ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በሀገረ ስብከቱ ለካህናት የሚሰጠውን ሥልጠና በጸሎትና በቡራኬ አስጀመሩ።

ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም
በጉራጌ ሀገረ ስብከት ለሚገኙ ካህናትና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የሚሰጠው የካህናት ሥልጠና በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጸሎት፣ ቡራኬና አባታዊ መመሪያ ተጀምሯል።
ይህ በሀገረ ስብከቱ በየጊዜው ከየወረዳው ካህናትን በመመልመል የሚከናወነው የማሠልጠን ተግባር፥ ብፁዕነታቸው በሀገረ ስብከቱ ከወጠኗቸውና ትኩረት ከሰጧቸው የሰው ኃይል ግንባታና ልማት ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በዚህም መሠረት በዘንድሮው መርሃ-ግብር ከ11ዱም ወረዳ ቤተ ክህነት ተመልምለው የተላኩ አገልጋዮች በሥልጠናው ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ብፁዕነታቸው በቃለቡራኬአቸው ይህ ሥልጠና አገልጋዮች ዘመኑን የዋጀ መንፈሳዊ አገልግሎት ለምዕመናን መስጠት እንዲችሉና የአገልግሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለዚህም አገልጋዮች በእውቀት ላይ የተመሠረተ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት እንዲሁም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማዕከል ያደረገ አገልግሎት እንዲሰጡ ሥልጠናው ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል።
በመጨረሻም ሥልጠናውን እየተከታተሉ የሚገኙ አገልጋዮች የተሰጣቸውን ወርቃማ ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፤ የሚያገኙትን የቤተ ክርስቲያን እውቀት በማሳታወሻቸው እንዲጽፉና በልባቸው እንዲከትቡ አባታዊ ጥሪ አቅርበዋል።
የወጣው መርሃ-ግብር እንደሚያሳየው ሥልጠናው እስከ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፥ ሰኔ 20 ቀን 2018 ዓ.ም የምስክር ወረቀት በመስጠት ይጠናቀቃል ተብሏል። ይህ የምስክር ወረቀት ግን የአገልግሎት ማጠናቀቂያ ሳይሆን ወደ ላቀ መንፈሳዊ ሥራ መሸጋገሪያና አዲስ አገልግሎት ማስጀመሪያ መሆኑ ብፁዕነታቸው በአጽንኦት አሳስበዋል።©ሳሌም ሚዲያ

ቋሚ ሲኖዶስ በምሥራቅ አርሲ ተገኝተው የተጎዱ ወገኖችን የሚያጽናኑ በፁዐን አባቶችን መደበ።

ግንቦ 28 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ኦርቶዶክሳዊያን የሚያጽናኑ ብፁዓን አባቶችን መደበ።
የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በአሰኮ፣ በሺርካ፣ በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በዛሬው ዕለት ባካሔደው መደበኛ ስብሰባው በችግሩ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግ፣በብፁዓን አባቶች የሚመራ የቤተ ክርስቲያናችን ልዑካን ቡድን ችግሩ ወደ ተፈጠረበት ቦታ በመሄድ ተጎጂዎችን እንዲጎበኝ፣ እንዲያጽናና እና አስፈላጊውን ጊዜያዊ ድጋፍ አንዲያደርግ ወስኗል።
ቋሚ ሲኖዶስ በጠቅላይ ቤተክህነት በኩል በሚቋቋም
ኮሚቴ አስተባባሪነትም በተፈጠረው ችግር ምከንያት የመቃጠል አደጋ የደረሰበት ጥንታዊው የጠላታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን እንዲያሰራ፣ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በቋሚነት ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ የሚዲያደርግ፣ በሀገረ ስብከቱ ዳግመኛ መሰል ችግሮች እንዳይፈጠርሩ ጥናት አካሒዶ ከመፍትሔ ሐሳብ ጭምር የሚያቀርብ ዐቢይ ኮሚቴ ተሰይሞ በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲገባ ወስኗል።
በትላንትናው ዕለት በምሥራቅ አርሲ አንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተውን ችግር ተከትሎ ፦
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
ብፁ አቡነ ዲዮስቆሮስ
ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ከፌዴራል ሰላም ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተከሰተው ችግር ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የሚመራ የቤተክርስቲያናችን የልዑካን ቡድን ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሰላም ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያየ።

ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት አንዳንድ ወረዳዎች በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ሕልፈተ ሕይወትና የቤተ ክርስቲያን መቃጠልን በማስመልከት የተሰማትን ጥልቅ ኀዘን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አማካኝነት ከገለጸች በኋላ ቋሚ ሲኖዶስ በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተመራ ከፍተኛ የቤተክርስቲያናችን የልዑካን ቡድን ከሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ፣
ከሚኒስትር ዲኤታው ከዶ/ር ኸይረዲን ተዘራና ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስሮስ በምሥራቅ አርሲ በአሰኮ፣ በሺርካ፣ በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ በደረሰው የሕይወት ጉዳት እና በጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን መቃጠል እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው መንግሥት የችግሩን ምንጭ አጣርቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግና በአካባቢውም አስተማማኝ ሰላምን እንዲያሰፍን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በችግሩ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትና መልሰው የሚቋቋሙበት ሥራ እንዲሠራ፣ ወንጀሉን የፈጸሙ ሰዎችም ለፍርድ ቀርበው
ቅጣታቸውን እንዲያገኙ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የምሥራቅ አርሲና የጅግጅጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሀገረ ስብከታቸው የተከሰተውን ችግር በማስመልከት ዝርዝር መረጃዎችን በቊጥራዊ ማስረጃዎች አስደግፈው አቅርበዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው
በተፈጠረው ችግር እጅግ በጣም ማዘናቸውን ገልጸው በመንግሥት በኩል በአስቸኳይ አጣሪ ቡድን ተቋቁም ወደ ስፍራው ተልኳል ካሉ በኋላ የአጣሪ ቡድኑን ሪፖርት መሠረት በማድረግም አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ብፁዓን አባቶቻችን በኦሮሚያ ፕ/ት ጽ/ቤት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ከብልጽግና ፓርቲ ድ/ ቤት አመራሮች ጋር ዝርዝር ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ወቅት የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት በሥፍራው የተከሰተውን ችግር ለመቆጣጠርና ሊከሰት ይችል የነበረውን ተጨማሪ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን፣ በአሁኑ ወቅትም ወደ ሥፍራው አጣሪ ቡድን መላኩንና የማጣራት ውጤቱን ተከትሎም አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ቤተክርስቲያኗ ምዕመናንን ለማጽናናትና ድጋፍ ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ሁሉ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግላት ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ፣ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንዲሁም የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያን መልሶ ለመገንባት እና በአካባቢው ዳግመኛ መሰል ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚያከናውኑ ከልዑካን ቡድኑ ጋር ባደረጉት የማጠቃለያ ውይይት ገልጸዋል።

የራሺያ ቤተክርስቲያን ልኡካን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጉብኝት አደረጉ።

ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም
ልኡካኑ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እና ከብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ የራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል ።
ከልኡካኑ መካከል የሞስኮ ፓትርያርክ የውጭ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት መምሪያ ሊቀመንበር የሆኑት የቮሎኮላምስክ ሜትሮፖሊታን አንቶኒ የራሺያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር ያላትን መንፈሳዊ አና ታሪካዊ ግንኙነት አንስተው በቀጣይም የጋራ ሥራዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል ።
አያይዘውም በሩሲያ የቲዎሎጂ አካዳሚዎች ከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ወደ ራሺያ ማቅናታቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር መቻሉን ገልጸዋል።
ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፣የደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በበኩላቸው የራሺያ ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያለፋበት መንገድ ተመሣሣይነት ያለው መሆኑን አንስተው በበርካታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መወያየታቸውን ተናግረዋል ።©Eotc tv

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በአርሲ ሀገረ ስብከት በቤተ ክርስቲያናችን እና በኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰውን ጥቃት በማስመልከት አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።

ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት አባታዊ የኀዘን መልእክት እንደሚከተለው ነው፦
መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
‹‹ወረሰዩ አብድንቲሆሙ ለአግብርቲከ መብልዐ ለአዕዋፈ ሰማይ፣ ወሥጋሆሙኒ ለጻድቃኒከ ለአራዊተ ገዳም፦ የአገልጋዮችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ፥ የቅዱሳንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት።››
(መዝሙረ ዳዊት ፸፰፥፪)
በአርሲ ሀገረ ስብከት በአሰኮ፣ በሽርካ፣ በሆንቆሎ፣ በዋቤ እና በሙኔሳ ወረዳዎች በመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችንና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ጥቃት የሰማነው በተሰበረ ልብ ነው።
የእምነት ነፃነት ተደፍሮ መቶ ዓመታት ያስቆጠረው የጠላታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በተቃጠለበት፣ እንዲሁም የካራ ኩፍቴና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በተዘረፈበት በዚህ ክፉ ቀን፤ በርካታ ምእመናን በግፍ መሰዋታቸውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘነ ክስተት ነው።
የሰላም፣ የፍቅርና የታሪክ ማህደር የሆነችው ቤተ ክርስቲያን በምድራዊ መከራ ውስጥ ያሉትን ምእመናን በምታጽናናበት በዚህ ወቅት ራሷ በፈተና ውስጥ ሆና ከመቸገሯም በላይ በአርሲ ምድር በተደጋጋሚ የሚስተዋለው በደልና ግፍ በሁላችንም ልቡና ውስጥ “እስከ መቼ?” የሚል የቁጭት እና የኀዘን ጥያቄን ፈጥሯል።
በመሆኑም ይህ መከራ እያበቃ ሳይሆን እየሰፋ በመምጣቱ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅና ሰላምን የማስፈን አደራ የተጣለባችሁ የጸጥታ አካላትና በየመዋቅሩ ያላችሁ ሓላፊዎች ከምንም በላይ ታሪክ የሚጠይቃችሁ በሥልጣን ዘመናችሁ ለዜጎች ደኅንነት በምትከፍሉት ዋጋ ነውና ይህንን የጥቃት ሰንሰለት በማስቆምና ወንጀለኞችን ለሕግ በማቅረብ ከታሪክ ባለዕዳነት ትድኑ ዘንድ በቤተ ክርስቲያናችን ስም አበክረን እናሳስባለን።
በየአካባቢው የምትገኙ ምእመናንና መላው ኢትዮጵያውያንም በወንድማማችነት መንፈስ ተጋግዛችሁ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና በጸሎት ከቤተክርስቲያናችን ጎን እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያናችን ለሰላም፣ ለይቅርታና ለሰው ልጆች ክብር ሁል ጊዜ የምትቆም መሆኑን በመግለጽ ይህንን የኀዘን ሰዓት አምላካችን በምሕረቱ ያሳልፍልን፣ የሞቱትን ነፍሶቻቸውን በመንግሥቱ ይቀበልልን፣ የተጎዱትንም በቸርነቱ ያጽናናልን በማለት አባታዊ የኀዘን መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
© የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት

ቅዱስ ፓትርያርኩ በቫቲካን በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ክፍል ኃላፉ ብፁዕ ካሪዲናል ክላውዲዮ ጉጀሮቲን በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፲፰ ዓም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በቫቲካን በቅድስት መንበር የምሥራቅ ክርስቲያናት ክፍል ኃላፉ ብፁዕ ካሪዲናል ክላውዲዮ ጉጀሮቲን በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
ቅዱስነታቸው ልዑካኑን “ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት እንኳን ደህና መጣችሁ፣ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ለመጎብኘት ስለመጣችሁ ደስ ብሎናል፤ መልካም የጉብኝት ወቅት ያድርግላችሁ” በማለት መልካም ምኞታቸውን ለልዑካኑ ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ ካሪዲናል ክላውዲዮ ጉጀሮቲም እንደተናገሩት “በመጀመሪያ መልእክቴ በፖፕ ሊዮ የተላከ የፍቅር መልእክት ለማድረስ ነው፡፡ ወደዚህች ምስጠራዊ ሀገር፣ የብዙ ሰማዕታት፣ መነኮሳት፣ የብዙ መንፈሳውያን ሀገር ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የመጣሁት” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ ካርዲናል ክላውዲዮ አያይዘውም “በዓለማችን በክርስቲያኖች ላይ እየተላለፈ ያለው ጥላቻ እየጨመረ መጥቷል፤ በዚህ ጉዳይ በቫቲካን ያለንም ሐሳብ ውስጥ ገብተናል፤ ክርስቲኖችን ለመታደግ በአንድነት አብረን መሥራት አለብን” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት “ሁላችንም በችግር ውስጥ ነው ያለነው፤ በዚህ ወቅት በኅብረት መሥራት፣ መነጋገር አስፈላጊም፣ ወቅታዊም ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ያለን መሣሪያ ጸሎትና ምህላ ብቻ ነው፡፡” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡©Eotc tv