**********
የካቲት ፱ቀን ፳ ፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
በብፁዕ ከቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና በባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚመራው የጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባዔ በወቅታዊ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ የካቲት ፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ልዩልዩ ውሳኔዎችን አስተላለፈ።
ጉባኤው በቤተክርስቲያናችን የተደረሰውን ስምምነት አስመልከቶ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የተሰጠውን ሰፊና ጥልቅ ማብራሪያ ካዳመጠ በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።
፩ኛ በትላንትናው ዕለት በቅዱስ ሲኖዶስና ተወግዘው በተለዩት አባቶች መካከል የተደረሰውን ስምምነት በማድነቅ ተቀብሎታል። ለአፈጻጸሙም የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማበረሰከት ቃል ገብቷል።
፪ኛ እርቀ ሰላሙ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ወክለው ለተወያዩ ብፁዓን አባቶች፣ ተወግዘው ተለይተው ለነበሩ አባቶች ከሁሉም በላይ ለቤተክርስቲያን አንድነት ቅድሚያ በመስጠት ለፈጸሙት ታሪካዊ ስምምነት አድናቆቱንና ምስጋናውን አቅርቧል።
፫ኛ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ቅዱስ ፓትርያርኩ ፣ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሉአላዊ ክብርና ቀኖናዊ ሥርዓቱን ለማስጠበቅ የከፈሉትን መስዋዕትነት በማድነቅ ስምምነቱ የቤተክርስቲያናችንን መብት ባስከበረ መልኩኩ እንዲፈጸም በማድረጋቸው የተሰማውን ልባዊ ደስታ ከመግለጽ ጋር ስምምነቱን ተከትሎ ለሚከናወነው ተቋማዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሁሉ በፍጺም ትጋት ለመፈጸም ዝግጁነቱን ገልጿል።።
፬ኛ ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሀገር ናት በማለት የሚገልጹትን ሀቅ በማጠናከር እርቀ ሰላሙን ተከትሎ “ሙሽራው ክርስቶስ እስከሚመጣበት ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አንድነቷ ተጠብቆ ይኖራል።” በማለት እርቀ ሰላሙ ከልብ እንዲከናወን ያደረጉትን ጥረት በማድነቅ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል።
፭ኛ የቤተክርስቲያን ቀኖና አይጣስም አንድነቷ አይናጋም በማለት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ለማስከበር ክቡር መስዋዕትነት ለከፈላችሁ የዘመኑ ሰማዕታት፣ለዕስርና ለእንግልት የተዳረጋችሁ ኦርቶዶክሳዊያን፣ለግርፋትና ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ልጆቻችን ሁሉ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ያለው ጉባኤው ለሰማዕታት መንግስተ ሰማያትን እንዲያወርስልን፣የአካልና የሥነ አእምሮ ጉዳት ለደረሰባቸው ምሕረትን ለልዑል እግዚአብሔር ይስጥልን ወዳጅ ዘዶቻቸውንም ያጽናናልን፣የታሰሩትንም ያስታልን በማለት የታሰሩ የቤተክርስቲያን ልጆችን ለማስፈታት በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማበርከት ቃል ገብቷል።
፮ኛ በዚህ ፈታኝ ወቅት የቤተክርስቲያንን ሉዓላዊነትና ቀኖናዊ አንዴነትን ለማስከበር በተደረገው ተጋድሎ ከቅድስት ቤተክርስቲያን ጎን በጽናት የቆማችሁ በየደረጃው የምትገኙ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና የጽሕፈት ቤት ሰራተኞች፣የቤተክርስቲያን አገልጋዮች፣ ማኅበራት፣ወጣት ልጆቻችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙሃን ድርጅት፣የቤተክርስቲያናችን የሕዝብ ግንኙት መምሪያ፣የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት በሚዲያው ዘርፍ ለተሰማሩሩ ልዩልዩ የሚዲያ ተቋማት አክቲቪስቶችና ጸሐፊያን ሁሉ ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች።
፯ኛ የቤተክርስቲያናችን ጉዳት ጉዳታችን ነው ከቤተክርስቲያናችን ጎን በጽናት እንቆማለን ፤ችግሩን የቤተክርስቲያንን መብትና ጥቅም በሚያስከብር መልኩ በሰላማዊ መንገድ እንፈታዋለን በማለት ሊገለጽ የማይችል ተጋድሎና እልህ አስጨራሽ ፈተናዎችን በጽናት አልፋችሁ ይህን ዕርቀ ሰላም እውን ያደረጋችሁ የመፍትሔ አፈላላጊና የሽምግልና ሥራ የሰራችሁ ባለሀብቶችና አትሌቶች ልፋታችሁ እንኳን ፍሬ አፍርቶ ለማየት በቃችሁ እንኳንም ደስ አላችሁ። በማለት ልባዊ ምስጋናችን እናቀርብላችኋለን።
፰ኛ በዚህ ፈተና ጊዜ ቤተክርስቲያንን አናስደፍርም፣ የቤተክርስቲያንን ጥሪ ተቀብለን ቤተክርስቲያንን እናስከብራለን በማለት ውድ ሕይወታቸውን በመስዋዕትነት ላቀረቡ ሰማዕታት ቤተሰቦች፣የአካልና የሥነ አእምሮ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን ለመደገፍና የቤተክርስቲያን ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ዓለም አቀፍ የርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ በአስቸኳይ እንዲቋቋም ወስኗል።
፱ኛ የሚቋቋመው ዓለም አቀፍ የርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ በተቋም ደረጃ በማዕከላዊ የቤተክርስቲያናችን አስተዳደር የሚቋቋም ብቻ እንዲሆን ይደረጋል።ከዚህ ውጪ በማኅበር፣በግልና በቡድን የሚቋቋም የርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ታውቆ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ የቤተክርስቲያያችን ማዕከላዊ አስተዳደር
በሚያሳውቀው ሕጋዊ አካል ብቻ ድጋፍ እንዲያደርጉና መላው ኦርቶዶክሳዊያን ይህን የተቀደሰ ዓላማ ለማሳካት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ እያቀረብን ለዚሁ ዓላማ የሚውል የባንክ ሒሳብ በአገር ውስጥና በውጪ ሀገራት የሚከፈት ይሆናል።
፲ኛ በቤተክርስቲያናችን ታሪክም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህን የመሰለ ፈተና ገጥሞ በማያውቅበት ጊዜ ከቤተክርስቲያናችን ጎን በመቆም ለቀኖናና ለአንድነታችን መከበር በጽናት የቆማችሁ የእስልምናና የኘሮቴስታንት ዕምነት ተከታይ ወንድሞቻችን ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሀገር መሆኗን በተግባር በሚያረጋግጥ ተጋድሎ በሀቅ ከጎናችን ስለቆማችሁ ልባዊ ምስጋናችንን በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ስም እናቀርብላችኋለን።
፲ ፩ኛ በዚህ ፈታኝ ወቅት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የስብከተ ወንጌል ስምሪት ተደርጎ ተጎጂዎችን የመጽናናት ፣የማስተማርና የመጎብኘት ሥራ በአስቸኳይ እንዲካሔድ ለዚሀህም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እንዲከናወን ወስኗል።
፲፪ኛ በዚህ የቤተክርስቲያንን መብትናጥቅም በማስከበር ሒደት ውስጥ የመንግስትን ሥልጣን መከታ በማድረግ በህገ ወጥ መንገድ ግድያ የፈጸሙ፣የአካል ጉዳት ያደረሱ፣ድብደባና ወከባ የፈጸሙ አካላትን ለህግ ተጠያቂነት ማቅረብ ለነገ የማይባል ተግባር በመሆኑ እነዚህን አካላት ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ምዕመናንና ምዕመናት እንዲሁም ወጣት የቤተክርስቲያያችን ልጆቻችን አስፈላጊውን ድጋፍ እንድተታደርጉ ጥሪአችንን እያቀረብን የቤተክርስቲያናችን የሕግ አገልግሎት መምሪያና ጠበቆቻችን ይህን ጉዳይ በልዩ ትኩረት በመከታተል የህግ ተጠያቂነትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የአስተዳደር ጉባኤው የወሰነ ሲሆን ውሳኔውም ለቋሚ ሲኖዶስ በመሸኛ እንዲላክ ብሏል።
፲፫ኛ የተጀመረው የሰላም ሂደት ፍሬ አፍርቶ ተጨባጭ ውጤት እስከሚገኝና ሁሉም ነገር ወደ ቦታው እስከሚመለስ ድረስ ኦርቶዶክሳዊያን ልቻችን ሁሉ አስከ ሁን ድረስ ስተታደርጉት እንደቆያችሁት ሁሉ ቤተክርስቲያናችሁን በጽናት እንድትጠብቁ ጉባኤው አደራ ብሏል።
በመጨረሻም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጃችን በዚህ ክፉ ወቅት በፍፁም ትጋት፣ብቃትን በተተተግባር ባመላከተው የአመራር ችሎታቸው በጥብአት የፈጸሙት ተጋድሎን ከልብ የምናደንቅ ሲሆን ለቀጣይ ሥራቸው መሳካት ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጃችን ጎን በመቆም ሌት ተቀን ለመስራት ፍጹም ዝግጁ መሆናችንን ስናረጋግጥ በፍጹም ደስታና ትህትና መሆኑን እንገልጻለን በማለት የዕለቱን ስብሰባ በጸሎት አጠናቋል።