ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የቢሮ ዕድሳት ሥራ ያለበትን ደረጃ ተመለከቱ

መጋቢት 20ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የሚያከናውነውን የቢሮ ዕድሳት ሥራ አፈጻጸምን ከጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ዛሬ ረፋዱ ላይ ተዘዋውረው ተመለከቱ።
ብፅዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ድርጁቱ የሚያከናውነው የቢሮ ዕድሳት ሥራ የደንበኛችን ምቹ አገልግሎት የማግኘት ዕድልን የሚያሰፋውንና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክትና በሰጡት የሥራ መሠሪያ ገልጸዋል። አያይዘውም የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት አሰራሩን ለማዘመንና ተደራሽነቱን በማስፋት አሰራሩን ከደንበኛ ተኮር የአገልግሎት ዐይነት ጋር በማቀናጀት ለመፈጸም የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው ይህንን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግም ከቤተክርስቲያን ምንም አይነት ወጪ ሳይጠይቅ በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር ቢሮውን በዘመናዊ መልኩ ማደስና ማደራጀት መጀመሩ የሚደነቅና የሚያስመሰግን ተግባር ነው ብለዋል።
ድርጅቱ በፍጥነት በመለወጥና በማደግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ይህንን በመምራትና በማስተባበር በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱት የድሮጅቱ ዋና ሦራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ ምስጋናና አድናቆት ይገባቸዋል። ካሉ በኋላ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የቢሮ ዕድሳት ሥራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ከእድሳት ሥራ አፈጻጸሙ መቀላጠፍ የተረዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ዜና ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በጠቅላይ ቤተክህነት አካባቢ የሚኖሩ ወገኖች በአካባቢው የተጋረጠውን የእሳት አደጋ የመፈጠርን ዕድል ተከትሎ በአስቸኳይ እንዲነሱ
የሚደረጉ ነዋሪዎች በጊዜየያዊነት የሚያርፉበት ቦታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት አማካኝነት በልደታ አካባቢ እየተሰራ መሆኑን ተከትሎ የጊዜያዊ ማረፊያ ቤት የግንባታ ሂደትን በትላንትናው ዕለት የተመለከቱ ሲሆን ድርጅቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን የመሰለ ማረፊያ ቤት በመስራት ዝግጁ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል።
በመጨረሻም የተጀመረውን የጊዚያዊ ማረፊያ ቤቶችን ግንባታ
በአስቸኳይና በጥራት በማጠናቀቅ ነዋረመዎችን የማዘዋወሩን ሥራ በፍጥነት ማከናወን እንደሚገባ ገልጸው ነዋሪዎቹ በሚያርፉበት ቦታ ላይ መብራት፣ውኃ፣መጸዳጃና ማብሰያ ቦታውች በአስቸኳይ ተሟልተው እንዲጠናቀቅ መመሪያ ሰጥተዋል።በአሁኑ ጊዜ በልደታ አካባቢ የሚከናወነው የግንባታ ሥራ ከሰማኒያ በመቶ በላይ የተጠናቀቀ ሲሆን በሦስት ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አልቆ ነዋሪዎችን የማዘዋወሩ ሥራ እንደሚጀመርና በፒያሳ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቶቹ ተሰርተው ነዋሪዎችን የማዘዋወሩ ሥራ እንደሚከናወን የድርጅቱ የዕቅድና ልማት ክፍል ኃላፊ መምህር ታዲዮስ ሽፈራሁ ገልጸዋል።

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ሥልጠና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከትናት በተሻለ መልኩ ለመሥራት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ገለጹ

መጋቢት ፲፯ / ፳፻፲ወ፰ ዓ.ም
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ሥልጠና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከትናት በተሻለ መልኩ ለመሥራት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ገለጹ።
ብፁዕነታቸው ይህንን የይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍልና የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ ክፍል በጋራ ባዘጋጁት የአንድ ቀን ሥልጠና ላይ ነው።
በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ለሠልጣኞች አባታዊ መመሪያና ቡራኬ ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው ሥልጠና በቤተ ክርስቲያንናችን አገልገሎት ውስጥ ከትናት የተሻለ ለመሥራት በእጅጉ እንደሚያስፈልግ አሳስበው በቀጣይም እንዲህ ዓይነቶች መርሐ ግብራት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
አክለውም ሀገረ ስብከቱ ከባለፈው ዓመት በበለጠ መልኩ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ በመፈጸም አርአያነት ባለው መልኩ ጥሩ የአገልግሎት አፈጻጸም እንዲኖረው አሳስበዋል።
በዕለቱ በመምህራነ ወንጌል አማካኝነት የቀረቡት ሦስት ዋና ዋና የሥልጠና ርዕሶች በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ላይ ተመሥርተው በዕቅበተ ዕምነት ፣ መልኩ ጥልቅ ትንተና ተሰጥቶባቸዋል፦
💠ዕቅበተ እምነት (Apologetics) በላዕከ ወንጌል መምህር ለሜሳ ሚልኬሳ፤

💠ወጣትነትና መንፈሳዊነት በመጋቤ ወንጌል ሄኖክ ታዬ ፤

💠በሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን፤ ሐዋርያዊ ተልዕኮአችን በዘመናችን በመጋቤ አእላፍ ተስፋዬ ቂጤሳ ጥናታዊ መነሻ ትምህርታዊ ጽሐፎች ቀርበዋል።
በቀረቡት ጽሑፎች ላይ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከተሳታፊዎቹ ጥያቄና አስተያያት ቀርቦባቸው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መልአክ ሰላም ቀሲስ ዓለማየሁ ተፈራ የሸገር ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ፣መጋቤ አእላፍ ተስፋዬ ቂጤሳ የስብከተ ወንጌል ዋና ሐላፊ ፣ መጋቢ ወንጌል ሄኖክ ታዬ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ሐላፊ፣ የክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጆች ፣ የክፍለ ከተማ የስብከተ ወንጌል ክፍል ሐላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት ሰባክያንና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አመራሮች በሥልጠናው ተሳትፈዋል።
©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት