ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አዲስ የተሠራውን የለገዳዲ አንቀጸ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን መረቁ፡፡

ግንቦት ፳፪ ቀን ፳፻፲ወ፰ ዓም
የለገዳዲ አንቀጸ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ ተመረቀ፡፡ ቤተክርስቲያኑን ለማጠናቀቅ ዐሥራ ሁለት ዓመት የፈጀ ሲሆን፤ በወቅቱ የመሠረት ድጋዩ የተጣለው በ፳፻፮ ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሲሆን፤ ለምርቃት የበቃውም በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ዕለት በዕለት ክትትልና አመራር ሰጪነት መሆኑን የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ቀሲስ ያሬድ ሺፈራው ያስረዳሉ፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ አያይዘውም አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው፤ በቤተክርስቲያን ሕሙማንን የሚፈውስ ታሪካዊ፣ በርካታ ገቢረ ተአምራት የሚፈጸምበት ጠበል የሚገኝ በመሆኑ ምእመናን ወደ ሥፍራው መጥተው እንዲጠመቁ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እንደተናገሩት “ ግሩም የሆነ፣ በጣም ያማረ ሕንጻ ቤተክርስቱያን አንጻችኋል፡፡ በድካማችኁ፣ በገንዘባችኁ ዘመን ተሸጋሪ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ታካዊ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ፈቅዶላችሁ፣ እናንተ የምትገለገሉበት፣ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ሠርታችሁ በማጠናቀቃችሁ እንኳ ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አያይዘውም ቤተክርስቲያኑን በፍቅር፣ በሰላም በአንድነት እንድታመሰገኑ ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ዐቢይ አበበ እንደተናገሩት ይህን ቤተክርስቲያን ስንሠራ ብዙ ነገር አሳልፈናል፤ እግዚአብሔር ለዛሬዋ ለምርቃት ቀን ስላበቃን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ብሏል፡፡
ሊቀ ብርሃናት መምህር ተክለ ብርሃን “እናንተ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆናችሁ ቤተክርስቲያን ሠርታችኋል፤ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው ቤተመቅደስ ሥሩልኝ እኔም በውስጡ እድራለሁ ያለውን ቃል ተግባራዊ ያደረጋችሁ በመሆናችሁ፤ ዕድለኞች ናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ለሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምእመናን፣ በጎ አድራጊዎችና በሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ ሲያገለግሉ የነበሩ ከብፁዕነታቸው እጅ ሽልማትና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ የለገጣፎ ለገዳዲ እና ኩራ ጂዳ፣ የመልካ ኖኖ፣ የጉጂ ገፈርሳ ክፍላተ ከተማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀ ልሣናት በዳሳ ቶላ የኮዬ ፈጬና ገላን ክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በርካታ የአካባቢው ምእመናን ተገኝተዋል፡፡©EOTC_TV

የወጨ አንቀጸ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አዲሱ ሕንጻ በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።

ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ.ም
በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት፣ በለገጣፎ ለገዳዲ እና ኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኘው የወጨ አንቀጸ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አዲስ ሕንጻ ግንባታው ተጠናቆ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።
የምረቃ መርሐ ግብር ላይ የለገጣፎ ለገዳዲ፣ የኩራ ጂዳ፣ የቡራዩ፣ የገፈርሳ፣ የጉጄ እና የመልካም ኖኖ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ አባ አፈወርቅ ዮሐንስ፣የክፍለ ከተማው ዋና ጸሐፊ መጋቤ አእላፍ ስዩም ብዙአየሁ፣የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች፣ የደብሩ አስተዳዳሪ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በርካታ ምዕመናንና ምዕመናት ተገኝተዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዕለቱ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት፤ የቤተ ክርስቲያኑን ሕንጻ በአንድ ዓመት አጭር ጊዜ ውስጥ ሠርቶ ማጠናቀቅ መቻሉ ትልቅ በረከት መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም “የመጀመሪያው ልማት እናንተ ናችሁ፤ እናንተ የክርስቶስ ሕንጻዎች ናችሁ። ስለዚህ ትውልድና ወጣቱ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፤ ሕፃናትንና ወጣቶችን በሰንበት ትምህርት ቤት ሰብስባችሁ በቅንነት ማስተማርና ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆኑ አድርጎ ማነጽ ይገባል” በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የደብሩ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለብፁዕነታቸው የቀረበ ሲሆን፤ የሕንጻ ቤተ መቅደሱን ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በማጠቃለያውም ቤተ ክርስቲያኑ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋናና የሽልማት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በመጨረሻም መርሐ ግብሩ በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ፍጻሜ ሆኗል።

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ምዕራፈ ሰማዕታት ወደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የተከናወነው የወንዝ ማስቀየስ ሥራ ተጠናቆ በብፁዓን አባቶች ቡራኬ ተመረቀ።

ከታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲገነባ በቆየው የወንዝ ማስቀየስ ሥራ በተለያየ ወረዳ ተበታትነው የነበሩ ቦታዎች ወደአንድ ወረዳ እንዲካተቱ እና ደብሩ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኝ ተደርጓል።
በከፍተኛ ወጪ በአጭር ጊዜ የተከናወነው ግንባታ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስአበባ የሀዲያ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ እና ኮሎራዶ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተባርኮ ተመርቋል።
በምረቃ መርሀ ግብሩላይ ብፁዓን አባቶች እና የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ መልዓከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን ፣ የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ሊቃውንት አባቶች የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አደፍርስ ሆራ እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
በኩረ ትጉኀን ጸጋዬ ዓለማየሁ የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ባቀረቡት ሪፖርት ደብሩ በ2012 ዓ.ም ከተመሠረተ ጀምሮ የተከናወኑ ሥራዎችን አብራርተዋል።
የክፍለ አተማው ሥራ አስፈፃሚ አቶ አደፍርስ ሆራ ቅድስት ቤተክርስቲያን የምታከናውነውን ሥራ አድንቀው በቀጣይም አብረው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል ።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብሥራት መምህር አብርሃም ዲበኩሉ በበኩላቸው በተከናወነው የልማት ሥራ አስተዋጽኦ ላበረከቱት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል ።
ከምስጋናውም ባሻገር በወንዝ ማስቀየስ ሥራው ላይ በተለያየ መልኩ ለተሳተፋ ወገኖች የምስጋና ስጦታ እና የምሥክር ወረቀት ተበርክቷል።©Eotc tv

በሸገር ሀገረ ስብከት የታነጸው የደብረ ሣህል ቅዱስ ገብርኤል አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጸሎተ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።

ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም
በሸገር ሀገረ ስብከት በስሉልታና መነአብቹ ክፍላተ ከተማ በአትሌት ፕሮጀክት መንደር የተገነባ የደብረ ሣህል ቅዱስ ገብርኤል፣ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እና ልደታ ለማርያም አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በዛሬ ዕለት ግንቦት 19/2018 ዓ/ም በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምስካየ ሕዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ጠባቂ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተባርኮ ተመርቋል።©Eotc tv

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሱማሌ ክልል ጅግጅጋ እና የምስራቅ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በምሥራቅ አርሲ አሰላ ከተማ ደብረ ምጽላል ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም
የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሱማሌ ክልል ጅግጅጋ እና የምሥራቅ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከዚህ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት ሀገረ ስብከቱን እንዲመሩ መድቧቸዋል።
በዚሁም መሠረት ብፁዕነታቸው በም0ሥራቅ አርሲ አሰላ ደብረ ምጽላል ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል ።
በአቀባበሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ የደቡብ ምስራቅ ትግራይና ራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ እና የድርጅት ኃላፊዎች ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፣የሀገረ ስብከቱ የልዩ ልዩ የክፍል ኃላፊዎች ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አባ ገዳዎችና በጣም በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
ብፁዕነታቸውና ብፁዓን አበው ሊቀነ ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያኑ ሲደርሱም ጸሎተ ወንጌልና ኪዳን ከተደረሰ በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ለብፁዕነታቸው የተዘጋጀ ደብዳቤ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦምና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ከተነበበ በኋላ ሕዝበ ክርስቲያኑ በእልልታና በደስታ ብፁዕነታቸውን ተቀብሏል።
የደብሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም የቅዱስ ያሬድ ዜማ ያቀረቡ ሲሆን በመቀጠልም ቅኔያት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቀርበዋል፡፡
የመታሰቢያ ስጦታዎችም ለብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ለብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም ለብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ተሰጥተዋል።
በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦምና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት የዕለቱን ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ የደቡብ ምሥራቅ የራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባታዊ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ሥራንና ሠራተኛን ማገናኘት የሚችሉና ጠንካራ አባት በመሆናቸው ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገረ ስብከቱ የነበረውን ችግር በማየት ሀገረ ስብከቱን እንዲያሳድጉ መመደባቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም በእምነታችን ከጸናን ሁሉም ስለሚያልፍ መጸለይ አለብን ፣ ቤተ ክርስቲያናችንን መጠበቅ አለበን በማለት አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና አባታዊ ቡራኬ የሰጡ ሲሆን ሀገረ ስብከቱ እንደ ቀደምትነቱ ብዙ ያልተሠራበት በመሆኑ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ እንደሚሰሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ሕዝቡ በቋንቋው መማር እንዳለበትና ሀገሩ እንዲለማ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ከታች ጀምሮ የተሰጣቸውን ሥራ ሁሉ በመሥራት የሚታወቁ በመሆናቸው አብሮ መሥራት ያሰጥተዋል።
በብፁዕነታቸው አባታዊ ቡራኬና ጸሎት መርሐ ግብሩ የተጠናቀቀ ሲሆን ለመንበረ ጵጵስናው ለሚሠራ ሕንጻ ፣ በጥምቀተ ባህር ግቢ ውስጥ G+6 ሁለ ገብ የሕንጻ የገበያ ማዕከል እንዲሁም ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ መሠረተ ድንጋይ ተቀምጠዋል ።
በተጨማሪም የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግና የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር ታስቦ የተገነባ ሁለገብ ሕንጻ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳተ ቡራኬ ተመርቋል።

ከግንቦት እስከ ግንቦት ክፍል ሦስት

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ሆነው እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በከፍተኛ ድምጽ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ደረጃውን
በጠበቀና የቅዱስ ሲኖዶስን ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲደራጅ ፣ እንዲጸዳና እንዲዋብ በማድረግ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ምንም ዓይነት ወጪ ሳይጠይቁ በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ያማረና ግሩም እንዲሆን አድርገውታል።
ይህም በመሆኑ ጽሕፈት ቤቱ አገልግሎቱን በተደራጀና በተቀላጠፈ አግባብ ማከናወን የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ከመቻላቸውም በላይ መደበኛና ከመደበኛ ውጪ በሆነ መልኩ የቅዱስ ሲኖዶስን ሥራ የሚያግዙ ምሁራን የሥራ ኃላፊዎችን በማሳተፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ በአግባቡ እንዲጻፍ፣የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲዘጋጅና ወጥነት ያለው የመረጃ መለዋወጫ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔዎች ተከትሎ ግልጽነት እንዲፈጠር በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስን ክብር የሚመጥኑ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ችለዋል።
ብፁዕነታቸው የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባዎች በሚደረጉበት ጊዜ ተቋማዊ መሰረታቸውን የበለጠ አጠናክረው የሚከናወኑበትን ሥርዓት በመከተል፣ቅዱስነታቸው በጤና እክል ምክንያት የቋሚ ሲኖዶስን ስብሰባ በማይመሩበት ጊዜ ቅዱስነታቸውን በመወከል የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባን በአግባቡ በመምራት ወቅታዊ መረጃዎችን ለቅዱስ ፓትርያርኩ በማስረዳትና ከቅዱስነታቸው መመሪያን ተቀብለው በአፋጣኝ በመተግበር የተዋጣለት ሥራን ሠርተዋል።በእነዚህ ጊዜያትም የቅድስት ቤተክርስቲያንንና የብፁዓን አባቶችን ክብር በማስጠበቅ ተቋማዊ ውሳኔዎችን በማስወሰንና አፈጻጸማቸውን በየወቅቱ በመከታተል አርዓያነት ያለው ሥራን ሠርተዋል።
ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው በዘመነ ሢመታቸው የተከናወኑ ሁለት ጉባኤያትን በአግባቡ በማስተባበር፣በመምራትና ሲኖዶሳዊ ክብርን የሚያስጠብቅ ማጠቃለያን በማቅረብ፣እጅግ የተረጋጋ፣ፍጹም መደማመጥ የታየበት ውጤታማ ጉባኤ እንዲካሔድ በማድረጋቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተሰማቸውን ደስታ በምስጋና ገልጸውላቸዋል።ለዚህ ውጤታማነታቸው ትልቁ ምክንያትም ብፁዕነታቸው ያላቸው የረጅም ጊዜ የሥራ ልምድ፣ብልሃት የተሞላበት የመሪነት ክህሎት፣አርቆ የማሰብ ብቃት፣መጠነ ሰፊ ተቋማዊ አመለካከት፣ ለቤተክርስቲያን ሉዓላዊነት እና ክብር በቆራጥነት የመሥራት የዳበረ ልምድና ፍጹም የሆነ የሁለንተናዊ ብቃት ባለቤት መሆናቸው እንደሆነ የሚጠራጠር አይደለም።
ከፍ ሲል በተጠቀሱት ዋናዋና ምክንያቶችም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የአንድ ዓመት የሥራ አፈጻጸም እጅግ ስኬታማና የተዋጣለት መሆን ችሏል።
ከግንቦት እስከ ግንቦት በቤተክርስቲያናችን ደረጃ የተመዘገቡት ውጤቶች እጅግ በአጭሩ በሦስት ክፍል የተመለከትናቸው ሲሆኑ የተመዘገቡት ውጤቶች ሊመዘገቡ የቻሉት አልጋ በአልጋ በሆነ የማስፈጸምና የመፈጸም ሂደት አልነበረም።ይልቁኑ በርካታ እሾህና አሜኬላ ታልፎ እንጂ፤በቤተክህነት ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ውጤት የተመዘገበውም ሁለቱ ብፁዓን አባትች በርካታና እልህ አስጨራሽ ተግዳሮቶችን በድል እድራጊነት ተወጥተው እንደሆነም ብዙ ማሳያዎችን መደርደር ይቻላል።
ከሁሉ የከፋውና አሁን ድረስ ልዩልዩ ሥልቶችን በመቀየር እየተሞከረ የሚገኘው ታላቁ ተግዳሮት ሁለቱን አባቶች ለመለያየት እየተደረገ ያለው ያልተሳካና ሊሳካ የማይችለው ሙከራ ሲሆን መሰረታዊ ምክንያቱ አሁን የተመዘገበውና ወደፊት የሚመዘገበው ውጤት እንዴት በሁለቱ አባቶች ዘመነ ሢመት ይሆናል? ከሚል ቤተክህነታዊ ቅንአት የሚነሳ ሆኖ መዳረሻው ዘረኝነትን በማስፋፋት ቤተክርስቲያንን የፖለቲካዊ ፍላጎቶች ማስፈጸሚያ መድረክ ማድረግን መሰረት ያደረገ ሆኖ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ በተደራጀ መልኩ የሚከወን እኩይ ተግባር እንደሆነም ግልጽ ነው።
ይህ በደንብ የገባቸውና የዚህ እኩይ ዓላማ አስፈጻሚዎች እነማን እንደሆኑ ጠንቅቀው የሚያውቁት ብፁዓን አባቶቻችን እነዚህ እኩያን በሁለቱ መካከል የሚገቡበት ቀዳዳ እንዳይኖር በማድረግና በዋና ሥራቸው ላይ ብቻ በማተኮር ባደረጉት እንቅስቃሴ የሚታይና የሚዳሰስ ውጤትን ሲያስመዘግቡ በሌላ በኩል ደግሞ የነዚህን እኩያን ፍላጎት ማምከን ችለዋል።
ይሁን እንጂ ሁለቱን ካላለያዩ፣በመካከታቸው መለያየትን ካልፈጠሩ፣ ፓለቲካዊ ዓላማቸውን ማስፈጸም እንደማይችሉ የተገነዘቡት የቤተክህነቱ ተግዳሮት ጠንሳሾች አንድ ጊዜ የፌስቡክ ሰራዊት በማደራጀትና የሐሰት ስም ማጥፋት ላይ በመሰማራት፣ ሌላ ጊዜ የአንደኛው አባት ተቆርቋሪ በመምሰልና የሐሰት ፕፖጋንዳን መሰረት ያደረገ ዘመቻን በመዝመት፣ሲያሻቸው ደግሞ የሚቀርቧቸውን አባቶች በማሳመንና አንዱ በአንዱ ላይ ጥርጣሬን በመፍጠር ወደ ጸብ እንዲገቡ በመጎትጎት፣ሲቀጥሉ ደግሞ የሁለቱ አባቶች ቀራቢ ናቸው የሚባሉ ሰዎችን በጥቅማጥቅም በመደለል እሱ አልሳካ ሲላቸው ደግሞ በነዚሁ ወገኖች ላይ ጠላቶችን በማደራጀት እንዲነሱባቸውና እንዲወነጀሉ በማድረግ፣ ሲጨንቃቸው የነሱ ተከታዮች በመሆን አባቶችን እንዲክዱ በማግባባት ሲብሰ ደግሞ ሁለቱን አባቶች በንዋይ በመደለል አንድነታቸውን ለማናጋት ብዙ ቢጥሩም የሁለቱ ብፁዓን አባቶች የኖረና ሦስት አሥርታትን የዘለቀ ወንድማማችነትን መናድ ሳይችል በመቅረታቸው እነሆ በፍቅርና በአንድነት ከግንቦት እስከ ግንቦት በስኬት መዝለቅ ችለዋል።
ለወደፊትም አንድነታቸውን አጽንተው፣ወንድማማችነታቸውን አሳድገው፣በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበው ፣የቤተክርስቲያንን
ጥቅም አስከብረው፣ የጠቅላይ ቤተክህነቱን አሰራር አዘምነው፣ ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ ጽፈው፣በጥቅሉ ቤተክርስቲያንን ለመበተን መከራ የሚበሉ ሕልመኞችን ፍላጎት አክሽፈው ቀሪ ዘመነ ሢመታቸውን ከአሁን በበለጠ አንድነትና ፍቅር በመፈጸም የቤተክርስቲያንን አስተዳደራዊ ትንሳኤን እንደሚያበስሩ ጥርጥር የለውም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ግንቦት ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም 81ኛ ዓመት የአንድነት ኑሮ ምሥረታ ክብረ በዓል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ተከብረ

ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም
የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም 81ኛ ዓመት የአንድነት ኑሮ ምሥረታ ክብረ እጅግ ባማረ በድምቀት ተከብረ በበዓሉም ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የማይጨው አላማጣ እና ራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እና ማኅበራት ምዝገባ ክትትል እና ቁጥጥር መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው የሥራ ኃላፊዎች ፣ አበው መነኮሳት ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል ።
በዕለቱም በሚያዚያ 27 ቀን 2018 ዓ.ም የ76 ኛ ዓመት የቅዳሴ ቤቱ ክብረ በዓል በማስተባበር እንዲሁም ልዩ አስተዋፅኦ ላደረጉ የገዳሙ ባለሟሎች የሰርተፍኬት ስጦታ ተበርክቶላቸው በጸሎት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል ።©ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም
ሚዲያ

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአዲስ አበባ የሰላምና የያብሮነት የጸሎት መርሐ ግብር ” ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን ” በሚል መሪ ቃል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የሌሎች ሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት አደረገ

ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም
በአራዳ ፓርክ በተከናወነው ጸሎት መርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤አገኘሁ ተሻገር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ፣ አቶ አደም ፋራህ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና ኃላፊ ፣ አቶ መሀመድ እንድሪስ የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ፣
ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ የጠቅላይ ቤተክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ : መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ሓላፊዎች የየገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተዘጋጀው ሀገር አቀፍ ልዩ የጸሎት መርሐ ግብር ላይ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ባደረጉት ንግግር ዘጠና ስምንት በመቶ አማኝ ህዝብ ያለበ ሀገር ዎች እንደመሆኑ መጠን የሃይማኖት መሪዎች ለሀገር ሰላም በአብሮነት መቆም አስፈላጊ በመሆኑ በአንድነት ለሀገር ሰላም ልንጸልይ ይገባል ብለዋል ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሊቃነጳጳስ ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ሓላፊዎች እና የአድባራት አስተዳዳሪዎች የመሐረነ አብ ጽሎት ያደረሱ ሲሆን በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለምዕዳን እና ቡራኬ ተሰጥቷል።© EOTC tv

የአዳማ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምህረት ካቴድራል 1ኛ ዓመት የቅዳሴ ቤት ክብረ በዓል ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ በተገኙበት ተከበረ

ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም
ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀማዳዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ቡራኬ ተባርኮ የተመረቀው የአዳማ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምህረት ካቴድራል አንደኛ ዓመት የቅዳሴ ቤቷ ክብረ በዓል በዛሬዋ ዕለት፤
ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባልና የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ በተገኙበት ተከብሯል።
በክብረ በዓሉም ላይም መልአከ ሣህል ቀሲስ ነጋሽ ሀብተ ወልድ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የሀገረ ስብከቱ የየመምሪያው ክፍል ኃላፊዎች ፣ የገዳማት አድባራት አስተዳደሪዎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ወዲያቆናት መምህራነ ወንጌል ፣ የሰንበት ት/ቤት ዘማርያን ማኅበራት: አባ ገዳዎችና አደ ስንቄዎች በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ተገኝተዋል። ©ሐመረ ተዋሕዶ ሚዲያ

በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ

ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም
ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሓላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ሌሎችም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።
በተጨማሪ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች ፤ መልአከ ገነት መምህር ኤርምያስ ውብሸት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ፤ አገልጋይ ካህናትና ፤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ዘማሪያንና በርካታ ምእመናን ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር የበረከቱ ተካፋይ ሁነዋል።
በዚሁ መርሐ ግብር ታቦተ ሕጉ ከመንበሩ ወጥቶ ምእመናንን የባረከ ሲሆን በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና በሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ለምርቃት መብቃቱንና የቅዳሴ ቤቱ መከበሩን የሚያዘክር ያሬዳዊ ጥዑመ ዜማ ቀርቧል።
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሓላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርት ደግሞ በአዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን “ቅዳሴው በሊቃነ ጳጳሳት ተቀድሶበታል ፣ሕፃናት አረጋዊያንም ቆርበውበታል ፣ከዚህ የበለጠ ደስታ ምንም ነገር የለም ፣ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንዲጠናቀቅ መመሪያ ሰጥተው ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ እንዲከበር ላደረጉት ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉም ተደምጠዋል።
ከዚህ በመለስ የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታ ለፍፃሜው እንዲበቃ ገንዘባቸውን ፣ እውቀታቸውንና ጊዜያቸውን በበጎ ፈቃደኝነት የሰጡ እንዲሁም በአስተባባሪነት ፣ በልዩ ልዩ የሥራ ድርሻዎችና ሓላፊነቶች የጎላ ድርሻ የነበራቸው ሁሉ ከቅዱስ አባታችን ሽልማት ወስደዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለማነፅ አነሳስቶ ስላስፈፀማችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።
ቅዱስ አባታችን ለለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ምእመናን “ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ለብዙ ዘመናት መገልገያ የሚሆናችሁን እግዚአብሔርን የምታመሰግኑበት ፣ የምትቆርቡበትን ሕንፃ ቤተክርስቲያን ነው የገነባችሁትና እንኳን ደስ ያላችሁ” ሲሉም አክለዋል።
ቅዱስነታቸው “ከዛሬ ጀምሮ ይህንን አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ካቴድራል ብለነዋል” ያሉ ሲሆን ቤተክርስቲያኑ በስያሜው ልክ መሆን ስለሚገባው ትምህርት ቤትና ሌሎችንም ከዚህ የበለጠ ልማት ሊሰራበት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ከ፻ ሚሊየን ብር በላይ ፈሰስ ተደርጎበት ለምርቃት የበቃው የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ጥር 29 ቀን 2002 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት፣ የዓለም የሰላም አምባሳደር የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት ግንባታው መጀመሩ ይታወቃል።
©Eotc tv