ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዶ/ር የሐይማኖት አባቶች ሠላም እንዲሰብኩ አሳሰቡ!

የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የመቱ ፈለገ ሕይወት መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

”  በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። መዝ.65:11 የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ቃል መሠረት አድርገው መልእክታቸውን አስተላለልፈዋል።

ፈጣሪ ዘመናትን አሳልፎ አዲሱን ዘመን የሚያሳየን በመልካምነታችን ሳይሆን በምህረቱ ብዛት ነው ያሉት ብፁዕነታቸው፤ሁሌም  ዓዲስ ዘመን የሚሰጠን ለሥራና ለለውጥ ነው ብለዋል።አዲሱን ዓመት ስንቀበል በሳለፍነው አሮጌ ዓመት ምን የጎደለን ነገር አለ?ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅና ምናልባታም ባጠፋነው ጥፋት ተጸጽተን ንሰሀ ገብተን እንመለስ ዘንድ አዲሱ ዘመን በቸርነቱ ተሰጥቶናል ብለዋል።

በሀገሪቷ ውስጥ በሁሉም ስፍራ ሠላም መጥፋቱ ዋና አጀንዳ ሆኗል ያሉት ብፁዕነታቸው ፤ በእኛ መሀል ሠላም የለም ፣ሁሌም መጣላት የሰርክ ተግባራችን ሆኗል፤ በየስፍራው የሚሰማው ዜና አሳዛኝ እየሆነ መጥቷል፣ጦርነት ሀገሪቷን ወደ ኋላ እየመለሳት ነው፣ ይህ ሁሉ የበደላችን ውጤት ነውና በአዲሱ ዓመት ወደ ልባችን ተመልሰን ልንለውጥ ይገባናል ብለው የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች  ሠላምን አብዝተው በመስበክ በሕዝብ መሀል ስምምነትና መተማመን  እንዲኖር መስራት አለባቸው  ብለዋል።

የሰው ልጅ በችሮታ የተሰጠውን ጊዜ ተጠቅሞ ካልተለወጠ የተለወጠ  ዘመን ማክበሩ ጥቅም የለውም ብለዋል። ብፁዕነታቸው አያይዘው  በርካትቶቻችን በአዲሱ ዘመን አስበን ልብሳችንን እንቀይራለን እንጂ ልባችንን አንቀይርም ብለው በውስጣችን ያለው  የድንጋይ ልብ አውጥተን የሥጋ ልብ የምህረትና የፍቅር ልብ ሊኖረን ይገባል በለዋል።

በአዲሱ ዘመን ጋራና ሸንተረሩ አበባን ለብሰው ደምቀውና አምረው ተቀይረው ይታያሉ ያሉት ብፁዕነታቸው የሰው ልጅ ግን አይቀየርም  ከምድር አበባ አንሰናልናል በእውነት ወደ ፈጣሪያችን መመለስ አለብን ብለው  ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ እንደሚጠፋ እንስሳ  እየሆነ መምጣቱ አሳሳቢ ነውና በተጨመረልን ዓዲሱ ዘመን ልንመለስ ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች፣በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ለሀገረ ስብከታችን ሕዝብ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወንጌላዊ ወደ ዘመነ ማቴዎስ ወንጌላዊ በሠላምና በጤና  አሸጋገረን አሸ፡ሀጋገራችሁ ብለዋል!

ጳጉሜ 5/2016 ዓ. ም
የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሚዲያ

ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዘመን መለወጫን በዓል አስመልክተው አባታዊ ቃለ በረከት አስተላለፉ።

መስከረም ፩ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የፌስቡክ ገጽ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፤ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም።”
“በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።” መዝ ፷፬÷፲፩

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ከሁሉ አስቀድሜ ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን ያለፈውን ዓመት በሰላምና በጤና በሕይወት ጠብቆ አሁን ላለንበት ጊዜና ሰዓት ያደረሰን ፈጣሪ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።

ውድ የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት የሆነችው የበረሃዋ ንግስት የድሬዳዋ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጪው ዓለም የምትገኙ ውድ ኦርቶዶክሳውያን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችንና መላው የሀገራችን ሕዝቦች በሙሉ።

እንኳን ለ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን የሰላም አምላክ የፍቅር ጌታ የደስታ ሁሉ ባለቤት መጪውን ጊዜ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ ጌታ እግዚአብሔር ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለቤተክርስቲያናችን ሰላምና ፍቅር ሰጥቶን በጋራ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን የምናለማበትና የምናሳድግበት የተጣላን የምንታረቅበት ከድኅነት ከችግር ነፃ የምንወጣበት የበረከትና የይቅርታ ዓመት ያድርግልን። ውድ ኦርቶዶክሳውያን መላው የሀገራችን ሕዝብ ሆይ እግዚአብሔር አምላክ በደላችንን ይቅር እንዲለን ከክፋት፣ከተንኮል፣ከሀሜት፣ከዘረኝነት ጸድተን በንጽህናና በቅድስና ሆነን ዘወትር ሁሉን ማድረግ ወደሚችለው አምላክ እንጸልይ ጌታ እግዚአብሔር ተአምራትን ያደርጋል ዓመቱን የሰላም፣የፍቅር፣የይቅርታ፣የአንድነት ያድርግልን አሜን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ !

አባ በርተሎሜዎስ
የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
መስከረም ፩ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
ድሬዳዋ ኢትዮጵያ

እግዚአብሔር አምላክ አገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፧ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳሞ፤ በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።”መዝ. ፷፬÷፲፩

ቸርነትና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነለት አምላካችን አግዚአበሔር ወሰን በሌለው አባታዊ ፍቅሩና መግቦቱ ሳይለየን ጠብቆና አቆይቶ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ ከ፳፻፲፮ ዓ.ም ወደ ፳፻፲፯ ዓ.ም በሰላምና በጤና አሸጋገረን
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የአንድነት፣ የሥራ፣ የመግባባትና የፍቅር ዓመት ይሁንልን።

እግዚአብሔር አምላክ አገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን።
አባ ዲዮስቆሮስ
የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከ፣የቤተ መጻሕፍት ወመዘክርና የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰጠውን መግለጫ መነነሻ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ልዩልዩ ውሳኔዎችን አስተላለፈ

ጷጉሜ ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም

ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት።

ጳጉሜን 4/2016 ዓ/ም
===============
እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ በሰላምና በጤና አሻገረን አሻገራችሁ። “ወይቤሎ ኅድጋ እግዚኦ ሐሪፈኒ’ “በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት” ሉቃ 13፥8

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ባስተማረው በዚህ ትምህርት ውስጥ የአትክልቱ ባለቤት፡ በወይኑ አትክልት ቦታ የተተከለች በለስና የአትክልቱ ሠራተኛ ይገኛሉ። የበለሷ ባለቤት በለስ መትከሉና የሚንከባከብ ሠራተኛ የመቅጠሩ መሠረታዊ ዓላማ ከበለሷ ፍሬ ለማግኘት ነው። ነገር ግን የአትክልቱ ባለቤት በለሷ ፍሬ መስጠት በሚገባት ወቅት ጠብቆ ቢመጣም ፍሬ ማግኘት አልቻለም። የአትክልት ሠራተኛውን እነሆ ከዚች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም ቁረጣት፣ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች? አለው። ጠባቂዋም ‘ጌታ ሆይ ፍሬ እንድታፈራ አስፈላጊውን እስካደርግላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት በማለት ልመናን አቀረበ።

የበለሷ ባለቤት በለስ ተክሎ ፍሬ እንደፈለገ ሁሉ እኛንም ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር ሲፈጥረን ፍሬ እንድናፈራ እንጂ ፍሬ አልባ በለሶች እንድንሆን አይደለም። ፍሬ ማፍራት ካልቻልን ደግሞ እጣ ፋንታችን መቆረጥ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የንስሓ፣ የፍቅር፡ የይቅርታ የበጎ ምግባር ፍሬ እንድናፈራ ይፈልጋል። የአትክልቱ ሠራተኞች በዚች ዓመት ተዋት ብለው እንደለመኑ ዛሬም እኛ ከዓመት ወደ ዓመት መሻገራችን በጎ ፍሬ ስለ ተገኘብን ሳይሆን ፍሬ እንድናፈራ አቤቱ የዘንድሮን ተዋት በማለት በሚማልዱልን በቅዱሳን መላእክት ምክንያት መሆኑን ማስተዋል ይገባናል። ፍሬ ሳታፈራ ለምን ምድርን ታጎሳቁላለች እንደ ተባለችው በለስ እኛም እንንከባከባት ዘንድ የተሰጠችንን ምድር በክፋት፡ በጥላቻ፡ ፍቅርን ትተን ጠብን በመዝራት እርስ በርእስ በመጠፋፋት ለሰው ልጆች የመከራና የሰቆቃ ስፍራ አድርገናታል፡፡ ክቡር የሰው ልጅ ደም በራሱ በሰው ልጅ ጭካኔ በከንቱ እየፈሰሰ ይገኛል፡፡ ፍሬ ባያገኝብንም እግዚአብሔር ቸር በመሆኑ በቅዱሳን ጸሎት ከዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ እንድንሻገር ፈቀደልን። በመሆኑም ይህ ዘመን የተጨመረልን ለንስሐ የሚገባ ፍሬን እናፈራ ዘንድ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ከዘመን ወደ ዘመን መሻገር በሰዎች ጥበብ የማይገኝ ከእግዚአብሔር ብቻ የሚሆን ትልቅ ስጦታ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ በጊዜ ላይ ጊዜ በእድሜ ላይ እድሜ የጨመረልን ካለፈው ዘመን ተምረን የሚቀጥለውን በማረም ፍሬአማ ሕይወትን መኖር እንድንችል ነው፡፡ በአዲሱ ዘመን ሰላምና ፍቅርን በሀገራችን ለማጽናት የበኩላችንን ማበርከት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ በ2017 ዓመተ ምሕረት በዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ ጥላቻን አርቀን ፍቅርን፣ ክፋትን ትተን ደግነትን፡ መገፋፋትን አስወግደን መረዳዳትን፡ ከኃጢአት ርቀን ጽድቅን የምንሠራበት፣ ጦርነት ከሀገራችን ተወግዶ በሰላም ወጥተን በሰላም የምንገባበት፡ መለያየታችን ወደ አንድነት የሚመጣበት ዘመን እንዲሆን በጸሎት ትተጉ ዘንድ አደራ ጭምር አሳስባችኋለሁ፡፡

የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስን የሰላምና የበረከት ያድርግልን፡፡ አሜን

መልእክተ ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስ ሀገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!!
አባ ዮሴፍ
የሲዳማ ሀገረ ስብከት እና የሀዋሳ ታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል።

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት እንዲሁም በመላው ዓለም የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምዕመናን ወምዕመናት እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አደረሳችሁ አሸጋገራችሁ

“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም –  በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል” መዝ ፡ ፷፬ ( ፷፭ ) ፥ ፲፩

ከላይ የተገለጸው ኃይለ ቃል የአምላካችንን ድንቅ መጋቢነት የሚገልጽ ሲሆን፤ እግዚአብሔር አምላካችን ዓመታትን በቸርነቱ እየለወጠ፤ የበረከት እጁን ሳያጥፍ እየመገበ፤ የሰዎችን ማንነት ሳይለይ ለክፉም ለደጉም፤ ለኃጥኡም ለጻድቁም፣ ለድሀውም ለሀብታሙም፣ ለአሕዛብም ለሕዝብም የምሕረት ዝናቡን እያወረደ ፍጥረትን በሙሉ የሚያረካ አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን ያስረዳናል። እንዲሁም ሥነ-ፍጥረትን ብንመረምር የበጋና የክረምት መፈራረቅ፤ ተራሮች በዝናብ መርካታቸው፤ ከድርቀት (ከፀሐይ) ወራት በኋላ የሚመጡት የበረከት (የዝናብ) ጊዜያት እንዴት ባለ በሚያስደንቅ ሁኔታ የምድሪቱን ገጽታ እንደሚቀይር እንገነዘባለን።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን

አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን ሲተካ በምን ዓይነት መንፈስ ነው የምንቀበለው ለሚለው ጥያቄ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽ ይሰጠናል። «የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፤ በመዳራት እና በሥጋ ምኞት፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለልክም በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት፣ በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና» በማለት ያስተምረናል። (1ጴጥ.፬፥፫) ዘመናትን በቸርነቱ የሚያሳልፈው እግዚአብሔር ነው፡፡ በተሰጠን የአንድ ቀን ዕድሜ ኖሬበታለሁ? ብለን ራሳችንን ልንመረምር ይገባል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በኃጢአት የኖርበትን ዘመን በሕይወት እንዳልኖርበት ነግሮናል፡፡ ለምን ቢባል በደሙ የከበርን ክርስቲያኖች አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስለን ባለመገኘታችን ነው፡፡

በክርስቶስ ክርስቲያን ተሰኝተን በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን የማይጠፋውን ልጅነት ካገኘን በኋላ መጠመቃችንን የክርስትና መጨረሻ አድርገን በመውሰድ በስም ብቻ ክርስቲያኖች በመባል በክፋት ጸንተን እንገኛለን፡፡ ሥራ የሌለው እምነት ፣ፍሬ የሌላት በለስ ሆነን ከመገኘት ክርስትናን ኖረንበት ልናልፍ ይገባል፡፡

