ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በእስር ላይ ለሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ለአዲሱ ዓመት ፳፻፲፯ ዓ.ም መዋያ የሚሆን የበሬ ሥጦታ አበረከተ።
ጳጉሜን ፭ ፳፻፲፯ ዓ/ም
ጳጉሜን ፭ ፳፻፲፯ ዓ/ም
“ካለፈው ዓመት ስህተት ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገር ማድረግ እና ለሁለንተናዊ ለውጥ ራስን ማዘጋጀት ይኖርብናል”።
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ” የዘመናት ባለቤት እግዚአ ሰማያት ወምድር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ 2017 ዘመነ ማቴዎስ የምሕረት ዓመት በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ” በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም:-
” አዲስ ዓመት፤ የዓመታት፣ የወራት፣የሳምንታት እና የቀናት ለውጥና መፈራረቅ ብቻ ሳይሆን ካለፈው ዓመት ስህተት ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገር ማድረግ እና ለሁለንተናዊ ለውጥ ራስን ማዘጋጀት እንዲሁም የለውጥን ሂደት ለመጀመር ቁርጠኛ መሆንን ይጨምራል።
ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ቅን ልቡና፣ ቅን ሕሊና እሰጣችኃለሁ በማለት የሚነግረን፤ ዛሬ ላይ እንደ ደንጊያ ጽኑ እና ጨካኝ የሆነው ልባችን ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን እየጎዳ ይገኛል። ቅን ልቡና እና የተሰበረ መንፈስ ጠፍቶ በጎቻችንን በምድራዊ ሀሳብ እና በቁሳዊ ተራ እይታ መመልከት ከጀመርን ሰንብተናል።
በተለይም በአባቶች ደረጃ ለተጠራንበት ተልዕኮ መሥራት ካቆምን፣ ልጆቻችንን አስጨናቂ አገዛዝ ከጫንባቸው እና የምንመራቸው ልጆቻችን በምንከተለው ኃላ ቀር የመሪነት ዘይቤ ተሰላችተው ተስፋ ከቆረጡ ቆይተዋል። ለዚህ ድካማችን መፍትሔውም የድንጋዩን ልብ ከውስጣችን አውጥተን የሥጋን ልብ ለማግኘት መሥራት እንጂ ለዘመናት በኖረ መቋጠሪያ በሌለው ችግሮች ውስጥ ሆነን በኛ ድክመት የፈታነውን ሕዝብ ልዩ ልዩ እንቆቅልሽ እየፈጠርን ግራ ማጋባት ሊጠቅመው አይችልም።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
ምእመናንና ምእመናት:-
አዲሱን ዓመት ስንቀበል በአሮጌው ዓመት የነበሩ የክፋት ሥራዎቻችን፣ የልዩነት መንገዶቻችን እና የጥፋት ዕቅዶቻችን በአዲሱ መንፈስ የሚሻሩበት፤ ከጨለማው አመለካከታችን ወጥተን የብርሃን መንገድን ልንከተል፤ ያለፈውን የጥፋት ሥራ ያበዛንበትን ዓመት በአዲሱ ዓመት በንስሐ ታጥበን ለእውነት ልንሰራ ይገባናል።
በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። እንዲል መጽሐፍ ቅዱስ በክፋት ባረጀው ሰውነታችን አዲስ ዘመንን መጨመር ከኃጢአት ላይ ኃጢአትን መጨመር እና የኃጢአት ክምርን ማብዛት ስለሚሆን ምን ጊዜም አዲስ ዓመትን ስንቀበል በንስሐ እና በጎ ተግባርን በማብዛት ሊሆን ግድ ይለናል።
አዲሱን ዓመት ስንቀበል፤ ራሳችንን ለለውጥ በማዘጋጀት፣ ሰላምን በመስበክ፣ ክርስቲያናዊ ተግባራትን በማብዛት፣የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት ሊሆን እንደሚገባ እያሳሰብን፤አዲሱ ዓመት የፍቅር፣የሰላም፣የአንድነት እና የስምምነት እንዲሆን እንመኛለን ፤በማለት አስተላልፈዋል።
+ አባ ሄኖክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ጳጉሜን ፭ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ሽዋ፣ የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ኃላፊ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት !
ወትባርክ አክሊለ አመተ ምሕረትከ፤በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ (መዝሙር 65-11)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ካህናት ዲያቆናት የመንፈስቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን
እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወንጌላዊ ወደዘመነ ማቴዎስ ወንጌላዊ በሰላም እና በጤና አሸጋገራችሁ
እንኳን አደረሳችሁ
ቀን እና ሌሊትን
ሳምንታትን እና ወራትን
አመታትን እና አዝማናትን እያፈራረቀ በዕድሜያችን ላይ ዕድሜን ጨምሮ ለአዲሱ ዘመን ያደረሰን ከዘመናት በፊት የነበረ ዘመናትንም አሳልፎ የሚኖር ለህላዌው ዘመን የማይቆጠርለት ቸሩ አምላካችን መድኃኔዓለም ስለማይነገር ስጦታው እስከዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን
እግዚአብሔር ለፍጥረታት ልዩ ልዩ ጸጋዎችን አድሏል
እግዚአብሔር ለምድር እስከዚህ ድረስ ተብሎ ሊቆጠሩ የማይችሉ አዝማናትን ሲሰጣት ለሰው ልጆች ደግሞ በአዝማናት ውስጥ የሚቆጠሩ ዕድሜያትን ይሰጣል
በእግዚአብሔር ቸርነት ምድር ዘመንን ስትቀይር የምታገኛቸው ልዩ ልዩ ጸጋዎች አሏት
በሚቀየረው ዘመን ውስጥ የምድር ገጽታ ይለዋወጣል
የደረቀው መሬት በዝናም ይርሳል
በዝናም የራሰው መሬት ቡቃያን ይይዛል
ቡቃያው ያፈራል
ቀላያት ሞልተው ይፈሳሉ
ተራሮች በአረንጓዴ ይሞላሉ
ከጊዜ በኋላ የለመለመው ሁሉ ረግፎ ምድር ወደ ባዶነት ትቀየራለች
የሰው ልጆች ዑደትም ይህን ይመስላል
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ዕድሜን ሲሰጥ
ሰዎች በተሰጣቸው ዕድሜ በኃጢአት የደረቀ ሕይወታቸውን በቅድስና እንዲያለመልሙ
በኃጢአት ያደፈ ማንነታቸውን በንስሓ እንዲቀድሱ
ከጥላቻ ሕይወት ወጥተው በፍቅር እንዲኖሩ
ከጦርነት ወደ ሰላም እንዲመለሱ
በአጠቃላይ ህገ እግዚአብሔርን ጠብቀው የእግዚአብሔርን መንግስት እንዲወርሱ ነው
እግዚአብሔር ዘመንና ዕድሜን ለሰው ልጆች ሲሰጥ ባለፉት ዘመናት የሰራናቸውን ክፉ ሥራዎች ይቅር ብሎ ከነዚያ ክፉ ሥራዎቻችን እንድንርቅ እና በንስሐ ወደ እርሱ እንመለስ ዘንድ ነው
ለዚሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመርያው መልእክቱ ምዕራፍ 4-3 ላይ
“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል።”
ብሎ ባለፈው ዘመን ከኖርንበት የኃጢአት መንገድ እንድንመለስ ያስተምረናል
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት
ዘመን አልፎ ዘመን ሲመጣ በደመና የጠቆረው ሰማይ ብርሃንን ይጎናጽፋል
ተራሮች ይለመልማሉ
ቆሻሻው በጎርፍ ታጥቦ ከምድር ይሠወራል
የደፈረሰው ውሀ ይጠራል
ምድር ፍሬን ትሰጣለች
የሰው ልጅ ግን ፊቱ በወንድሙ ላይ እንደጠቆረ ነው
ሰውነቱ በጽድቅ ከመለምለም ይልቅ በኃጢአት ደርቋል
ሰላምን ከመስበክ ይልቅ የጦርነት ዜና ማስተጋባትን መርጧል
ለወንድሙ መድኃኒት ከመሆን ይልቅ የወንድሙ ገዳይ ሆኗል
በእንደዚህ አይነት ሕይወት ውስጥ ሆኖ አዲስ ዘመንን መቀበል የእግዚአብሔርን ስጦታ ማቃለል ነው
ካለፈው መጥፎ ሕይወት ሳይመለሱ የዕድሜ ባለቤት መሆን በዕዳ ላይ ዕዳን መጨመር ነው
ስለዚህ ሁላችን ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት ከሚያልፈው አሮጌ ዘመን ጋር አሮጌ አስተሳሰባችንን በመጣል አዲሱን ዘመን እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መልካም አስተሳሰብ ልንቀበለው ይገባል
ይህን ካደረግን አምላካችን እግዚአብሔር ዘመናችንን ይባርክልናል
