ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በሀገረ ስብከቱ ለካህናት የሚሰጠውን ሥልጠና በጸሎትና በቡራኬ አስጀመሩ።
ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም
በጉራጌ ሀገረ ስብከት ለሚገኙ ካህናትና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የሚሰጠው የካህናት ሥልጠና በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጸሎት፣ ቡራኬና አባታዊ መመሪያ ተጀምሯል።
ይህ በሀገረ ስብከቱ በየጊዜው ከየወረዳው ካህናትን በመመልመል የሚከናወነው የማሠልጠን ተግባር፥ ብፁዕነታቸው በሀገረ ስብከቱ ከወጠኗቸውና ትኩረት ከሰጧቸው የሰው ኃይል ግንባታና ልማት ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በዚህም መሠረት በዘንድሮው መርሃ-ግብር ከ11ዱም ወረዳ ቤተ ክህነት ተመልምለው የተላኩ አገልጋዮች በሥልጠናው ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ብፁዕነታቸው በቃለቡራኬአቸው ይህ ሥልጠና አገልጋዮች ዘመኑን የዋጀ መንፈሳዊ አገልግሎት ለምዕመናን መስጠት እንዲችሉና የአገልግሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለዚህም አገልጋዮች በእውቀት ላይ የተመሠረተ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት እንዲሁም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማዕከል ያደረገ አገልግሎት እንዲሰጡ ሥልጠናው ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል።
በመጨረሻም ሥልጠናውን እየተከታተሉ የሚገኙ አገልጋዮች የተሰጣቸውን ወርቃማ ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፤ የሚያገኙትን የቤተ ክርስቲያን እውቀት በማሳታወሻቸው እንዲጽፉና በልባቸው እንዲከትቡ አባታዊ ጥሪ አቅርበዋል።
የወጣው መርሃ-ግብር እንደሚያሳየው ሥልጠናው እስከ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፥ ሰኔ 20 ቀን 2018 ዓ.ም የምስክር ወረቀት በመስጠት ይጠናቀቃል ተብሏል። ይህ የምስክር ወረቀት ግን የአገልግሎት ማጠናቀቂያ ሳይሆን ወደ ላቀ መንፈሳዊ ሥራ መሸጋገሪያና አዲስ አገልግሎት ማስጀመሪያ መሆኑ ብፁዕነታቸው በአጽንኦት አሳስበዋል።©ሳሌም ሚዲያ