እግዚአብሔር በቸርነቱ ዘመንን ያቀዳጀን በመንፈሳዊ ሕይወት ታድሰን ተለውጠን አዲስ የተሻለ መንፈሳዊ ሰው እንድንሆን ነው። አዲስ ሰው መሆን ማለት ያለፈ ዘመንን ክፉ ግብር/ሥራ/ መተው፣ ደግሞም ኃጢአት ላለመስራት መታቀብና ራስን መግዛት ነው።እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ለመጨረሸዋ የፍርድ ቀን መልካምን ቃል የሚያሰማንን ተግባር ለማከናወን ለመልካም ሥራ መነሳሳት፣ የመንፈስ ፍሬያትን ማፍራት ያስፈልጋል። «የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው።» ገላ፭፥ ፳፪

“እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው።” (፪ኛ ቆሮ ፮፥፪) ባሳለፍነው ዓመት በሀገራችን ብሎም በዓለማችን እጅግ በጣም ብዙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶችን አሳልፈናል። ለአብነትም ያኽል በሰሜኑ እንዲሁም በተለየዩ በሀገራችን ክፍሎች እጅግ በጣም ብዙ ንጹሐን ሕይወታቸውን አጥተዋል ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ፣ ብዙ ሕጻናት ወላጅ አልባ ሆነዋል። ምንም በማያውቁት እጅግ በጣም ብዙ ንጹሐን የጦርነት ሰለባ ሲሆኑ ተመልክተን አዝነናል። እንዲሁም በተፈጥሯዊ ክስተት ደግሞ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በሰሜኑ እና በደቡቡ የሀገራችን ክፍል በመሬት መንሸራተት ምክንያት ብዙ ወገኖቻችን ለሞት ፣ ለከፍተኛ የአካል ጉዳት እንዲሁም ቀላል ለማይባል ለኢኮኖሚያዊ ፣ ለማኅበራዊ እና ለስነ-ልቦናዊ ጉዳት እንደተዳረጉ እንገነዘባለን።

በዚህ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቀውስ ምክያንት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን እግዚአብሔር አምላካችን ሐገረ ሕይወትን መንግስተ ሰማያትን እንዲያወርስልን ፣ ከቤት ንብረታችሁ ተፈናቅላችሁ ላላችሁ አምላካችን በሰላም ወደመንደራችሁ እንዲመልሳችሁ ፣ ቤተሰቦቻችሁን በሞት አጥታችሁ ላላችሁ ልጆቻችን መጽናናቱን እንዲልክላችኹ ሰላም ላጡ ሁሉ ሰላማቸውን እንዲመልስላቸው የዘወትር ጸሎታችን ነው።

በዘመነ ማቴዎስ እጅግ በጣም ብዙ የበደሉንን ይቅር ብለን ፣ የበደልናቸውን ክሰን ፣ ለሰው ሁሉ ፍቅርን ሰጥተን ፣ ፍቅርን በመቀበል ፣ የፍቅር አምላክ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች መሆናችንን በግልጥ የምናሳይበት የፍቅር ፣ የሰላም ፣ የደስታ ፣ የጤና ፣ የበረከትና የመተሳሰብ ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለጥፋት ፣ ሕዝቡ ለስደት የማይዳረግበት ዘመን ይሆንልን ዘንድ እንዲሁም ከኃጢአታችን በንስሐ ውኃ የምንታጠብበት፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ በቀራንዮ የቆረሰልንን ቅዱስ ሥጋውን የምንበላበት፣ ያፈሰሰልንን ክቡር ደሙን የምንጠጣበት ዘመን እንዲሆንልን እግዚአብሔር አምላካችንን በጸሎት ልንለምን ይገባል።

 

“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

“አስመ የአክለክሙ ዘኀለፈ መዋዕል ዘገበርክሙቦቱ ፈቃዶሙ ለአህዛብ”“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” /1ኛ ጴጥ. 4፥3/፡፡

“አስመ የአክለክሙ ዘኀለፈ መዋዕል ዘገበርክሙቦቱ ፈቃዶሙ ለአህዛብ”“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” /1ኛ ጴጥ. 4፥3/፡፡

ውድ ኦርቶዶክሳውያን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን

እንኳን ብርሃናት ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት የዓመት ዑደታቸውን ጨርሰው ለሚጀምሩበት ርእሰ ዐውደ ዓመት ለሆነው ለኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ።
የአዝማናት ባለቤት አምላካችን እግዚአብሔር ሳይገባን በዘመን ላይ ዘመንን እየጨመረልን በየዘመናቱም ብዙ መልካም ነገር እያከናወነልን ነው። ይህም የአምላካችንን ፍቅር የሚያስረዳንና በተጨመሩልን ዘመናት የትናንት ስህተታችንን አርመን የተጣላን እንድንታረቅ፣ የበደልን እንድንክስ፣ ግፍ ከመሥራትና ድሀን ከመበደል እንድንርቅ እንዲሁም ህገ ወንጌልን አምነን የታረዘን እንድናለብስ፣ የተጠማን እንድናጠጣ፣ የተራበን እንድናበላ እንጂ፤ በቀደመ የኃጢአት ሕይወት እንድንመላለስ እንዳልሆነ የሚያስታውሰን ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” እንዳለው ያለፈው ዘመናችንን ወደኋላ ትተን አሮጌውን ሰውነት አውልቀን አዲሱን ሰው በመልበስ የተጨመረልንን አዲስ ዓመት ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበት ከጠብ ከክርክርና ከመገዳደል የምንወጣበት በተግባረ ክርስትናና በፍቅረ ቢጽ የምናሸበርቅበት እንዲሆን አደራ እንላለን። አዲሱ ዓመት በሀገራችን ያሉ ክፉ ነገሮች ሁሉ ተወግደው ፍጡራን ሁሉ መውጣት መግባታቸው የሰላም እንዲሆን አምላከ ሰላም ወደሆነው አምላካችን ዘወትር እንጸልያለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
አባ ሕርያቆስ የሀድያ ስልጤ የደቡብና ምዕራብ
አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወሰብዓቱ ዓመተ ምሕረት

አዲሱ ዘመን በሃይማኖት መንፈስ ግጭትን በውይይት፤ መለያየትን በአንድነት፤ አለመግባባትን በዕርቅ ፈትተን በመታደስ ማማ ላይ የቆመ ማኅበረ ሰብን ለመገንባት ሁላችንም ጥረት እንድናደርግ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የበጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ውይይት አደረገ።

ሀገረ ስብከቱ የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም ጥቅል የሥራ አፈጻጸም ውይይት በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሐላፊ በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ መሪነት መከናወኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዛሬው ዕለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

የተከበራችሁ የሃገራችን ሕዝቦች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና ምዕመናን፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሀገርን ዳር ድንበር እና ሰላም ለማስከበር ቀን ከሌት የምትደክሙ የሠራዊት አባላት፣ በሕመም ምክንያት በቤታችሁ እና በሕክምና ማዕከላት የምትገኙ ሕሙማን፣ በማረሚያ ቤቶች የምትገኙ የሕግ ታራሚዎች በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የምትገኙ ውድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለ2017 ዓመተ ምሕረት የዘመን መለወጫ ባዕል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ፣ አደረሰን፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ቢገጥሟትም በፈጣሪ እርዳታ እና በሕዝባችን አስተዋይነት እንዲሁም  ትጋት ለማለፍ ችላለች፡፡ ሰላም በአንድ ቀን በሚሠራ በጎ ሥራ የሚገነባና የሚጠናቀቅ ባልለመሆኑ ሁላችንም በሃገራችን አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከግጭት ይልቅ እርቅን፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ለእኔ ብቻ ከሚል ክፉ አስተሳሰብ ለእኛ ማለትን፣ ከንቀት ይልቅ መከባበርን፣ ከልባችን በመምረጥ በአስተማማኝ ሰላሟ ተምሳሌት የሆነች እና ያደገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም በቅን ልቦና እንድንሰራ በፈጣሪ ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በተለይም በየደረጃው የምትገኙ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ፈጣሪ እና ሃገር የጣሉብንን ታላቅ ኃላፊነት እና አደራ ሰላምን በመስበክ እና በመጠበቅ፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳት እና  ፍትህ ላጡ እና ለተበደሉ ወገኖቻችን ድምጽ በመሆን ከምን ጊዜውም በላይ እንድንሰራ አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የምሕረት፣ የርህራሄና፣ የአንድነት እና የመረዳዳት ዓመት እንዲሆንልን በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስም እየተመኘን በዓሉን ስናከብር በተለመደው ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህል የተቸገሩትን በመርዳት እና በአዲሱ ዓመት በሃገራችን የተሟላ ሰላም ይሰፍን ዘንድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቃል በመግባት እንዲሆን በፈጣሪ ስም አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ/ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