ምድራችን የሰላም ምድር ትሆናለች
በሰዎች መካከል ጥላቻ ጠፍቶ ፍቅር ይነግሳል
ከሁሉም በላይ በሚያልፈው ዘመንና በምታልፈው ምድር የምንሰራው መልካም ሥራ የማያልፈውን የእግዚአብሔር መንግሥት እንድንወርስ ይረዳናል
ዘመኑ የሰላም የፍቅር የአንድነት የዕርቅ የበረከት ዘመን ይሁንልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
መልካም አዲስ ዓመት
አባ ሳዊሮስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ ምዕራብ ሽዋ የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ኃላፊ
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዘመን መለወጫን በዓል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።
የብፁዕነታቸውን ሙሉ መልእክት እነሆ!!!
* * * * *
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ምድር ሠናይት እንተ ዘልፈ ይሔውጻ እግዚአብሔር አምላክከ ፤ ወአዕይንቲሁ ለእግዚአብሔር አምላክከ ላዕሌሃ እምርእሰ ዓመት እስከ ማኅለቅተ ዓመት ”
“አምላክህ እግዚአብሔር የሚጎበኛት አገር ናት ፤ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የእግዚአብሔር ዓይን ሁልጊዜ በርሷ ላይ ነው”ዘዳ ፲፩ ÷ ፲፪
የተወደዳችሁ እና የተከበራችሁ በቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ በመላው ዓለምም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር 2016 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን በሰላም እና በጤና አስፈጽሞ እንኳን ለ2017 ዓም ዘመነ ማቴዎስ በሰላም እና በጤና አደረሰን! አደረሳችሁ!!!
የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር ዘመንን በዘመን እየለወጠ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ 5500 ዓመተ ኲነኔ 2017 ዓመተ ምሕረት በአጠቃላይ 7517 ዘመን ይሆናል ።
እስራኤል ዘሥጋ በግብፅ ባርነት በነበሩበት ዘመን ተወልዶ በፈርኦን ቤት የፈርኦን ልጅ መባልን በእምነት እንቢ በማለት ያደገው ክቡደ መዝራዕት ሙሴ ከ4 መቶ 30 የግብፅ ባርነት ዘመን በኋላ እስራኤላውያንን ነጻ ለማውጣት በግብፅ እና በግብፃውያን ላይ ዘጠኝ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አሥረኛ ሞተ በኲርን አሥራ አደኛ ስጥመትን ፈጽሞ በርሱ መሪነት በመልአኩ ተራዳኢነት በእግዚአብሔር አሻጋሪነት ቀይ ባሕር ተከፍሎላቸው በደረቅ አልፈው ከሞት ወደሕይወት ከባርነት ወደነጻነት ከውርደት ወደ ክብር ተሸጋግረዋል ።
በመሆኑም የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ በጸናች የእግዚአብሔር እጅ እስራኤል ዘሥጋን ከግብፅ የባርነት ሕይወት ነጻ አውጥቶ ሊወርሷት ወደአለችው የአባቶቻቸው ርስት የተስፋይቱ ምድር ከነአን ለመግባት በሞአብ ሜዳ ላይ በጉዞ ለነበሩት ለእስራል አዲሱ ትውልድ የምትወርሷት የበረከት ምድር ከነዓን ዝናብ እንደማይዘንብባት እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም።
የቃል ኪዳን ምድር ከነዓን የዘሩባትን የምታበቅል የተከሉባትን የምታጸድቅ እግዚአብሔር የሚጎበኛት የእግዚአብሔር ዓይን በረድኤት የማይለያት መሆኑን በመግለጽ በውስጧ በሰላም ለመኖር የባርነት ቀንበራቸውን ሰብሮ መና ከሰማይ አውርዶ እየመገበ ውኃ ከዓለት ላይ አፍልቆ እያጠጣ ያሻገራቸውን የእግዚአብሔርን ሕግ እና ሥርዓት ጠብቀው እንዲኖሩ በአጽንኦት ሲመክራቸው እናስተውላለን።
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን አባቶቻችን በአጥንታቸው እና በደማቸው አጽንተው ያስረከቡን ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ስሟ በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ የተወሳ ልክ እንደተስፋይቱ ምድር ከነዓን 3 መቶ 65 ቀናት ስመ እግዚአብሔር የሚጠራባት ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጸምባት እግዚአብሔር ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ በምሕረት ሀገረ እግዚአብሔር በምሕረት ዓይኑ የሚመለከታት ፣ መዝበ ታሪክ ዓይኑ የሚመለከታት ሀገረ እግዚአብሔር ፣ መዝገበ ታሪክ ፣ የቅርስ ማዕከል እና የሰው ዘር መገኛ መሆኗን እናስታወሳለን።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለየ ሁኔታ ከውስጥና ከውጪ እየደረሰ ባለው ፈርጀብዙ የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት በአራቱም ማዕዘን በጦርነት ድምፅ እየተናጠች የፈተናና የመከራ ማዕበል እያንገላታት ትገኛለች።
በዚሁ ችግር ምክንያት የተነሳ በርካታ ወገኖቻችን መተኪያ የሌላት ውድ ሕይወታቸውን እያጡ ሲሆን ለዘመናት የደከሙበት ሀብት ንብረታቸው እየጠፋ ይገኛል።
ከቤት ቀያቸው ተፈናቅለው ለቀን ሀሩር ለሌሊት ቁር ተጋልጠዋል ፤ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ተለይተው የለጋነት እድሜያቸውን በከንቱ እያሳለፉት ይገኛሉ ፤ በአጠቃላይ በሀገራችን እየሆነ ያለውን ነገር ስንመለከት ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እንገነዘባለን።
በመሆኑም ከዘመነ ዮሐንስ ወደዘመነ ማቴዎስ ስንሸጋገር እስራኤል ዘሥጋ ከግብፅ ወደከነዓን ሲሻገሩ የግብፅን ትብት በግብፅ ቀብረው ከሞት ወደሕይወት ከባርነት ወደነጻነት እንደተሻገሩ እኛም እስራኤል ዘነፍስ ያረጀውን ሰውነት ገፍተን አዲሱን ሰውነት በመልበስ አሮጌውን የኃጢኣት ርሾ አስወግደን አዲስን የጽድቅ ርሾ ገንዘብ በማድረግ ጥላቻን አውልቀን ፍቅርን በመልበስ መለያየትን ተጸይፈን አንድነትን በመጎናጸፍ የክርስቶስ መልክ መገለጫ የሆነውን የሰውን ልጅ በሰውነቱ ብቻ በማክበር በአዲስ ልብ በአዲስ አስተሳሰብ በአዲስ መንፈስ ልንሻገር የሚገባ መሆኑን በአጽንኦት ማሳሰብ እንፈልጋለን ።
ዘመነ ክረምት አልፎ አዲሱ ዓመት ሲገባ መስከረም ሲጠባ የወንዝ ውኃዎች ይጠራሉ አበባዎች ይፈካሉ የእኛም ሕይወት በንስሓ ውኃ ሊጠራ በበጎ ነገር ሁሉ ሊፈካ በአዲሱ ዓመት አዲስ ማንነት ሊኖረን ያስፈልጋል።
በመጨረሻም የዘመን መለወጥ ለሰው ልጅ ሕይወት ትርጉሙ ከፍ ያለ በመሆኑ በሕይወታችን ተለውጠን ስለ ሀገራችን እና ስለሕዝባችን በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት በመጸለይ የሰላም ሰው ሆነን ለሰላም የልባችንን በር በመክፈት እጃችንን ለፍቅርና ለአንድነት በመዘርጋት በማረሚያ ቤት ፣ በሆስፒታል እና በተለያየ ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን በመጠየቅ ፣ ያለንን ለሌላቸው ወገኖቻችን በማካፈል በይቅርታ ልብ መጪውን አዲሱን ዓመት እንድንቀበለው በማለት መልእክታችንን እናስተላልፋለን ።
መጪው አዲሱ ዘመን ዘመነ ማቴዎስ ሞት እና ጦርነት የሚቆምበት የጥይት ጩኸት የማንሰማበት የሀገራችን ችግር የሚፈታበት የሰላም የፍቅር እና የበረከት ዘመን እንዲሆንልን መልካም ምኞታችንን በመጸለይ ጭምር እንገልጽላችኋለን ።
ቅዱስ እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!!!
አባ ቀሌምንጦስ
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ!!!
ጳጒሜን ፭ ቀን ፲፫ ወር ፳፻ ፲፮ ዓም
ሺዋ ደብረ ብርሃን ኢትዮጵያ!!!
“ይህ ዓመት ለሕዝባችን፣ ለሀገራችንና ለዓለማችን ሰላም፣ ደስታና መንፈሳዊ እድገት እንዲያመጣ የዘወትር ምኞቴና ጸሎቴ ነው” ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የዩኬ፣ አየርላንድና የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ሊቀ ጳጳስ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ መልእክት አስተላልፈዋል። የብፁዕነታቸው መልእክት ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
‘‘ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዓይን ሁልጊዜ በርስዋ ላይ ነው።’’
ኦሪት ዘዳግም ፲፩:፲፪
በዚህ የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ዕለት ሰፊ በሆነው ምሕረቱ ፣ ጥልቅ በሆነው የአባትነት ፍቅሩ ለሰከንዶች በማይቋረጠው ጥበቃውና እንክብካቤው ሳይለየን ከዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ አሸጋግሮ ለዚህ ቀን ላደረሰን ሁሉን ቻይ ለሆነው ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋናችንን በፊቱ እናቀርባለን።
በኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 11 ቁጥር 12 ላይ ያሉት አምላካዊ ቃላት አልፋና ኦሜጋ የሆነው አምላችን ልዑል እግዚአብሔር በዘመናት ውስጥ ሁሉ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር የሚያስገነዝብና በተለይም በኦርቶዶክሳዊው ቅዱስ ትውፊት የእግዚአብሔር መግቦትና እንክብካቤ በሕይወታችን ዘመን ሙሉ እንደሚሰራና በፍጹም አባትነቱ እንደሚመራን የምንገነዘብበት ክፍል ነው።
በጥንታውያን ቅዱሳን አባቶቻችን ትምህርትና ሕይወት ባማረውና ባሸበረቀው የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜያችን ይህ ክፍል እግዚአብሔር ፍጥረታቱን ፈጥሮ የተወ ሳይሆን ይልቁንም ከፍጥረታቱ ያለተለየ የፍጥረታት ሁሉ መጋቢና ጠባቂ መሆኑን እንመለከትበታለን።
አበው እንደተረጎሙትም ‘‘የእግዚአብሔር ዓይን’’ ተብሎ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የተጻፈልን ቃል እግዚአብሔር በፍጥረታቱ ላይ የሚያፈሰውን የማያቋርጥ መግቦት፣ ጥበቃ፣ መሪነትና በረከተን የሚያሳይ ነው። ለዚህም ወደር የለሽ መለኮታዊ እንክብካቤ የማያቋርጥ የምስጋና እና የመታዘዝ ሕይወትን በመምራት ራሳችንን በምላሹ ለእርሱ መስጠት ይገባናል።
የ ፳፻፲፯ ዓመተ እግዚእ አዲስ ዓመትን ስንጀምርም፣ ያለፈውን ዓመት እንዴት እንደተጓዝነውና እንዳሳለፍነው በማሰላሰል ልባችንን ለመንፈሳዊ የሕይወት ለውጥና ዕድገት ዝግጁ ማድረግ ይገባናል። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የጊዜያችንን አላፊ መሆንና የተሰጠንንም ጊዜ በጥበብ መጥቀም እንዳለብን ካስገነዘበ በኋላ በጥበብ መመላለስ እንደሚገባን ‘‘በልብ ጥበብን እንድማር ቀኝህን እንዲህ አስታውቀን’’ (፹፱:፲፪) በማለት ያስተምረናል።
ጥበብን ማወቅ ማለት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ፣ ሀሳብና መንገድ መጓዟን ፣ ፍትሃዊ መሆንን ፣ ምሕረት ማድረግ መውደድንና ይልቁንም እንደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትህትና በምድር ላይ መመላለስና መኖር መቻል ነው።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን በእያንዳንዷ ቅጽበት እግዚአብሔርን በማሰብና የእርሱን ከእኛ ጋር መሆኑን ማስተዋል እንደሚገባን ታስተምራለች። የሥርዓተ አምልኮ ማዕከልም ከተሰጠን ከእስትንፋሳችን ጀምሮ ለማያልቀው ከእርሱ ለተቀበልነው ልዩ ልዩ ስጦታዎቹ የማያቋርጥ ምስጋናን ማቅረብና ከእርሱ ያልሆነ ምንም ነገር እንደሌለ ማስገንዘብ ነው።
ቅዱስ ዳዊት ‘‘በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ ፣ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል’’ (፷፬፡፲፩) በማለት እንደዘመረው ፈጣሬ ዓለማት ልዑል እግዚአብሔር ዘመናትን የበረከቱን አክሊል ያቀዳቸዋል። እኛም ልጆቹ በጸሎት፣ በመልካም ሥራና እርሱ ለመምሰል በሚደረግ ክርስቲያናዊ ጉዞ እንድንጓዝ ተጠርተናል።
በመሆኑም አሮጌው አልፎ አዲሱን ዓመት ስንቀበል ቅዱስ ጳውሎስ በ ፪ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ‘‘ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው’’ (፭:፲፯) በማለት የጻፈልንን ቃል ማሰብና እንደ ቃሉ መኖር ይገባናል።
ይህ ከእግዚአብሔር የተሰጠን አዲስ ዓመት ምድራዊ ለውጥን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም መንፈሳዊ የሕይወት ለውጥ እንድናመጣና ዕድገትንም እንድናሳይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠን አዲስ የንስሐ ጊዜ እንደሆነ እናስብ። ይህ የመንፈሳዊ ሕይወት ለውጥም በቤተክርስቲያናችን ውስጥ በጾም፣ በጸሎትና በቅዱሳት ምሥጢራት አማካኝነት በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ መሆኑን እናስተውል።
በዚህ አዲስ ዓመት በእነዚህ ከእግዚአብሔር በተሰጡን ቅዱሳት ምሥጢራት አማካኝነት በኃጢአት የጎሰቆለውን አሮጌውን እኛነታችንን ትተን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማያቋርጥ መንፈሳዊ ዕድገት ውስጥ መገኝት ይገባናል።
የተወደዳችሁ አበው አባቶቻችንና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ፣
ይህንን አዲስ ዓመት ስንጀምር ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ፣ በጸሎት ሕይወታችን በመበርታት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባሳየን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር እርስ በእርሳችን በመዋደድ ለቤተክርስቲያናችን ፣ ለሀገራችን ብሎም ለዓለማችን የሰላም ምሳሌዎችና ምንጮች እንሆን ዘንድ በልዑል እግዚአብሔር ስም እማጸናችኋለሁ።
ይህ ዓመት ለሕዝባችን፣ ለሀገራችንና ለዓለማችን ሰላም፣ ደስታ እና መንፈሳዊ ዕድገት እንዲያመጣ የዘወትር ምኞቴና ጸሎቴ ነው።
በዚህ አዲስ ዓመት ዘላለማዊ የሚሆን የሰማይ ቤታችንን ብቻ መመልከት እንችል ዘንድ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና እና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃ፣ ረድኤትና በረከት ይደርብን ! ከዚህ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ የእግዚአብሔር በረከቱ፣ ፀጋው፣ ፍቅሩ እና ጥበቃው ከእኛ ጋር ይሁን! አሜን።
‘‘የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታና ሰላምን ሁሉ ይሙላባቹሁ ’’ሮሜ ፲፭: ፲፫
አባ ያዕቆብ
የሩቅ ምሥራቅ፣ እንግሊዝ፣ አየርላንድና
አካባቢው ሀገራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
“…እርስ በእርሳችኹ በሰላም ኑሩ።” ፩ኛ ተሰ. ፭፥፲፫
እግዚአብሔር ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችንን በሰላም ይጠብቅልን።
በዓሉ የተቀደሰ፣ የሰላም፣ የደስታና የጤና እንዲኾንላችኹ እመኛለኹ።
*ልዑል እግዚአብሔር የተቀደሰ ዐዲስ ዓመት ያድርግልን።*
አባ ዲዮናስዮስ
የምሥራቅ ጎጃም፣ እና የጀርመን አካባቢው
አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የመቱ ፈለገ ሕይወት መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።
” በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። መዝ.65:11 የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ቃል መሠረት አድርገው መልእክታቸውን አስተላለልፈዋል።
ፈጣሪ ዘመናትን አሳልፎ አዲሱን ዘመን የሚያሳየን በመልካምነታችን ሳይሆን በምህረቱ ብዛት ነው ያሉት ብፁዕነታቸው፤ሁሌም ዓዲስ ዘመን የሚሰጠን ለሥራና ለለውጥ ነው ብለዋል።አዲሱን ዓመት ስንቀበል በሳለፍነው አሮጌ ዓመት ምን የጎደለን ነገር አለ?ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅና ምናልባታም ባጠፋነው ጥፋት ተጸጽተን ንሰሀ ገብተን እንመለስ ዘንድ አዲሱ ዘመን በቸርነቱ ተሰጥቶናል ብለዋል።
በሀገሪቷ ውስጥ በሁሉም ስፍራ ሠላም መጥፋቱ ዋና አጀንዳ ሆኗል ያሉት ብፁዕነታቸው ፤ በእኛ መሀል ሠላም የለም ፣ሁሌም መጣላት የሰርክ ተግባራችን ሆኗል፤ በየስፍራው የሚሰማው ዜና አሳዛኝ እየሆነ መጥቷል፣ጦርነት ሀገሪቷን ወደ ኋላ እየመለሳት ነው፣ ይህ ሁሉ የበደላችን ውጤት ነውና በአዲሱ ዓመት ወደ ልባችን ተመልሰን ልንለውጥ ይገባናል ብለው የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሠላምን አብዝተው በመስበክ በሕዝብ መሀል ስምምነትና መተማመን እንዲኖር መስራት አለባቸው ብለዋል።
የሰው ልጅ በችሮታ የተሰጠውን ጊዜ ተጠቅሞ ካልተለወጠ የተለወጠ ዘመን ማክበሩ ጥቅም የለውም ብለዋል። ብፁዕነታቸው አያይዘው በርካትቶቻችን በአዲሱ ዘመን አስበን ልብሳችንን እንቀይራለን እንጂ ልባችንን አንቀይርም ብለው በውስጣችን ያለው የድንጋይ ልብ አውጥተን የሥጋ ልብ የምህረትና የፍቅር ልብ ሊኖረን ይገባል በለዋል።
በአዲሱ ዘመን ጋራና ሸንተረሩ አበባን ለብሰው ደምቀውና አምረው ተቀይረው ይታያሉ ያሉት ብፁዕነታቸው የሰው ልጅ ግን አይቀየርም ከምድር አበባ አንሰናልናል በእውነት ወደ ፈጣሪያችን መመለስ አለብን ብለው ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ እንደሚጠፋ እንስሳ እየሆነ መምጣቱ አሳሳቢ ነውና በተጨመረልን ዓዲሱ ዘመን ልንመለስ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች፣በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ለሀገረ ስብከታችን ሕዝብ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወንጌላዊ ወደ ዘመነ ማቴዎስ ወንጌላዊ በሠላምና በጤና አሸጋገረን አሸ፡ሀጋገራችሁ ብለዋል!
ጳጉሜ 5/2016 ዓ. ም
የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሚዲያ
መስከረም ፩ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የፌስቡክ ገጽ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፤ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም።”
“በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።” መዝ ፷፬÷፲፩
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ከሁሉ አስቀድሜ ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን ያለፈውን ዓመት በሰላምና በጤና በሕይወት ጠብቆ አሁን ላለንበት ጊዜና ሰዓት ያደረሰን ፈጣሪ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።
ውድ የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት የሆነችው የበረሃዋ ንግስት የድሬዳዋ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጪው ዓለም የምትገኙ ውድ ኦርቶዶክሳውያን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችንና መላው የሀገራችን ሕዝቦች በሙሉ።
እንኳን ለ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን የሰላም አምላክ የፍቅር ጌታ የደስታ ሁሉ ባለቤት መጪውን ጊዜ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ ጌታ እግዚአብሔር ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለቤተክርስቲያናችን ሰላምና ፍቅር ሰጥቶን በጋራ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን የምናለማበትና የምናሳድግበት የተጣላን የምንታረቅበት ከድኅነት ከችግር ነፃ የምንወጣበት የበረከትና የይቅርታ ዓመት ያድርግልን። ውድ ኦርቶዶክሳውያን መላው የሀገራችን ሕዝብ ሆይ እግዚአብሔር አምላክ በደላችንን ይቅር እንዲለን ከክፋት፣ከተንኮል፣ከሀሜት፣ከዘረኝነት ጸድተን በንጽህናና በቅድስና ሆነን ዘወትር ሁሉን ማድረግ ወደሚችለው አምላክ እንጸልይ ጌታ እግዚአብሔር ተአምራትን ያደርጋል ዓመቱን የሰላም፣የፍቅር፣የይቅርታ፣የአንድነት ያድርግልን አሜን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ !
አባ በርተሎሜዎስ
የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
መስከረም ፩ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
ድሬዳዋ ኢትዮጵያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፧ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳሞ፤ በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።”መዝ. ፷፬÷፲፩
ቸርነትና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነለት አምላካችን አግዚአበሔር ወሰን በሌለው አባታዊ ፍቅሩና መግቦቱ ሳይለየን ጠብቆና አቆይቶ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ ከ፳፻፲፮ ዓ.ም ወደ ፳፻፲፯ ዓ.ም በሰላምና በጤና አሸጋገረን
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የአንድነት፣ የሥራ፣ የመግባባትና የፍቅር ዓመት ይሁንልን።
እግዚአብሔር አምላክ አገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን።
አባ ዲዮስቆሮስ
የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከ፣የቤተ መጻሕፍት ወመዘክርና የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ
ጷጉሜ ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም