሳቴ ብርሀን›› ቅጻላዊ ስያሜ ሰይሞታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅና ቅዱስ ያሬድ ይህን የአቡነ ሰላማ ሢመተ ጵጵስናን ሐዋሪያዊ ተልእኮን ሲገልጽ፦

‹‹ዓሣተ ሥላሴ ዜነ

ከዕለ ሐዋሪያት ዲቤሁ ተክዕወ፤ “ይክሥት ብርሃነ ተፈነወ አባ ሰላማ ዘድልው ለጵጵስና ሢመተ ክህነቱ ርቱዕ በሕገ ቀኖና”፡፡ በአማርኛ

‹ የሥላሴን ሥልጣን አበሰረ፤

የሐዋሪያት ሀብት በላዩ ላይ ፈሰሰ፤   ብርሃንን ሊገልጽ ተላከ

ለጵጵስና የተገባ አባ ሰላማ    የክህነቱ ሹመት በቀኖና ሕግ የተገባ ነው››፡፡

በማለት በሰማያዊ ዜማው መስክሮአል፡፡ አቡነ ሰላማ ካሳቴ ብርሃን ከዚህ በላይ በተገለፀው ትጋቱና በተመሰከረለት ሢመተ ጵጵስናው ወንጌለ ክርስቶስን አስተምሮ ብዙ ሕዝብን ካጠመቀ በኃላ ጠንካራና በሁለመናው የተደራጀ መንበረ ጵጵስናን በአክሱም አቋቋመ፡፡የክህነት አገልግሎት በስፋት እንዲሰጥ ከዱቁና ክስከ ኤጲሰ ቆጶሶነት ባሉት ማዕርገ ክህነትየሐዱስ ኪዳን ካህናትንሾመ፡፡

ሢመተ ካህናት

አቡነ ሰላማ ካሳቴ ብርሃን ሊቀ ጳጳስ ወንጌለ ክርስቶስን ከማስተማር ሐዋሪያዊ ተግበሩ ጎን ለጎን በአክሱም የብሉይ ኪዳን ደብተራ (ድንኳን) አገልጋዪች የነበሩትን ካሕናተ ኦሪት አስተምሮ ከሃይማኖተ አይሁድ ወደ ሃይማኖተ ክርስትና ከመለሳቸው በኃላ ካሕናተ ሐዲስ ኪዳን አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡በአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን አንጠሮተ እድ እንደተሾሙ በታሪክ የሚታወቁ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን የሐዱስ ኪዳን ካህናት የሚከተሉት ናቸው፡፡

ዲያቆናት ቀሳውስት ኤጲሶቆጶሳት
የብሉይኪዳንስማቸው የሐዲስ ኪዳን ስማቸው
፩  ፊንሐስ ተንሥአ ክርስቶስ ተክለሃይማኖት እንበረም-ሕዝበ ቀድስ
፪  አሮን ስምዖን ገብረመስቀል
፫  አዛርያስ ማቴዎስ
፬  አቤሜሌክ ዘእግዚእ
፭  ላእከሄኖክ አማኑኤል
፮  መልከጼዴቅ አሐዱ አምላክ
፯  ሳዶቅ ማዕቀበ እግዚእ

በሚል ስያሜ የሐዲስ ኪዳን ካህናት አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡እዚህ ከተገለፁት ካህናት መካከል የሁለቱ ቀሳውስት የብሉይ ኪዳን ስማቸው አልተገኘም፡፡በኋላ ሁሉንም ዲያቆናት ቀሳውስት አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡በቅዳሴ በሥርዐተ ቁርባን እና ሕዝቡን በማስተማር እንዲረዱት አድርጎአቸዋል፡፡ብፁዕ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በመንፈስ ቅዱስ አየተመራ ይህን ሐዋርያዊ ተልእኮውን በተሳካ መልኩ በማከናወን ተጋድሎውን ከፈጸመ በኋላ በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሐምሌ ፳፮ ቀን  ዓረፈ፡፡ይህ ሐዋርያዊ ሰንሰለት ተያይዞ አሁን እስከ አሉ ቅዱሳን ፓትርያሪኮች፣ሊቃነ ጳጳሳት ኤጲስ ቆጶሳት ቀሳውስትና ዲያቆናትደርሶአል፡፡ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢጥዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዚህ ሐዋርያዊ ታሪክ አካል ናቸው፡፡

Read more

የጥምቀት በዓል አከባበር  በአኃት አብየተ ክርስቲያናት፤ በምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያንና በምዕራቡ ዓለም 

በመልአከ መዊዕ ሳሙኤል እሸቱ

የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ

የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ተብለው የሚጠሩት በዋናነት ኮንስታንቲኖፕል የሚገኘውን ኢኮሚኒካል ፓትርያርክ ርእሰ መንበርነት  ተቀብለውና የራሳቸው የማይናወጥ አስተዳደርና ፓትርያርክ ኖሯቸው እምነታቸውን የሚመሩ የግሪክ ፤ሩሲያ፤ ቡልጋሪያ፤ ዩክሬን፤ ጆርጂያ፤ ቼክ፤ ቆጵሮስ፤ ቦስንያና ወዘተ … የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በምሥራቁ ኦርቶዶክስ ክፍለ ዓለም  ከልደት እስከ ጥምቀት ያለው ወቅት ኤጲፋኒያ ተብሎ ይጠራል፡፡የጥምቀት ጊዜ ደግሞ ቴዎፋኒ ይባላል፡፡ ኤጲፋኒያ አጠቃላይ የክርስቶስን በሥጋ መገለጥ ለመግለጽ የሚጠቀምበት ሲሆን ቴዎፋኒ ጥምቀቱንና በዚያም የተገለጠውን ምስጢር ለመግለጥ ሚጠቀሙበት ቃላት ነው፡፡ትርጓሜውም መገለጥ ፤ማሳየት አልፎ ተርፎም  ማሳወቅ ማለት ነው፡፡ይኸውም መድኅን ክርስቶስ ሥጋ በመልበስ ሰውን ለማዳን የተገለጠበትን ለማመልከት ነው፡፡በምሥራቅ ኦርቶዶክስ ያለው የጥምቀት አከባበበር አብዛኛው ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም መንፈሳዊ ይዘቱንና ባህላዊ ክንውኑን በመጠኑ በዚህ ጽሑፍ እንዳስሳለን፡፡

በምሥራቁ በዓለ ጥምቀት (ኤጲፋንያ ፤የቴዎፋኒ) የገናን በዓል ተከትሎ የሚከበር ሲሆን እሱም ታኅሣሥ 29 ቀን ተጀምሮ ጥር 11 ቀን ያበቃል። በዘመነ ቴዎፋኒያ ታላቁ የውኃ በረከት በዚህ ቀን ይፈጸማል፣ የተባረከውን ቅዱስ ውሃ  ምዕመናን ይጠመቁበታል ።የአጥቢያው ካህንም የምእመናንን ቤቶች እየዞረ በቅዱሱ ውኃ ይባረካል፡፡

  • በግሪክኦርቶዶክስ 

በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩ በዓላት መካከል ቴዎፋኒ (ኤጲፋኒያ) አንዱና ዋነኛው ሲሆን በዓሉ በበርካታ ክርስቲያናዊ ባህል በልጽጎ የሚከበር ነው ፡፡ ጌታ መጠምቁን  ተድላን እንፈጽም ዘንድ ግድ ነው  ብሎ  በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ  ወንዝ መጠመቁን የሚዘክር በመሆኑ የደስታና የሓሴት ቀን ተብሎ በግሪክ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ይከበራል፡፡በበዐሉ ከሚታየው ትርዒት መካከል  ካህኑ  ከቅዱስ መስቀል ጋር የውሃውን በረከት ይዞ በሕዝቡ ፊት በመቅረብ ለበዓሉ የሚገባውን ጸሎት

‹‹በዮርዳኖስ ወንዝ ውኃ ውስጥ፣ በዚህ ቀን የሁሉ ጌታ ዮሐንስን፡- አትፍራ እኔንም ከማጥመቅ ወደኋላ አትበል፤ እኔ አስቀድሞ የተፈጠረውን አዳምን ለማዳን መጥቻለሁና ብሎ ጮኸ››።

የሚለውን አሰምቶ በተከተረው ውሃ ወይም በወንዙ አልያም በሀይቅ  ቅዱስ መስቀሉን በወረወረ ጊዜ ዋናተኞች እየዘለሉ ወደ ውሃው ውስጥ በመግባት መስቀሉን ለማግኘት የሚያሳዩት ሥርዓትም በእጅጉ ማራኪ ነው። በዚህ ትዕይንት ውስጥ መስቀሉን ቀድሞ ይዞ ወደ ካህኑ የሚያመጣው ሰው  ዓመቱን ሙሉ ይባረካል ተብሎ ስለሚታሰብ በከፍተኛ ፉክክር የታጀበ ትዕይንት ይከናወናል።

በሀገራቸው የጥምቀት በዓል ልክ እንደ ገና  የራሱ ልዩ የምስጋና  መዝሙር አለው ከሚጠቀሱት መካከል

  ‹‹ዛብሎን ሆይ፥ ተዘጋጅ :ንፍታሌም ሆይ፥ ተዘጋጅ ! የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ጉዞህን ቀጥል እና አሁን ለመጠመቅ የሚመጣውን ሉዓላዊ ጌታን ለመቀበል በደስታ ዝለል። አዳም ሆይ ደስ ይበልህ እናታችን ሔዋን ደስ ይበልሽ፡፡በገነት ውስጥ እንደ ቀድሞው አትደብቁ።ራቁትህን አይቶ የፊተኛውን ልብስ ሊያለብስህ  ክርስቶስ  አሁን ተገለጠ። ፍጥረትን ሁሉ ለማደስ በእውነት ይፈልጋልና››

በባህላዊ ረገድ ልጆች ስለ በዓሉ እየዘመሩ ገንዘብ እና ጣፋጮች ምግቦችን ያገኛሉ፡፡ልጆች ከሚዘምሩት የጥምቀት ዜማዎች ውስጥ ቅዱስ ዮሐንስ ራዕዩን ባየበት  በደሴተ ፍጥሞ ላይ የተዘመሩ መዝሙሮች  የበዐሉን መልእክት የሚይዝ ነው፡፡ይህም  ዝማሬ የሚጀምረው ስለ ፍጥረተ ዓለም ስለ ውሃ አፈጣጠርና የእግዚአብር መንፈስ በውሃ ላይ ስለመስፈፉ እና በመጨረሻም ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ቀን ስለነበረው ክብር ይገልጻል፡፡ ማዕከላዊው ግሪክ  የበዓሉ ዋነኛ መስህብ የሚንጸባረቅበት ቦታ ሲሆን ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ ሰዎች ልብስ ለብሰው ከቤት ወደ ቤት እየዞሩ ዜማውን እየዘመሩ ገንዘብ ይሸለማሉ።እያንዳንዱ ቡድንም በአለባበሱ ወቅት ሊያካትታቸው የሚገቡት  አልባሳት የሙሽራና ሙሽሪት ፤የቄስ ፣ የአያት ፣ የዶክተር እና በግሪክ ገጠራማ አካባቢዎች ያሉ ሰዎችን  አለባበስ መልበስ ግዴታቸው ነው፡፡ሌላው በጥምቀት የሚከናወነውን ጥንታዊ ሥርዓት ሰዎች ርኩሳን መናፍስትን ከከተማው ለማስወጣት በሚል አስፈሪ ጭምብሎችን ለብሰው ትርኢት በመሥራት ጭንብል የለበሱት ሰዎች ርኩሳን መናፍስትን የሚወክሉትን በማባረር የሚያሳዩት ትርኢት የበዓለ ጥምቀት አንዱ ገጽታ ነው

  • በሩስያኦርቶዶክስ

በሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀት ልክ እንደ ግሪክ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ  በዓላት አንዱ ሲሆን መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስን  በዮርዳኖስ ወንዝ ያጠመቀበት ቀን በማሰብ የሚከበር በዓል ነው፡፡የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም በጥምቀት ምሥጢረ ሥላሴ መተርጎሙን በዝማሬ እንዲህ እያለች በበዓሉ ታመሰግናለች

  ‹‹አቤቱ በዮርዳኖስ በተጠመክ ጊዜ የሥላሴ ሕልውና  ተገለጠ። አብ በድምጹ የተወደደ ልጄ ብሎ ሲጠራህ ልጅነትህን  መስክሮልሃልና። መንፈስም በርግብ አምሳል የቃሉን እውነት አረጋገጠ። የበሥጋ የተገለጥክ ዓለምን ያበራህ አምላካችን ክርስቶስ ሆይ ክብር ላንተ ይሁን››።

በሩሲያ በዓሉ በቤተ ክርስቲያንና በአደባባይ የማክበር ልማድ ያላቸው ሲሆን በመስቀል ቅርጽ በረዷማ ወንዞችን በመከተር በዓሉ ሲከበርም በቀዝቃዛው በወንዙ ውስጥ  ዘልቆ በመዘፈቅ በቀዘቀዘ በረዶ ውስጥ የመጠመቅ ወይም የመዋኘት ሥርዓት ይደረጋል፡፡

  • በቡልጋርያኦርቶዶክስ 

በቡልጋርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም  የበዓሉ አከባበር  በጣም የተለየ ክስተት አለው፡፡ በዋዜማው ቅዳሴ ተደርጎ ውሃን የመባረክ ሥርዓት ይደረጋል ሕዝቡና ካህናቱ እግዚአብሔር የምድሪቱን ውሃ እንዲባርክ ይጸልያሉ ፡፡በእምነታቸው የምድር ሁሉ ውሃ መባረኪያ ቀን የጥምቀት ቀን እንደሆነ ያምናሉ ፡፡

በጥምቀት ዕለት ያለው ባህላዊ ክዋኔ ዘማሪዎች(የባህል ዘፈን አቀንቃኞች) በቀዝቃዛ በረዶ ውሀ ውስጥ በመግባት ባህላዊውን ዘፈን እየዘፈኑ ቄሱ ለበዓሉ የሚስማማውን ጸሎት አድርጎ የሚወረውረውን መስቀል ለመያዝ ይጠባበቃሉ፡፡ በሌሎቹ ምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንደተመለከትነው  መስቀሉን ቀድሞ ያገኘ ወንዙ ውስጥ ባሉት ሰዎች  ተከቦ እየዘመሩ በዓሉን ያከብራሉ ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ምእምናን ቤታቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሁለንተናቸውን  ለመባረክ የተባረከውን ውሃ ወደ ቤታቸው በመውሰድ ዓመቱን ሙሉ በጠበልነት ይጠቀሙበታል ፡፡

  • በዩክሬንኦርቶዶክስ

በዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት  በዓል ብዙ ልማዶች እና ወጎች አሉት፡፡ ልክ እንደ ሌሎቹ የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን በባህር ዳርቻ የሚደረገው ሥርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ ጊዜ ጾምን የሚጨርሱበት ወቅት በመሆኑ  ለጥምቀት ልዩ ልዩ ምግቦችን በማዘጋጀት የመጀመሪያው ኮከብ በሰማይ ላይ ከታየ በኋላ እራት ይመገባሉ፡፡ በእርግጥ ዋናው በዓል  ውሃን መቀደስ የሚለው በመሆኑ ካህኑ መስቀልን  “ዮርዳኖስ” ተብሎ ወደ  ሚጠራው ልዩ ሆኖ  በተሠራው የበረዶ ጉድጓድ ውስጥ አድርጎ ጸሎቱን ያቀርባል ሲጨርስ ውሃው ኢየሱስ እንደተጠመቀበት  እንደ ዮርዳኖስ ወንዝ ቅዱስ ስለሆነ በሽታ ሊፈውስ በሚችል ልዩ ባሕሪያትና ኃይል እንዳለው ሲያውጅ አማኞች በዚህ ውኃ ለመዘፈቅ ተሸቀዳድመው ይገባሉ  ፡፡በዚህ ውሃ በመጠመቅ ከሥጋ ደዌና ከአእምሮ በሽታ እንደሚፈወሱ ያምናሉ ፡፡ከቅዱስ ውሃ በመውሰድም  ቤታቸውንና ግቢያቸውን በመርጨት ክፉ መናፍስትን ያርቁበታል፡፡

  • በኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን

የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት በዓልን ቀደም ባሉ ጊዚያት ከባህላዊው ኪያክ  ወር ጋር ተገጣጥሞ ቀደም ባሉት ጊዚያት ወደ ዓባይ ወንዝ በመውረድ የሚከበር የነበረ ሲሆን  በአሁኑ ወቅት ግን በዓሉን በአደባባይ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን  በቅዳሴ ሥርዓት ታጅቦ ይከበራል ፡፡

  • በምዕራቡዓለም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት

በምዕራቡ ዓለም ያለውን የጥምቀት አከባበር ስንቃኝ  በሁለት ዝግጅቶች ላይ በዋናነት ያጠነጠነ ነው፡፡  እርሱም የጥበብ ሰዎች ለሕጻኑ ኢየሱስና ለእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም የሰጡት ስጦታና በቃና ገሊላ ስለተደረገው ሠርግና ተአምራት በማዘከር ነው፡፡ ሰብአ ሰገል  ሕፃኑንና እናቱን ማርያምን በኮከብ ተመርተው በማግኘት ስጦታ ወይም አምኃ እንዳቀረቡ ሁሉ አማኞቹ  ከልጆች ጋር የስጦታ ዝግጅትን በማድረግና ስጦታን በመስጠት ያከብራሉ፡፡

ማጠቃለያ 

የጥምቀት በዓልን አከባበር ከላይ በሁሉም ሀገርና አብያተ ክርስቲያናት እንደቃኘነው አብዛኛዎች በጥቂት ቁጥርና በተወሰነ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በዓሉን ያከብራሉ፡፡ የአከባበር ሁኔታውም ቢሆን በከተማና በገጠር በተለያየ ሁኔታ ያከናውኑታል፡፡ ዘመናዊነት እንደፈጣን አውሎ ንፋስ ምድራችንን እያጥለቀለቀ ባለበት በዚህ ጊዜ መሠል በዓላትን በጥቂቱም ቢሆን እያከበሩ የሚገኙት ኦርቶዶክሳውያኑ አብያተ ክርስቲያናት መሆናቸውን ስናይ የወንጌል እውነት እንዳይበረዝ ባህልና ወግ እንዳይጠፋ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ባለውለታ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ከሁሉም ግን የሚያስደንቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  ለሁለት ሺህ ዓመት ይህን እውነት ጠብቃ በዓላትን በአደባባይ እንዲከበር ማድረጓ በእምነት የጸናች በነጻነቷ የተከበረች ባህልና ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ተባለች ሀገር በአፍሪካ ምድር እንደ እንቁዕ እንድታበራ አድርጋለች ለዚህም ነው ኦርቶዶክስ ሀገር ናት ያስባለው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር