ደንበኛ ተኮር ስርዓት የወለደው የነዋሪዎች አንድነት ከድርጅቱ አልፎ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጋርም እያስተሳሰረ መሆኑ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የተጀመረው ደንበኛ ተኮር ስርዓት ደንበኞችን ከድርጅቱ ጋር ከማቆራኘት አልፎ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጋር መናበብን የፈጠረ ሲሆን ይህንኑ በሚገልጽና ተባባሪነትን በሚያሳይ መልኩ በዛሬው እለት የጽዳት ዘመቻ አካሂዷል።
የጽዳት ዘመቻው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳም የበላይ ኀላፊ፤ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅርሳቅርስ ፣ ቤተመጻሕፍትና ወመዘክር ፣ የማኅበራት ፣ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያዎች የበላይ ኀላፊ፣ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊና የመንትዮች ሕንፃ ነዋሪዎች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን ወደፊት በሁሉም ሕንፃዎች እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ይህ የጽዳት ዘመቻ ከአከራይና ተከራይ ትስስር ባለፈ በባለቤትነት ስሜት እንዲገለገሉ የሚያቀራርብና ወደፊትም በትብብር ቤተክርስቲያንን ለማገልገል የሚረዳ እንዲሁም ነዋሪዎች ለኑሮ የሚመርጡት ሥፍራ ምቹ ፣ ጽዱና ማራኪ ሕንጻዎች እንዲሆኑ የሚያደርግና የሚያግዝ በመሆኑ በየወሩ መካሄድ እንዳለበት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
የብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊምው በበኩላቸዉ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት በዋናው መሥሪያ ቤት እየተከናወነ የሚገኘው ቅጥር ጊቢውን የማስዋብ ሥራ ወደ ውጭ ወጥቶ የድርጅቱ ደንበኞች በሚገኙበት ሁሉ መቀጠል እንዳለበት ሲያሳስቡ ቤተክርስቲያን የንጽሕና አዳራሽ ናት ። ንጽሕና የክርስትና ዋና መገለጫ ነው። ይህንን ማድረግ ክርስትናን መግለጽ ሲሆን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የፈነጠቀው የልማት ጀምበር በሁሉም ሕንጻዎች መካሄድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በተለይም የድርጅቱ ደንበኞች እስካለሁ እኖራለሁ በሚል ጠባብ አስተሳሰብ ውስጥ እንዳይገቡና በባለቤትነት ስሜት የተከራዩትን ቤት በአግባቡ በመጠቀም ትብብራቸውን እንዲያሳዩ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የሁሉም ሕንፃ ነዋሪ ኮሚቴዎች በየጊዜው ይህንን የጽዳት ዘመቻ ለመካሄድ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን በዘሬው እለትም የጽዳት ዘመቻ ያደረጉት የመንትዮች ሕንፃ ነዋሪዎችና ኮሚቴዎች ባደረጉት ሥራ ፈር ቀዳጅ በመሆናቸው ተመስግነው በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተጠናቋል።

በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ቡራኬ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ተከናወነ

ግንቦት ፲፭ ቀን ፳፻፲ወ፰ ዓ.ም
በቡራኬ ቤተክርስቲያን መርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሓላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ሌሎችም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።
በተጨማሪ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች ፤ መልአከ ገነት መምህር ኤርምያስ ውብሸት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ፤ አገልጋይ ካህናትና ፤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ዘማሪያንና በርካታ ምእመናን በቡራኬ ቤተክርስቲያን በዓሉ ላይ ታድመዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት “ለበርካታ ዓመታት ደክማችሁ ይህንን ሕንጻ ቤተክርስቲያን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ በማስመረቃችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ቤተመቅደሱ እውን እንዲሆን የደከሙ ምእመናን ፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት ፣ የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴዎች በሰማይም በምድርም ትልቅ ክብር የሚያገኙበትን ቅዱስ ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
“ዐይኖቸና ልቤ በዚህ ሥፍራ ለዘለዓለም ይሆናሉ” የሚለውን ቅዱሱን የእግዚአብሔር ቃል መነሻ አድርገው ፤ ለምርቃት የበቃው የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ሥጋውን የምንበላበት ደሙን የምንጠጣበት ፣ የካህናት ጸሎት የሚያርግበት ነውና “እንኳን ደስ አላችሁ” ያሉት ደግሞ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ቡራኬ ላይ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሓላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርት “ቤተመቅደሱ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ፣ ካህናት የሚዘምሩበት ፣ ምእመናን የሚጸልዩበት ፣ ሕጻናት የሚቆርቡበት ፣ አረጋዊያን የሚማፀኑበት ፣ በመጨረሻም ደግሞ የኦርቶዶክሳዊያን ዘላቂ ማረፊያ ነው” ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሲሰጡ ሸገር ከተማ በሀገረ ስብከት ደረጃ ተቋቁሞ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ መመራት ከጀመረ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው ለውጥ እንዳስደሰታቸው ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በመርሐ ግብሩ ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለበርካታ ዓመታት ከግንባታ ውጭ ሁኖ መቆየቱን በማስተዋል በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ መመሪያ ሰጥተው ዛሬ ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ለምርቃት እንዲበቃ ላደረጉት ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ምስጋና ቀርቧል።
በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንፃ ቤተክርስቲያን ጥር 29 ቀን 2002 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት፣ የዓለም የሰላም አምባሳደር የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት ግንባታው መጀመሩ ይታወቃል።©Eotc.tv.

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ለሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለአገልግሎት የሚሆን ፕራዶ መኪና ገዝቶ በስጦታ አበረከተ

ግንቦት ፲፫ ቀን ፳፻፲ወ፰ ዓ.ም
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመኪናውን ቁልፍ ለብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሸካ ቤንች ማጂ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ የበላይ ኃላፊ አበርክተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት “ሥራ የሚሠራ ሰው ዋጋ ይገባዋል፡፡ ለአገልግሎት የሚሆን መኪና አስፈላጊ ነው፡፡ ብፁዕነትዎ እርስዎ ብዙ ጊዜ ሲጠይቁ ቆይተው አሁን ማግኘትዎ በጣም ደስ ብሎናል፤ ለአገልግሎት የሚሆን መኪና ስላገኙ ሁላችንም ደስ ብሎናል፤ እግዚአብሔር የተባረከ ያድርግልዎት” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት “ቀደም ሲል ለቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተያዘው በጀት ዓመት ቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ አባታችን መመሪያ ሰጪነትና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ፕራዶ መኪና እንዲገዛ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በጠየቁት መሠረት ጥሩ መኪና ተገዝቶላቸዋል፡፡ ብለውል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልም እንደተናገሩት “እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜና ሰዓት ጥሩ መኪና ተገዝቶልናል፤ ለዚህም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አስተዋጽኦ መሠረት ሲሆን፤ ይህን ያደረገ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፣ እግዚአብሔር ይስጥልን ስለተደረገልኝ በጣም አመሰግናለው” ብለዋል፡፡
የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት ከተመሠረተበት ከ1935 ዓም ጀምሮ መንፈሳዊውንና ዘመናዊውን ትምህርት ጎን ለጎን በማስተማር አያሌ ሊቃውንትን፣ ጳጳሳትንና ሊቃነ ጳጳሳትን በማፍራት የታወቀ አንጋፋ ትምህርት ቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡በአሁኑ ወቅትም የትምህርት አድማሱን በማስፋት የትምህርት አገልግሎቱን አጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑ ይታወቃል፡፡
©Eotc tv

ክፍል ሁለት …..” ከግንቦት እስከ ግንቦት ” እንደሚከተለው ይቀርባል

ባለፈው “ከግንቦት እስከ ግንቦት” ዝግጅታችን በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ዘመነ ሢመት የተከናወኑ ዋናዋና ሥራዎችን በመጠኑ የዳሰስንበትን ዘገባ ለንባብ ማቅረባችን ይታወሳል።ቀጣዩን ክፍል እንደሚከተለው እናቀርባለን፦
7.ኛ ቤተክርስቲያን በመጪው ዘመን መንፈሳዊ አገልግሎቷን ለማሳለጥ፣ ቀደምት አባቶቻችን ጥለውልን በሄዱት ይዞታዎች ላይ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ሠርታ ለማስተላለፍ እንዲሁም በከተማችን የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍና በከተማችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት በሚያስችላት መልኩ በፒያሳና በአራት ኪሉ በብዙ ቢሊየን ብር ወጪ ግዙፋን ሁለገብ ሕንጻዎችን ለመገንባት የሚያስችላትን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በሚገባ ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ግንባታ ሥራ በመግባት በፍጥነት የግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።ይህ የግንባታ ሥራ ጊዜያዊ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር ባለፈ ተጨማሪ ቋሚ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ዜጎችን የሚጠቅም እንደሚሆንም ይታመናል።ይህንን ውጤታማ ሥራ በሚገባ በመምራት ፣በማደራጀትና በመቆጣጠር ረገድም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ስኬታማ ሥራ እየሠሩ ነው።
8ኛ ባለፈው ዐንድ ዓመት ውስጥ በቤተክርስቲያናችን ዋናዋና መምሪያዎች የተከናወኑት የለውጥና የሕዳሴ ሥራዎች ለተቋሙ ሁለንተናዊ ዕድገትና መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦን የሚያበረክቱ ከመሆን ባለፈ የቤተክርስቲያናችን ቁልፍ ሥራ የሆነውን የስብከተ ወንጌል መስፋፋትና መጠናከርን ዕውን ከማድረግ ባሻገር የመምሪያውን ሥራ በሚደግፉ ክፍሎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበበትም ነበር።
ከእነዚህ ክፍሎች መካከልም ኢ/ኦ/ቲ/ሲ ቴሌቪዥን አንዱና ዋነኛው ነው።ድርጅቱ በተለይም በሁለቱ ብፁዓን አባቶች ዘመነ ሢመት ከፍተኛ መነቃቃት ከታየባቸው የቤተክርስቲያናችን ተቋማት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሲሆን የፕሮግራም ይዘቶች መሻሻል፣የዜናና የፕሮግራም አቀራረቦች ዘመኑን የሚመጥኑ እንዲሆኑ መደረጉ፣ዜናዎች በመልክና በይዘታቸው ተለይተው እንዲሰራጩ መደረጉ፣ወቅታዊ ፕሮግራሞች ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲለቀቁ መደረጉ፣የቀጥታ ሥርጭቶችና አስፈላጊ መረጃዎች በፍጥነት እንዲሰራጩ መደረጉ ወዘተ…ድርጅቱ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በስኬት ካከናወናቸው በርካታ ውጤቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
እነዚህ ስኬቶች ሊመዘገቡ የቻሉትም የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ፣የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፣የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች፣የመርሐ ግብር አዘጋጆችና ጋዜጠኞች ተናበውና ዕቅድ አውጥተው በመሥራታቸው እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አመራር፣ክትትልና ድጋፍ ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስድ በመሆኑ ለለውጡ መመዝገብ ትልቁን ድርሻ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የሚወስዱት ይሆናል።ይህም የብፁዕነታቸውን የመሪነት ጥበብና የለውጥ ሰውነት የሚገልጽ በመሆኑ ለለውጡ መመዝገብ ብፁዕነታቸው የከፈሉ መስዋዕትነት ፍሬ እንዲያፈራ በማድረግ ረገድ በትጋት በመሥራት ላይ የሚገኙትን የድርጅቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ቁርጠኝነትና የመሪነት ጥበብ ዕውቅና መስጠትም የሚገባ ይሆናል።
9.ኛ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዘመነ ሢመታቸው ትልቅ ውጤት ካስመዘገቡባቸው ተቋማት መካከል የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያና የገዳማት አስተዳደር መምሪያዎች ተጠቃሾች ሲሆኑ በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በኩል የሰበካ ጉባኤ ስምሪት መደረጉ፣የተሳካ ዓለምዓቀፍ የሰበካ ጉባኤ መካሔዱ፣ልዩልዩ ሥልጠናዎች መሰጠታቸው፣ወዘተ ተጠቃሽ የብፁዕነታቸው ዘመነ ሢመት ውጤቶች በመሆን በታሪክ ተመዝግበዋል።በሌላ በኩል የገዳማት አስተዳደር መምሪያም ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን ለገዳማት አበ ምኔቶች፣ለገዳማውያንና ለሚመለከታቸው ሁሉ በመስጠት፣በገዳማት አስተዳደር በኩል ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ ያደረገ ሲሆን በገዳማት አስተዳደር መምሪያ በኩል ከፍተኛ መነቃቃትና ተጨባጭ የሥራ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል።ለዚህ ስኬትም የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቆራጥ አመራር የመምሪያ ኃላፊው ለሥራው ትኩረት መስጠትና በብቃት የመምራት ክህሎት ታክሎበት በመምሪያው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣትና በመምሪያውና በገዳማት መካከል ተገቢ የሆነ የሥራ ትስስር ፣መነቃቃትና ውጤት መመዝገብ አስችሏል።
10.ኛ ቅድስት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የምታከብራቸው የአደባባይ በዓላት በደመቀና ባማረ መልኩ እንዲከበሩ በማድረግ ሂደት ውስጥ በየ ዘመናቱ በርካታ ሥራዎች የሚሠሩ እንደሆነና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ በዓላት እንደሆኑም ይታወቃል።እነዚህ በዓላት በዓለም አቀፉ ተቋም በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገቡና የቤተክርስቲያናችን ዐበይት በዓላት በመሆናቸው በልዩ ትኩረትና በድምቀት መከበር እንዳለባቸው በጽኑ የሚገነዘቡት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዓላቶቹን በተቻለ አቅም በከፍተኛ ድምቀት፣ወጪ ቀናሽ በሆነ ስልትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማክበር ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ሁለቱ የአደባባይ በዓላቶቻችን ማለትም የመስቀልና የጥምቀት በዓላት እጅግ ባማረና በደመቀ መልኩ ተከብረው መዋል እንዲችሉ አድርገዋል።
በተለይም የአደባባይ በዓላቶቹ ወጪዎች በከተማ አስተዳደሩ በኩል እንዲሸፈኑ፣ተገቢው የጸጥታ ሥራ እንዲሠራ፣የበዓል ዝግጁቱ የቤተክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ትውፊት በጠበቀ መልኩ እንዲከናወንና የአከባበር መርሐ ግብሩም የተዋጣለት እንዲሆን በማድረግ ረገድ ብፁዕነታቸው የሰጡት አመራር በዓላቱ የአገራችንን የሃይማኖት መሰረትነትና የቤተክርስቲያንንና የመንግሥትን አስፈላጊ ግንኙነቶችን በማጠንከር ረገድ ውጤታማ በመሆናቸው የ2018 ዓ.ም የመስቀልና የጥምቀት በዓላት በተዋቡ፣በተረጋጉና በደመቁ ሁኔታ ተከብረው መዋል ይችሉ ዘንድ ብፁዕነታቸው የሚጠበቅባቸውን የመሪነት ሚና በሚገባ ተወጥተዋል።
11.ኛ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዘመነ ሢመታቸው ከሠሯቸው በርካታና ውጤታማ ሥራዎች መካከል እጅግ አስገራሚና ልዩ ሥራ ተደርጎ በታሪክ መዝገብ ከሚሰፍሩ ሥራዎቻቸው መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው የሸገር ሀገረ ስብከት ውጤታማ ሥራቸውና ከአስተዳደራዊ ሥራዎች በተጓዳኝ የሚያከናውኗቸው የመንፈሳዊ አገልግሎቶች ናቸው።
ብፁዕነታቸው በሚገርም ትጋትና ብቃት የአስተዳደራዊና የልማት ሥራዎችን ከመምራት ጎን ለጎን በዓበይት በዓላት፣በአብያተ ክርስቲያናት ምረቃ፣በስብከተ ወንጌል አገልግሎቶች፣ወዘተ
በሀገረ ስብከታቸው በየጊዜው በመገኘት በአስገራሚ ሁኔታ መንፈሳዊውን ዘርፍ በመምራት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ውጤት አስመዝግበዋል።በተለይም ወጣቱ ትውልድ በስብከተ ወንጌል አማካኝነት፣በቃለ እግዚአብሔር ታንጾ እንዲያድግና የቤተክርስቲያን ተረካቢ እንዲሆን በማድረግ ረገድ እያደረጉት ያለው ጥረትና እያስመዘገቡት ያለው ውጤት የሚያስገርምና የመሪነት ብቃታቸውን የሚያሳይ ነው።
ከዚህ ትጋት ጎን ለጎንም በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበርና ወደ ሥራ በማሰማራት የጠቅላይ ቤተክህነቱንና የሸገር ሀገረ ስብከት ቢሮዎችን የቤተክርስቲያንን ክብርና ልዕልና በሚመጥን መልኩ በማስዋብና ግብዓቶችን በማሟላት የተቋማቱን ክብር ከፍ በደርግ፣በተቋማችን እንድንመካና እንድንደሰት የሚያደርግ ሥራን ሠርተዋል።
12.ኛ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዘመነ ሢመታቸው ካስመዘገቧቸው በርካታና ስኬታማ ሥራዎች መካከል የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የዕድሳት ሥራ አንዱ ሲሆን ገዳሙ ለበርካታ ዓመታት ተገቢው የዕድሳት ሥራ ሳይደረግለት መቅረቱን ተከትሎ ወደ መቅደሱ ሳይቀር ዝናብ እየገባ መንፈሳዊ አገልግሎቱን እያወከ ከመቆየቱም በላይ ቅጽር ጊቢውና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሥፍራዎች ተጎሳቁለው አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆኑን በመገንዘብ ከገዳሙ የሥራ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በመነሳት ሕንጻ ቤተኮርስቲያኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታድሶ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ሥራን በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
በዚህም ሕንጻ ቤተኮርስቲያኑን ለማደስና ወደ አገልግሎት ለመመለሰ የሚያስችል ሥራን በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገባ በመሥራት በመጪው ሐምሌ ወር ቤተክርስቲያኑ እንዲመረቅና ታቦተ ሕጉ ወደ ቤተክርስቲያኑ እንዲመለስ የሰጡትን መመሪያ ተከትሎ የቤተክርስቲያኑ የዕድሳት ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በመጪው ወር መጀመሪያ ላይ ሥራው ተጠናቆ ርክክብ የሚፈጸም ይሆናል።ይህም የብፁዕነታቸው የአመራርና የሥራ ውጤት በመሆን በታሪክ መዝገብ በደማቅ ቀለም የሚመዘገብ ይሆናል።
ይ ቀ ጥ ላ ል በክፍል ሦስት ዝግጅታችን የቅዲስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤትን የሥራ እንቅስቃሴን፣የቋሚ ሲኖዶስ እና የምልዓተ ጉባኤውን ስብሰባዎች በመዳሰስ የብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊውን “ከግንቦት እስከ ግንቦት”የሥራ ስኬቶችን እና የሁለቱ አባቶችን ዘመነ ሢመት ተግዳሮቶች እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመዳሰስ የምናቀርብ ይሆናል።ቸር እንሰንብት።

የለገጣፎ ደብረ ብፁዓን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ አቡነ ሀብተ ማርያም እና አቡነ ሐራ ድንግል ዘመናዊ የፀበል ቤት በብፁዕ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተባርኮ ተመረቀ

ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም
በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት፣ በለገጣፎ ለገዳዲ እና ኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኘው የደብረ ብፁዓን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ አቡነ ሀብተ ማርያም ወአቡነ ሐራ ድንግል በዘመናዊ መልክ ያስገነባው የፀበል ቤት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የለገጣፎ ለገዳዲ እና ኩራ ጂዳ፣ የቡራዩ ገፈርሳ፣ የጉጄ መልካ ኖኖ ክፍላተ ከተማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ የክፍለ ከተማው ዋና ጸሐፊ መጋቤ አእላፍ ስዩም ብዙአየሁ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ሐዲስ ሙሴ በለጠ፣ አባቶች ካህናት እና በርካታ ምዕመናንና ምዕመናት ተገኝተዋል።
በዚሁ መርሐ ግብር ላይ የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ሐዲስ ሙሴ በለጠ የደብሩን አጠቃላይ የሥራ ሪፖርት ለብፁዕነታቸው አቅርበዋል።
ብፁዕነታቸው በእለቱ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት፤ “በጌጠኛ ቤትህ ልማት ይሁን” በሚል ኃይለ ቃል ሰፊ ትምህርት የሰጡ ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ልማቶችን እንደምታከናውን አብራርተዋል።
የመጀመሪያውና ዋናው ልማት የክርስቶስ ሕንጻ የሆነውን የሰውን ልጅ አእምሮ በወንጌል ማልማትና የጠፉትን በጎች ፈልጎ ወደ በረቱ መመለስ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ምዕመናን የሚፈወሱበትን የፀበል ቤት ማዘጋጀትና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎችን በመገንባት ቤተ ክርስቲያን ራሷን እንድትችል ማድረግ ነው ብለዋል። አክለውም ፀበሉ ለሕሙማንና ለድውያን ትልቅ የፈውስ ቦታ መሆኑን ገልጸዋል።
በመቀጠልም የፀበል ቤቱን ግንባታ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ያሠሩትን ለኃይለ ሚካኤል እና ለባለቤታቸው ለወይዘሮ ሥርጉተ ገብርኤል ብፁዕነታቸው የላቀ የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክተውላቸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በሐሳባቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምዕመናን የሽልማትና የምስጋና መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በመጨረሻም መርሐ ግብሩ በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተጠናቋል።© ሸገር ሀገረ ስብከት ሚዲያ

በአዶላ ወዩ በሚገኙ አድባራት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል ለሚማሩ ደቀመዛሙርት አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተሰጠ

ግንቦት 10ቀን 2018ዓ.ም
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በኩል ተዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት፣ በብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ የጉጂ ቦረና ሊበን እና የምዕራብ አርሲ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መመሪያ መሠረት በሁለቱም አኅጉረ ስብከቶች ተግባራዊ እየሆነ መሆኑ ተገልጿል።
በግንቦት 09 ቀን 2018 ዓ.ም በአዶላ ወዩ ለሚገኙ አድባራት የሰንበት ትምህርት ቤት ደቀመዛሙርት የተሰጠው ሥልጠና፣ በወረዳው ዋና ጸሐፊና በደብረገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ላዕከ ወንጌል ወሰን የለው ባሕሩ ተሰጥቷል።
በመርሃ ግብሩ “በሰንበት ትምህርት ቤት እና አብነት ተማሪዎች ላይ በትኩረት እንሥራ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን፣ የወረዳው ዋና ሥራ አስኪያጅና የደብረብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መጋቤ ተአምር ሃይማኖት ደኖ በተገኙበት አባታዊ ምክርና መመሪያ ተሰጥቷል።
በዕለቱ ከተለያዩ አድባራት የመጡ በርካታ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በፕሮግራሙ ላይ መሳተፋቸውን በመግለጸሰ ዘገባውን ያደረሰን የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ነው።

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ወሊሶ ማዕከል ጋር በመተባበር በአፋን ኦሮሞ የሚያገለግሉ 15 ተተኪ መምህራንን አስመረቀ

ግንቦት 09 2018 ዓ/ም
ዛሬ የተመረቁት ተተኪ መምህራን ለ፫ ወራት ግብረ ዲቁና ፣ኪዳን ፣ ሊጦን ፣ መስተበቁዕ ፣ መልክዓ ሥዕል ፣ መልክዓ ቁርባን ፣ መልክዓ ውዳሴ ፣ መልክዓ ማርያም ፣ መልከዓ ኢየሱስ በአፋን ኦሮሞ እንዲሁም ነገረ ሃይማኖታዊ ፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ ፣ የስብከት ዘዴ ፣ ሐዋሪያዊ ተልዕኮ ፣ ነገረ ቅዱሳን ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር እና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ኮርሶችን የወሰዱ ናቸው ተብሏል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ሌሎችም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።©Eotc tv

በሸገር ሀገረ ስብከት የዓለምገና ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ተመረቀ

ግንቦት 09 2018 ዓ/ም
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የኤድመንተንና የመካከለኛው ካናዳና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የሲያትልና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ጤሞቴዎስ የዳውሮና ኮንታ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ተገኝተዋል።
በተጨማሪም መልአከ ሰላም አለማየሁ ተፈራ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ፤ ቆሞስ አባ አፈወርቅ ዮሐንስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለሚኩራ ክፍላተ ከተማና በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሦስቱ ክፍላተ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ፣ መልአከ ምሕረት ፀጋየ ስለሽ የዓለምገና ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ፤ ካህናት ፣ መምህራን እና ምእመናን ተገኝተዋል።
ግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተመረቀው የዓለምገና ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በሸገር ሀገረ ስብከት በስፋት እየተካሄደ የሚገኘውን የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳ ነው ተብሏል።©Eotc tv

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅጣጫ ሰጪነት እየታደሰ የሚገኘውን ዕድሜ ጠገቡን የወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ጎበኙ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካሏት፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳም አንዱ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው ወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ነው። ገዳሙ በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተመሠረተ በወንጪ ሐይቅ ደሴት ላይ የሚገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳም ነው። ገዳሙ ከ800 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አቅጣጫ ሰጪነት እየታደሰ የሚገኝ በመሆኑ ገዳሙ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ ታዋቂ የሥነ ሕይወት (ኢኮ-ቱሪዝም) መዳረሻ ሆኗል።
ግንቦት ፯ ቀን ፳፻፲፰ ዓም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በገዳሙ እየተሠራ ያለውን ልማት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፣ ልማቱንም አድንቀዋል። ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት ይህ ቦታ በዚህ መልኩ ለምቶ በማየታችን በጣም ነው ደስ ያለን። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ይህን ቦታ በማየታቸው የቀደመውን ታሪክ ትውልዱ እንዲያውቀው በማድረግ እንዲሁም የአብነት ት/ቤት በመክፈት ተተኪ ለመፍጠር መሥራት ትልቅ ሥራ ነው። መሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረትም በአስተባባሪነት ይህን በመሥራታቸው ዕድለኛ ናቸው። በዚህ ዘመን የሚሠሩ ሥራዎች የሚያስደንቁ በመሆናቸው በጣም እናመሰግናለን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ስለ ወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም አመሠራረት የታሪክ መዛግብት ጠቅሰው ያስረዱት ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ገዳሙ በ13ኛው ክፍለ ዘመን በታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተመሠረተ ሲሆን በ15ኛው ክፍለ ዘመን በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን በኋላም በዐፄ ፋሲል እና በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የመልሶ ግንባታ ሥራ እንደተካሄደ ገልጸዋል።
ገዳሙ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ በርካታ ቅርሶች የያዘ ታሪካዊ ገዳም ነው። ከእነዚህም መካከል ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ያበረከቱት “ገድለ ቂርቆስ” ፣ ዐፄ ፋሲለደስ ያበረከቱት “ዜና ፋሲል” እና ለገዳሙ ያበረከቱት “የጎንደር ደወል” በመባል የሚታወቀው ግዙፍ የቤተ ክርስቲያን ደወል የሚጠቀሱ ናቸው።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳምና አካባቢው ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሲሆን ፣ የወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርስነቱን ጠብቆ በዘመናዊ ልማት እየተደገፈ ያለ ማራኪ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል። ይህም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትንም ፈጥሯል።
በመጨረሻም የገዳሙን ልማት የጎበኙ ብፁዓን አባቶች ገዳሙን ለማገዝና በአካባቢው የሚኖሩ ልጆችን በማስተማር ተተኪ ለማፍራት በማሰብ በየአህጉረ ስብከታቸው አብነት ት/ቤትና በመንፈሳዊ ኮሌጆች ልጆችን ለማስተማር ቃል ገብተዋል።
©Eotc tv.

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ እየተገነባ ያለውን ዓለም አቀፍ የሥብሰባ አዳራሽ ጎበኙ

ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም | የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
​የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ክብሯንና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖዋን የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎችን አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በግቢው ውስጥ የሚገኘውንና ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያካተተውን ዓለም አቀፍ የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ በቦታው ተገኝተው ጎበኙ።
በዚህ ከፍተኛ የሥራ ጉብኝት ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የድርጅት ሥራ አስኪያጆች እና የመምሪያ ኃላፊዎች መገኘታቸው የፕሮጀክቱን ታላቅነት ያመለክታል።
​ስለ ግንባታው ሂደት ዝርዝር መረጃ የሰጡት የ AV Consultant አማካሪ አርክቴክት ሳሙኤል አፈወርቅ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በ2,500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ግዙፍ ሕንጻ ሲሆን በአንድ ጊዜ 2,500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዋና አዳራሽን ጨምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ አዳራሽ፣ የሰንዳኬት (Syndicate) መሰብሰቢያ፣ የቪ.አይ.ፒ (VIP) አዳራሽና ሬስቶራንት እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቢሮዎችን በውስጡ ይዟል።
ሕንጻው ከመደበኛ የግንባታ ጥበቡ ባሻገር እስከ 30 ቋንቋዎችን በቅጽበት መተርጎም የሚችል የትርጉም ክፍል፣ ዘመናዊ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት፣ የጋዜጣዊ መግለጫ መስጫ (Press Conference) ክፍል፣ የድምፅ መከላከያ (Soundproof) ሥርዓት እና ዘመናዊ የቅዝቃዜ መቆጣጠሪያ (AC) ግብዓቶች የተሟሉለት በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያደርገዋል።
​ከቴክኖሎጂው ባሻገር ለተገልጋዮች ምቾትና ለደኅንነት ልዩ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ በአንዴ 16 ሰዎችን መጫን የሚችሉ ሁለት ሊፍቶች፣ ለ90 ሰዎች የሚሆኑ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች እና ቀድሞ እስቶር በነበረው ሰፊ ቦታ ላይ ከ300 በላይ መኪናዎችን ማቆም የሚችል ዘመናዊ ፓርኪንግ ተዘጋጅቶለታል። የሕንጻው የውስጥ (Interior) ዲዛይን የቤተ ክርስቲያኒቱን ረጅም ታሪክ፣ ጥበብና መንፈሳዊ ማንነት በሚሰብክ መልኩ የተቀረጸ ከመሆኑም በላይ አጠቃላይ ግንባታው የአረንጓዴ ልማትን (Green Infrastructure) መሠረት ያደረገ ሆኖ ለውበት የሚተከሉ ዕፅዋት በሙሉ ሀገር በቀል እንዲሆኑ ታቅዷል። በተጨማሪም የግቢውን የውሃ ችግር ለመፍታት የከርሰ ምድር ውሃ ወጥቶለታል። በ Atom Construction አማካኝነት እየተገነባ የሚገኘው ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምታካሂዳቸው ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ኩነቶች ታላቅ አቅምና ገጽታ የሚፈጥር መሆኑ በጉብኝቱ ወቅት ተመላክቷል።